Thursday, May 13, 2010

ልደታ ለማሪያም!

ስለ እመቤታችን በዓለ ልደት ከመናገር አስቀድመን ስለእመቤታችን ማንነት ማወቅ ያስፈልጋል። እመቤታችን በብዙ ትንቢት የተነገረች ናት። እመቤታቸን ለአምላክ ዙፋንነት፣ ለመለኮት ማደርያነት፣ ለአምላክ እናትነት እና ለድኅነተ ዓለም የተዘጋጀች የተመረጠች ናት።

በመሆኑም በአምላክ ሕሊና ስትታሰብ ኖራለች። በተአምረ ማርያም መቅድም- “እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በኅሊና አምላክ- እግዝእትነ ማርያም ከዓለም አስቀድሞ በአምላክ ሕሊና ትታሰብ ነበር” ይላል። እመቤታችን በአዳምም ኅሊና ስትታሰብ ነበረ። ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴዉ- “አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት- አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ” ሲል እንዳስረዳ።

ልበ አምላክ ዳዊት በመዝሙር 86.1 ና 2 ላይ “መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን:: ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን:: እምኲሉ ተዓይኒሁ ለያዕቆብ። ነኪር ነገር በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር- መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር
የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል።” በማለት የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥርወ ግንድ እንዲሁም የእርሷን
ልዩ ክብርና ጸጋ አስቀድሞ በትንቢት ገልጾ ነበር። መሠረት የተባሉት ከእናቷ ከቅድስት ሐና ከአባቷ
ከቅዱስ እያቄም ጀምሮ እስከ አብርሃም ድረስ ያሉትን ነው። የተቀደሱ ተራሮች የተባሉት እግዚአብሔር ለወዳጆቹ በተራሮች ላይ እየተገለጸ ተራሮቹን እንደቀደሳቸው (ዘጸ. 3.5፤ማቴ. 17. 1- 8) የአርሷንም አባቶች በረድኤት እየቀረበ ስለቀደሳቸው ነው። ተራራዎች እንዲሁ በረድኤት እንደተቀደሱ የእመቤታችንም አባቶች፣ ወላጆች እና ዘመዶች እንዲሁ በተቀደሱ ተራሮች ተመስለዋል። በአባቷ ወገን
ከንጉሥ ዳዊት በእናቷ ወገን ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን ናት።

እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸው ተስፋ የሚፈጸምላቸው. የተነገረላቸው ቃል የሚደርስላቸው በእመቤታችን በኩል
በመሆኑ ገና ሳትወለድ በእርሷ ይመኩ ነበር። ለምሳሌ አባቷን ክቡር ዳዊትን ብንወስድ- "በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። ልጄ ሆይ. ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ዉበትሽን ወድዶአልና፤" መዝ. 44. 9 ና 10 ብሏል።

“ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል” ማለት ከሌሎች የእሥራኤል ደናግል ሕዋሳት ይልቅ እግዚአብሔር ጽዮን የተባለች የእመቤታችንን ሕዋስ ለተዋሕዶ መረጧል ማለት ነዉ። “የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል” ማለትም እመቤታችን በማኅፀኗ 9 ወር ከ5 ቀን እግዚአብሔር የተመሰገነባት ረቂቅ ከተማ መሆኗንና ከእርሷ ድንቅ ተዋሕዶ የተደረገ መሆኑን መናገር ነዉ።

የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና መካን ነበረች። እንደ ካህኑ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥ ኢያቄምና ሐና ልጅ ስላልነበራቸው ኑሮዋቸው በሃዘን የተሞላ ነበር። በዚህም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር ከማመልከት አልቦዘኑም ነበረ። የነቢዩ ሳሙኤል እናት በመካንነቷ ዘመን ዘወትር ወደ መገናኛው ድንኳን እየሄደች በታቦተ ጽዮን ፊት ቆማ ታለቅስ እንደነበረ ሁሉ (1ኛ ሳሙ. 1፣ 9- 18) እነርሱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሄዱ ያለቅሱ ነበር። ጊዜው ሲደርስ ሁለቱም በየራሳቸው ደግ ሕልም አዩ። ወደ ሕልም ፈቺ ሄደው
ቢያስተረጉሙ ከፍጥረታት ወገን የሚተካከላትና የሚመስላት የሌለ ደግ ልጅ እንደሚወልዱ ተነገራቸው። እግዚአብሔር በሕልምም በገሃድም ምሥጢር መግለፅ ልማዱ ነው (ዘፍ. 18.1፣ መሳ. 13.3፣ ሉቃ. 1፣8 ሉቃ. 1፣16)።

ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ይህንን ምሥጢር ካወቁ በኋላ አንዲህ ዓይነቱን ፀጋ ጾም ጸሎት ይዞ መቀበል ይገባል ብለው መኝታቸውን ለይተው ሱባኤ ገቡ። በሱባኤ ጊዜ ያልተለያቸው መልአክ መኝታቸውን አንድ እንዲያደርጉ ነግሯቸው እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተፀነሰች። ይህንንም ሊቁ
አባ ሕርያቆስ ሲናገር “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እም ሐና ወኢያቄም
ተወለድኪ” ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም ከሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ አንጂ ብሏል።

እመቤታችን በማህፀን ሳለች ተአምር ታደርግ ነበር። አንዲት ዐይነ ስውር የነበረች የሐና ዘመድ ፅንሷን ለማረጋገጥ የቅድስት ሐናን ሆድ ብትዳስስ ዐይኗ በርቶላታል። እንዲሁም ሳሚናስ የሚባል ሰዉ ሞቶ ዘመዶቹ ሊቀብሩ ይዘዉት ሲሄዱ ቅድስት ሐናም ዘመዷ ነዉና እንደ ሥርዓታቸዉ አስከሬኑ የተኛበትን የአልጋዉን ሸንኮር (እግሩን) ይዛ ስታለቅስ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው ይፈውስ እንደነበረ (ሐዋ. 5. 15 ና 16)
የቅድስት ሐና ጥላ ቢያርፍበት ሳሚናስ ተነስቶ በሐና ማኅፀን ያለች ፅንስ ንጉሠ ሰማይ ወምድርን እንደምትወልድ መሰከረ። ለእመቤታችንም ምስጋና አቀረበ።

የእመቤታችን በማኅፀን ውስጥ ሆና ተአምር ማድረግ አይሁድን አስቀናቸው፤ አስቆጣቸውም። ስለዚህም ቅዱስ ኢያቄምንና ቅድስት ሐናን ከሰፈራቸዉ አባረሯቸዉ። በዚህም የተነሣ የእመቤታን ወላጆች ከአይሁድ ፊት ወደ ሊባኖስ ተራራ ሸሹ። ወደ ሊባኖስ ተራራ መሄዳቸው ለጊዜው ሽሽት ቢሆንም ምስጢሩ ግን “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ” መኃ. 4.8 የሚለው ትንቢት እንዲፈጸም ነው።
ሙሽራ የተባለች እመቤታችን ናት። ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ ሲናገር “ሙሽራዬ ሆይ ከከንፈሮችሽ ማር ይንጠባጠባል ከምላስሽ በታች ማርና ወተት አለ፣ የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ ሽታ ነው። እኅቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት” መኃ. 4. 12 ብሏል። ከከንፈሮችሽ ማር ይንጠባጠባል ሲል የአማላጅነቷን ጣዕም ማለቱ ነው። የተቆለፈ ገነት የተዘጋ ምንጭ ያለው ደግሞ
ማኅተመ ድንግልናዋን ነው።

እንግዲህ በዚህ ዓይነት ትንቢት የተነገረላት እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ ግንቦት 1 ቀን ተወለደች።
የተወለደችው የፀሐየ ጽድቅ የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ናትና የሊባኖስ ተራራ በብርሃናውያን መላእክት ተሞልቷል፤ በምስጋናም ተናውጧል። ብዙ ሰዎችም የተደረገውን ተአምር አይተው ዜናውን ሰምተው ወደዚያ ተራራ ጎርፈዋል፤ ደስታቸዉንም ገልፀዋል።

እመቤታችን የተወለደችዉ ወላጆቿ በስደት ላይ ሳሉ ነዉ። በስደት እያሉ ወላድ የምትታረስበት የላመ የጣመ ዝግጅት የለምና ዛሬ ያንን ለማስታወስ ከቤት ወጥቶ ሻይ ቡና አፍልቶ ንፍሮ ቀቅሎ በዝማሬ በትምህርተ ወንጌል የእመቤታችን የልደት በዓል ይከበራል።

በቤተ ክርስቲያን በዓሉ በማኅሌት፣ በቅዳሴ እና በልደታ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በተጨማሪ በሥርዓተ ንግሥ ይከበራል። በአጠቃላይ የእመቤታችን ልደትና የበዓሉ አከባበር ይህንን ይመስላል።
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ልጅ ከሰጠኸን እኛን የሚያገለግል ሳይሆን አንተን የሚያገለግል ይሆናል ብለው ተስለው ስለነበር እመቤታችን 3 ዓመት ሲሞላት ታህሣሥ 3 ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ወስደዉ በስዕለታቸዉ መሠረት ለእግዚአብሔር ሰጥተዋል። እመቤታችንም በቅድስና በንፅሕና በቤተ መቅደስ አድጋ ለፈጣሪ እናትነት ለድኅነተ ዓለም ምክንያትነት በቅታለች።

በድኅነተ ዓለም ሂደት ዉስጥ እመቤታችን ታላቅ ድርሻ አላት። ጌታን በመዉለድ ብቻ ሳይሆን እርሱን ይዛ በመሰደድ . በጌታችን ላይ ከአይሁድ ይደርስ በነበረዉ ተቃዉሞና መከራ ሁሉ እንደ እናትነቷ የመከራዉ ተካፋይ በመሆን እስከ መስቀሉም እስከ መቃብሩም ብዙ መከራ ተቀብላለች። ምህረትን ለሰዉ ልጅ ሁሉ በመለመን. በቃል ኪዳኗ በመጠበቅ የድኅነታችን ምክንያት ናትና በዓለ ልደቷን በታላቅ ደስታ እናከብራለን።

እድሜ ለንስሐ ጨምሮልን ለዚህ ያደረሰን አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ከእመቤታችን በረከት ረድኤት ይክፈለን፣ የእመቤታችንም እናትነት. በረከትና አማላጅነት አይለየን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አዘጋጅ፦
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት
ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በአውሮፓ ማዕከል
የሆላንድ ቀጠና ማዕከል ትምህርት ና ሐዋርያዊ አገልግሎት
ክፍል
ግንቦት 2002 ዓ.ም.

No comments:

Post a Comment