ውዴ የሰላም ልብ ያለህ ወጣቱ ልጄ፣ ጉልበቴ ደከመ፤ ዓይኖቼም ደከሙ፤ እንግዲህስ ለኔ መቃብሬ የተቆፈረ ነው። ግን አንድ ተስፋ አለኝ ልጄ፤ እግዚአብሔርንም እርሱን ከ፸፭ ዓመት በላይ ስለምነው ኖሬያለሁ። ሐሳቤ በሁለት ነገር የተከፈለ ሆኖ ሐሳቤና ምኞቴን እንዲያሳካልኝና ከመንታ ሐሳቤ ክፍልፋይነት ወደ ምሉዕነት ተመልሼ ወደ መቃብሬ እንዳርፍ ነው እግዚአብሔርን ስለምነው የኖርኩት።
ውዴ ልጄ የደማችን ክፋይ፤ እነሆ በዚያ በ፭ ዓመት የፋሽስት ዘመን በዱር በገደሉ የወዳደቁትን ንጹሐንን፣ ከነጻነት በኋላ በሴረኛ ሀገር ሻጭ፣ አሽቃባጭ ባንዳዎች ተንኮልና በግብዝ ንጉሳችን ተገደሉትን አርበኞች አባቶችህን አደራ ተሸክሜ እጠብቅሀለሁ። ትመጣለህ ብየ ስጠብቅህ እነሆ ፸፭ ዓመት ሆነው፤ …. እህ … እህ … እህ ……. አይ ልጄ አሁንማ ልጄ ይኸው አደራየን ሳትቀበለኝ ዕድሜየ ወደ አንድ ምዕተ ዓመት ሞላ።
ውድ ልጄ የወገኖቼን አስከሬን ተራምጄ ጠላትን መትቻለሁ፤ የወደቀው በህይወትና በሞት መካከል ያለው ጓደኛየ አርበኛ ጠላትን ለመምታት እርሱን ዞሬ እንዳላየው፤ ከወደቀበት እንዳላነሳው፤ እርሱ የሰማይ አሞሮች፣ የዱር አራዊት ቀለብ ለመሆን፤ እኔ ግን ጠላትን በገባበት ገብቼ እንድወቃው ተማፀነኝ። የነገዋን ኢትዮጵያን እያሰበ ሞትን አልፈራትም፤ ወድቆ በሚያሳብቅ ዓይኑ የሐገር፣ የወገን ፍቅርን ለናንተ አደራ እንዳስተላልፍ በሥራው ነገረኝ። እናም ልጄ የዛሬዋን የእናንተን ዘመን በጎ፣ ሰላም፣ ፍቅር እና መልካም ለማድረግ እነሆ የወደቀውን፣ የምወደውን፣ የማውቀውን ሰው ተራምጄ ጠላትን ቆላሁት።
ውድ ልጄ! የሀገር ጠላት ባንዳዎች፣ ግብዝ ንጉስ፣ ክፉ መንፈስ ያለበት ዘመን መጥቶብን የወዳደቁትን አባቶቶችን አደራ ለመቀበል የተገባና የሚፈልግ ሰው አጣሁ፤ እነሆ ልጄ ፍቅርና ሀገር ወዳድነት በሥልጣንና በግብዝነት ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ተለወጠ፤ ልጄ፣ እኛ ሐገራችንን ከጠላት ፋሽስት ጣሊያን ነጻ ካወጣን በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በየክፍረለ ሀገሩ የነበሩት ጠላትን መውጪያ መግቢያ ያሳጡት አርበኞች ስልጣንና ዕውቅና ተነፍጓቸው በየክፍለ ሀገሩ የነበሩ ሀገር ክደው ለጠላት ያደሩ ባንዳዎች ሹመትና ሽልማት ተሰጣቸው። እንግዲህ የዚያን ጊዜ ነው “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፤” ተብሎ የተገጠመና የተዘፈነው።
ልጄ! ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለወገኑ የሚኖር ሰው እየተገለለ በሀሰተኛ ክስ፣ በብልጣ ብልጥ ራስ ወዳዶች እየተገፋ፣ እየተሰደደ፣ እየተገደለ፣ እየታሰረ ወዘተርፈ እነሆ ጨለማ፣ ምቀኝነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ብልጣ ብልጥነት፣ ሀሰተኝነት፣ ጎሰኝነትና ጎጠኝነት፣ ሙሰኝነትና ስልጣን ወዳድነት በመሳሰሉት ክፉ መናፍስት ትውልዱ ተይዞ ክቡር ዕንቁ የሆነው የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብና የመከባበር አደራ ተናቀ።
ይህ አደራ ከሥረ-መሰረቱ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ በአስራ ሰባተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ ለአንድ መቶ ሰባ ዓመታት ካሁኑ ሁኔታ ጋር በተመሳሰለ ሁኔታ ይህ መልካም አደራ ተዳክሞ በአስራ ዘጠንኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ተመልሶ ለምልሞ፣ በአድዋ አብቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ከቆየ በኋላ እነዚያ ውድና ዕንቁ አርበኞች ጓደኞቼ በደማቸው ጽፈው ለኔ አስረከቡኝ።
እነሆ ልጆቻቸውና ልጆቼ አደራየን ለመቀበል በ፲፱፵ዎቹ እንቅስቃሴ ጀምረው የኤርትራን ፌደሬሽን በውብ ሥነ-ጽሑፋቸውና በክርክራቸው ውብ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር። ነገር ግን ልጄ! በዚያ ጊዜ ግብዝ ንጉሳችንና መፍቀሬ-ንጉስ የሆኑ ሆዳም ባላባት ተብዮቹ እንቅስቃሴውን ነጥቀው ውል ያለው የፍቅርና የሰላም ማህተም ሳይደረግ፣ አደራየንም ሳይቀበሉኝ የተወሰኑት ሞት በላቸው፤ አንዳዶቹ ደግሞ እስር፤ ሌሎቹ ደግሞ ስደት።
ይኸው ልጄ እስከ ዛሬ ውል ያለው የአንድነትና የፍቅር በርን የሚከፍት መልካም፣ ቸር እረኛ ጠፍቶ ልጆቼ ተመልሰው ሁለት (ብዙ) ክፋይ ሆኑ። እኔም አንድ ሰው ሳልሆን፣ አደራየንም ለማን እንደምሰጠው ግራ እንደገባኝ፣ ከልጆቼም አንዱ አባቴ እነሆኝ እኔ አለሁ ሳይለኝ መቃብር መውረዴ ነው።
እናም አንተ ልጄ፣ ፍቅር የሚያቃጥልህ፣ የፍቅር ድርሰትን፣ የፍቅር ዜማን ድምፅ የምታወጣ፣ አንተ ሰብሳቢ ምልክት (Uniting Figure)፣ ከወዴት አለህ? ከአፋር በረሃዎች ነው የተሰወርኸውን? እዚያ አለህ ቢሉኝ እኮ እመጣ ነበር ልጄ - በረሃው ሳይገድበኝ፣ ሽበት የጨፈረብኝ ሽማግሌ መሆኔን ማሰብም አልፈልግም ነበር፤ ወዳንተ ስመጣ ወድቄ አሞራ ይብላኝ እንጅ። ብቻ ልጄ አንተ ባትመጣ እንኳ ያለህበትን ብቻ ንገረኝ እኔው እመጣለሁ። ከሞያሌ ጫፍ ነውን? ከኦጋዴን በረሃ ነውን ወይስ ከመተማ ድንበር ባሉት ደኖች? የት ነው ያለኸው ልጄ፣ የት ነው ያለኸው? ከጋምቤላ ደኖች መካከል ነውን ወይስ በከፋ ደኖች? በተከዜ በረሃ ነውን ወይስ በሃማሴን ተራሮች? የት ነው ያለኸው ልጄ? እባክህ ንገረኝ ልጄ፣ ባለህበት ልምጣ ወይ አንተ ና፤ የአንተንና የመጪው ትውልድን የህልውና አደራ ተሸኽሜ እጠብቅሃለሁ።
ብዙ ጅቦች የያዝኩትን አደራ ሊበሉ፤ ብዙ ቀበሮዎች የያዝኩትን የሀገር ህልውና ወይን ሊያበላሹ ከበውኛል። ልጄ እኔ ደግሞ ቀበሮዎቹን የማባርርበት ፍጥነቴ፣ ጅቦቹን የምከላከልበት ጥንካሬየ ደከመ፤ አይኖቼም ፈዘዙ፤ ጆሮዬ የክፉ መናፍስትን ድምጽ ለመለየት ጃጀ። ልጄ ናልኝ እባክህ፤ መቃብሬ ጉድጓድ አፋፍ ላይ ነኝ። ና እባክህ በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ያልጠቀስኩልህ ብዙ ምስጢራትን በእጄ ይዤ እጠብቅሃለሁ።
ጠላትም ከቦኛል፤ ምስጢራቱን ከጄ ነጥቆ ለመበተን፤ የልጆቼን የፍቅርና የአንድነት ቁልፎች ሊያማስኑ የጨለማ ጭፍራዎች ከበውኛል፤ ምናልባትም እስካሁንም በእጄ የጠበቃቸው የኔ ጥንካሬ ሳይሆን የወገኖቼ ደምና አጥንት እንዲሁም የ፸፭ ዓመት ልመናዬ ነው፤ ፈጣርዬ ዐይኔ እያየ የጨለማ አበጋዞች ምስጢራቱን ከጄ እንዳይነጥቁብኝ፣ በሲኦል የበርባኖስ ጥልቅ ባህር ወስደው እንዳይቀብሩብኝ ለምኜዋለሁና። ሳልሞት ናና ተረከበኝ ልጄ፤ ከመቃብሬ ቀድመህ ካልመጣህ፣ ከሞትኩ፣ ዓይኔም ካላዬ ጠላት ይውሰዳቸው!? ዓይኔ እያየ ጠላት ከመዘበራቸው ግን ሳልሞት ሲኦል ገባሁ ማለት ነው፤ የሞት ሞት ማለት ይሄ ነው።
እናም ልጄ! ናልኝና ሁለታችንም እናትርፍ። አንተ እራስህንና ልጆችህን አትርፍ፤ እኔ ደግሞ ከቁም ኲነኔ ልዳን፣ ሆዴ።
ትመጣለህ ብዬ ሳይ ኖርሁኝ መምጫህን፣
ለ፸፭ ዓመት ሳዳምጥ ዱካህን፣
እኔንም ላክብኝ ቀድመህ ሞተህ እንደሆን።
እክባሪው አርበኛ አባትህ
No comments:
Post a Comment