Thursday, August 16, 2012

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ዐርፈዋል


ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ዐርፈዋል እየተባለ ነው፡፡ ነገሩ እውነት ከሆነ በጣም ያሳዝናል! እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያሳርፋቸው እንላለን፡፡ 

ቤተክርስቲያን መሪዋን ስታጣ ክፉም ሆነ ደግ ትጎዳለች፡፡ ደግ መሪ ብታጣ መልካም ሥራዎቹ ለብዙዎች ፋና ወጊ በመሆን ይሰጠው የነበረው አገልግሎት በመቋረጡ ትጎዳለች፡፡ ክፉ መሪ ደግሞ በውስጡ ያስጠለላቸው ግብረ አበሮቹ ከለላቸው ባለመኖሩ ለራሳቸው ሌላ ተተኪ ለመፈለግ ወይም የተለመደውን ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ወይም ቢያንስ ባደረሱት ጥፋት ተጠያቂ ላለመሆን በድርጊታቸው ቤተክርስቲያን ትጎዳለች፡፡
አሁን የኛን ቤተክርስቲያን ሁኔታ በሁለቱም አቅጣጫ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በመጀመሪያው አቅጣጫ መልካም መሪን እግዚአብሔር የእረፍት ጊዜህ አሁን ነው፤ ና ወደ እረፍቴ ግባ ካለው ቀሪው የሚጎዳ ቢሆንም ሌላ መልካም መሪ እንዲያድለን ከመፀለይ በቀር የምናደርገው ነገር የለም፡፡ በሁለተኛው አቅጣጫ ግን መልካም መሪን እንዲያድለን ከመፀለይ በተጨማሪ ብዙ ክንውኖች ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ከማኅበር ካህናት፣ ከምዕመናን ይጠበቃል፡፡ በማወቅም ወይም በየዋህነትም በቤተክርስቲናኒቱ ውስጥ በተለይ በቤተክህነቱና በአዲስ አበባ አድባራትና ቤተክርስቲያናት ውስጥ የተሰገሰጉ ብዙ የፍቅር ንዋይ ያደረባቸው ወይም የቤተክርስቲያኒቱ ህልውናን የማይሹ ወሮበ በሎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ የመሸጋገሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን በሚከተሉት መንገዶች ጉዳት ላይ ሊጥሏት ይችላሉ፡-
1.      የራሳቸውን እንደራሴ በመንበረ ፓትርያርኩ ለማስቀመጥ በሚያደርጉት ሙከራ ብጥብጥ ሊፈጥሩና ቤተክርስቲያንን ሊያዉኩ ይችላሉ፡፡
2.     በመንበረ ፓትርያርኩ ዐቃቤ መንበር ለመምረጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ብጥብጥ ሊያስነሱ ይችላሉ፡፡
3.     የቤተክርስቲያንን ንብረቶችና ገንዘብ በማሸሽና አንድ አንድ መተኪያ የሌላቸውን ንዋተ ቅድሳት በማጥፋት ቤተክርስቲያኗን ታሪክ አልባና ቅርስ አልባ ለማድረግ ሊተጉ ይችላሉ፡፡
በጊዜያዊነት ምን መደረግ አለበት ለሚለው፡-
ከሁሉም ምዕመናን ከፈተኛ ጥረት ይጠበቃል፤ መንግስትና የቤተክርስቲያኒቱ ቋሚ ሲኖዶስ በቤተክርስቲያኒቱ ስም የተከፈቱ አካውንቶችን በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን ለጊዜው መዝጋት፣ በየጉምሩክ ፍተሻዎች ወይም በሌላ ቦታ ያላችሁ የእምነቱ ተቆርቋሪዎች የንዋያተ ቅድሳት እንቅስቃሴ ወደ ውጭ አገር እንዳይወጣ በዐይነ ቁራኛ መጠበቅ እና በፖሊስ ማስያዝ፣ በተለያዩ የአዲስ አበባ ቤተክርስቲያናት፣ አድባራትና ገዳማት ያላችሁ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች የነቀዘ አስተዳደር የተደገፉ አስተዳዳሪዎችና አመራሮቻችሁ ካሉ እነርሱ ከላይ ከለላቸውን በማጣታቸው ለመጨረሻ ጊዜ ያላቸውን ዕድል ለመጠቀም ይህንን የቤተክርስቲያን ያለመረጋጋት ወቅት በመጠቀም የቤተክርስቲያን መንፈሳው ሀብትና ንብረት ዘረፋ እንዳያከናውኑ ጥበቃ ማደረግ፣ ሊቃነ ጳጳሳትና ሌሎች ኃላፊነት ያለባችሁ ሰዎች ለጊዜው ጥሩ ዐቃቤ መንበር በኋላም ጥሩ የቤተክርስቲያን መሪን ሁሉን ባሳተፈ መልኩ በመምረጥ የተረጋጋ ሽግግር እንዲከናወን ይሁን፡፡
አምላከ ቅዱሳን የአባ ጳውሎስን ነፍስ በገነት ያሳርፍለን! ለቤተክርስቲያናችን ቅን መሪ ያድለን! አሜን!!!   

2 comments:

  1. nefisachewn begenet yanurln, Amen leagerachin selam lemelaw chiristian tinat lebetekirstian melkam abat yadililn, Amen!!!!!!!!

    ReplyDelete