የይቅርታ ቃላት ለዚህ ብሎግ ተከታታዮች
ባለፉት ወራት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ባጭሩ በተከታታይ ከክፍል አንድ እስከ ሰባት በዚህ ብሎግ መነበቡ ይታወሳል።
ነገር ግን በኑሮ ወከባዎች ምክንያት ለረጅም ጊዜ በዚህ ብሎግ ምንም ዓይነት ፅሑፍ ሳይሰተናገድ ቆይቷል። ለዚህም የሚበልጥ ዋ ጋ የሚያስገኝ ስራን በዚህ ዓለም ዝባዝንኬ በመለወጤ ባለቤቱን እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን እናንተንም ይቅርታ መጠየቅ መልካም ሆኖ ታየኝ። እናም ልዑል እግዚአብሔር ቸርነቱ የበዛ አምላክ ይቅር እንዳለኝ እናንተም የእርሱ ልጆች ናችሁና የእርሱን በሚመስል ይቅርታ ይቅር እንድትሉኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ።
ባለፈው ክፍል በግራኝ አህመድ ዘመን የደረሰውን ጥፋት እና ያስከተለውን የታሪክ ጠባሳ ተመልክተናል። ዛሬ ደግሞ የአውሮፓ ካቶሊካውያን “መልዕክተኞች” በሀገሪቱ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱትን ጥፋት እና የዘመነ መሳፍንትን ታሪክ በአጭሩ እንቃኛለን።
ከግራኝ አህመድ ውድቀት በኋላ የ”ኢየሱሳውያን መልዕክተኞች” ከፖርቱጋል እና ከስፔን በመምጣት በኢትዮጵያ የሮማ ቤተ ክርቲያን የመንግስት ሐይማኖት እንዲሆን በማቀድ ሐይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ አቋማቸውን ማንፀባረቅ ጀመሩ። በዚህም ባለፈው ክፍል ለመመልከት እንደሞከርነው በዘመነ ሱስኒዮስ ከሦስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ከ፰ ሺህ በላይ ሕዝብ በሰማእትነት ተጨፍጭፈዋል።
ዘመነ ሱስኖዮስ አልፎ የአፄ ፋሲል አመጣጥ ግን እጅግ አስገራሚ እና ልብን ደስ የሚያሰኝ ውሳኔ በአውሮፓውያን “መልዕክተኞች” ላይ አስተላለፈ። እነዚህ የጥፋት “መልዕክተኞች” ከሀገር ወዲየውኑ እንዲወጡ በአፄ ፋሲል በመወሰኑ ከሀገር ሲወጡ አንድ የሮማ ቤተክርስቲያን መነኩስን ሁለት ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ሊሸኙት ተከትለውት ወደ ወደብ ጉዞ ጀመሩ። ነገር ግን ይህ መነኩስ ተንኮል ስላሰበ አመመኝ ብሎ በማመካኘት ሀማሴን አውራጃ ሲደርስ በመተኛቱ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት እንክብካቤ እያደረጉለት አንዱን ሲልከው ሌላው አብሮት እየተቀመጠ ሳለ ለአንዱ መነኩስ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ አስተምህሮ አስተማረው። ይህ የተማረው መነኩስ ሲሄድ ደግሞ ለሌለኛው ኢትዮጵያዊ መነኩስ ሌላ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ አስተምህሮ አስተማረው። እነዚህ ሁለት መነኮሳት ተመልሰው በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ቤተክርስቲያኗን ለሦስት የከፈለ ሐይማኖት መሳይ ትምህርት መሰረት ጣሉ። የአንዱ መነኩሴ ትምህርት የቅባት እምነትን ሲወልድ የሁለተኛው መነኩሴ ደግሞ የፀጋ እምነትን ወልዷል። በስልጣን ሽኩቻ እና በውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ ሀገሪቱ እየተዳከመች ሄዳ የአንድነት ተምሳሌት የሆነው ማዕከላዊ መንግስት ጠፍቶ ዘመነ መሳፍት ሲተካ የቤተክርስቲያን አንድነትም በዚያው ልክ አደጋ ላይ ወደቀ። ከላይ የተጠቀሰው የሮማ መነኩሴ “ተበቀልኩት! ሁለት እሾህ ተከልኩበት!” በማለት የአፄ ፋሲልን ውሳኔ ስላበሳጨው ለሁለት ደቀመዛሙረቱ የተለያየ ትምህርት አስተምሯቸው አውሮፓ ገባ።
በዚህ በዘመነ መሳፍንት እነዚህ የቅባት እና የፀጋ ትምህርቶች በአንድ አንድ አካባቢዎች ከመሳፍንትም ድጋፍ በማግኘታቸው እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን የተዋህዶ ጠበቃዎች ለእስራትና ለእንግልት የተዳረጉበት ሁኔታ ነበር። በተላያዩ አደባባዮች በሦስቱ ጎራዎች የሐይማኖት ክርክር ያደረጉበት እና ኢፍትሐዊ ብያኔ በአንዳንድ መሳፍንት ይሰጥ ስለነበር የቤተክርስቲያን አንድነት እና ለዘመናት የነበራት በኑፋቄ ያለመበረዝ ታሪክ አደጋ አጋጠመው።
የቤተክርስቲያን የመከራ ዘመናት ከግራኝ አህመድ በኋላ ተከታታይ በመሆኑ እና ከሦስት መቶ ክ/ዘመናት ባነሰ ጊዜ ሦስት ዋና ዋና የሰማእታት ዘመናት በማሳለፏ የደረሰባት መዳከም የሐይማኖታዊ ባህል ለውጡ ቋሚ ጠባሳ እንዲሆን አድርጓል። የግራኝ የእልቂት እና የመከራ ዘመናት፤ የሱስንዮስ የሐይማኖት ለውጥ ዘመቻ እና እልቂት ዘመናት፤ የዘመነ መሳፍንት ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ ተንሰራፍቶ መቆየት እና የቤተ ክረስቲያን መዳከም ተመልክቶ ለትንሳኤዋ ተግቶ የሚሰራ ባለመኖሩ እና በግራኝ አህመድ ዘመን የተጀመረው ሕዝቡ የባህል ለውጥ እንዲያደርግ የመገደድ ሁናቴ ሊሸከምበት የሚችልበት የሥነ-ልቦና ጥንካሬ በማጣቱ ለውጡ ሳይቀለበስ ለመቅረቱ ምክንያት ሆኗል። ከእነዚህ የሐይማኖታዊ ባህል ለውጦች መካከል ለመመልከት ያህል:-
፩. የተክሊልና ክርስቲያናዊ ቤተሰብ መቅረት:- ከግራኝ አህመድ መምጣት በፊት ሕዝበ ክርስቲያኑ ልጆቹን ትዳር የሚያሲዘው ሕገ እግዚአብሔር በሚፈቅደው በቤተክርስቲያን ሥርዓት እና ቀኖና ነበር። ነገር ግን ከአስራስድስተኛው መ/ክ/ዘመን ከግራኝ አህመድ ዘመን ወዲህ የአሕዛብ ልማድ ወደ ሕዝበ ክርስቲያኑ በመግባቱ የልጆቻቸው የጋብቻ ሥርዓት ተለውጦ አሕዛባዊ ልማዶች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል። አሁን በመላው ሃገሪቱ የሚገኘው የገጠሩ ሕዝበ ክርስቲያን ምስጢረ ተክሊል ለዲያቆናት እና ለቀሳውስት ብቻ የተሰጠ እንደሆነ እስከማመን የደረሰ ነው። በከተማ የአውሮፓውያንን አሕዛባዊ ልማድ ሥርዋፅ ያስገቡ የሥርዓተ ተክሊል ክንዋኔዎች የሚታዩ ቢሆንም እነዚህም በቅርቡ በከተሞች በሚሰጠው የስብከተ ወንጌል ፍሬዎች እንጅ የቆዬ ልማዶች እንዳልሆነ ይህ ብርቅዬው ሥርዓታችን ለዘመናት ተዘንግቶ ለዲያቆናት እና ለቀሳዉስት ብቻ እየተሰጠ እንዲቆይ ሆኗል። በዚህ እና ሌሎች ተያያዥ በሆኑ ክርስቲያናዊ የህይወት መስመሮች የገጠሩ ሕዝበ ክርስቲያንም ከሚዘረፈው እየተቆነጠረ እንዲደርሰው የሚመለከታቸው የቤተክርስቲያኒቱ አመራሮች ሊያስቡበት ይገባል። የገጠሩ ሕዝበክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ክፍያ እየተባለ እውነትን ተከትሎ የቤተክርስቲያንን ክፍያ በአግባቡ የሚከፍል ሆኖ ሳለ ለሕዝቡ ግን አንዳችም ትኩረት ሳይሰጠው የመናፍቃን ጉዳይ አስፈፃሚ የሆኑ “የዕርዳታ” ድርጅቶች ሰለባ እየሆነ ይገኛል።
፪. የሕዝቡ የመለያ ስም የቦታ ስም እና የተለያዩ ነገሮች ስያሜ ክርስቲያናዊ ሕይወትን የማያሳይ አሕዛባዊ ልማድ የሚንፀባረቅበት መሆኑ
፫. የሕዝቡ የአኗኗር ዘይቤ ክርስቲያናዊ ፈር መልቀቅ:- ለምሳሌ አስራት በኩራት አወጣጥ፤ ክርስቲያናዊ ህይወት እና መንፈሳዊነት መቀነስ
፬. የባዕድ አምልኮ መበራከት:- ሕዝቡ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ በእርሱም ከመታመን ገለል በማለቱ የተላዩ ዓይነት የባዕድ አምልኮ ሥርዓቶች በሕዝቡ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ እየተለመዱ መምጣት
እና ሌሎቹም አሉታዊ ገፅታዎች ይገኙበታል።
ዘመነ መሳፍንት አልፎ አፄ ቴወድሮስ መንበረ ስልጣን ሲረከቡ …
… ይቀጥላል…