በባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ የዚህን ፅሑፍ መጀመሪያ ክፍል በዚህ መጦመሪያ ገፅ መነበቡ ይታወሳል። አሁን ካለፈው የሚቀጥል ሰው በምድር ሲኖር ሊኖሩት የሚመኛቸው እሴቶች በሚመለከት እንመለከታለን። የመጀመሪያውን ክፍል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!
ባለፈው ክፍል ለማየት እንደሞከርነው ሰው በምድራዊ ህይወቱ ጤናማ ህይወት፣ ደስታ፣ ፍቅር፣ ምቾት እንዲኖረው ይመኛል። የእነዚህ እሴቶች መገኛ ደግሞ ምን እንደሆነ በጥቂቱ ለመመልከት ሞክረናል። የሰው ልጅ ባህርይ ከእንስሳት ጋር የሚጋራቸው አራት ባህሪያተ ሥጋ እና ከእገዚአብሔር ጋር የሚያመሳስሉት ሦስት ባህሪያተ ነፍስ አሉት። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት እሴቶች ደግሞ ሰው በእንስሳዊ ባህሪው ሊያጣጥማቸው በሚችልበት ሁኔታ ብቻ ህይወቱን ከተረጎመው የሚያገኘው ደስታ እና ምቾት እንስሳት ጥሩ ምግብ በልተው በተደሰቱበት ጊዜ የሚያሳዩትን ፈንጠዚያ የሚመስል ይሆናል። እነዚህ እንስሳት ሆዳቸው በጎደለ ጊዜ ማጉረምረማቸው አይቀርም። ስሜታቸውም ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ነው። እናም ሰው ቁሳዊ በሆኑ ሀብቶቹ ለምሳሌ በገንዘብ በምግብ በልብስ እና በመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ የሚያገኘው ደስታ ጊዜያዊ በመሆኑ ወዲያው ይጠፋል።
በአለም ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር አምላኩ እፀ-በለስን በልቶ ከተለየበት ጊዜ አንስቶ ለስጋዊ ባህርይው የሚገዛ እና እውነተኛ ሰላምን በማጣቱ ከላይ የተጠቀሱት እሴቶችን ለዘለቄታው ለራሱ ማድረግ የተሳነው ሆኗል። ነገር ግን ብሩህ ተስፋ በክፉ ጊዜ ያለን መከራ የስቃይ ስሜት እንዲቀዘቅዝ ያደርጋልና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማሪያም ተወልዶ በበደላችን ምክንያት የተረገመችውን ምድርን በኪደተ-እግሩ ቀድሶ ወንጌልን ለሕዝብ እና ለአሕዛብ አስተምሮ በጥምቀቱ በዮርዳኖስ በምድር የተቀበረውን የእዳ ደብዳቤያችንን ደምስሶ በቀናተኛ አሁዶች እጅ ተይዞ ተገርፎ እና መከራ መስቀልን ተቀብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የእዳ ደብዳቤያችንን እና በደላችንን ሁሉ ደምስሶ እንደሚያድነን ለአዳም በሰጠው ተስፋ የሰው ልጅ ህይወት የደስታ ምንጮች የመዳን ተስፋ ሆነ።
በዚህ ብቻ አላበቃም ርህርሄው የበዛ አምላክ። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ብንጠብቅ በምድራዊ ህይወታችንም በባህሪያዊ ነፍሳችን የምንገነዘበው በህይወት ዘመናችን ሁሉ የሚያስደስተን የደስታ ምንጮችንም ከፈተልን። ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች አድልተን ለእውነተኛ ደኛ ለሆነው አእምሮአችን የሚመች ሥራን በመሥራት ዘለቄታ ያለው ደስታ እና ምቾት ማግኘት እንደሚቻል ከተሰጠን ትእዛዛት እና ትእዛዛቱን በመጠበቃችን የምናገኘውን ሰማያዊ ዋጋ ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ዋጋም ተነግሮናል።
ነገር ግን ከዘመነ አዳም ጀምሮ የተወሰኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅ መጀመሪያ በምድራዊ ህይወታቸው በኋላም በሰማያዊ ህይወታቸው የብዙ እሴቶች ባለቤት ሲሆኑ ሌሎቹ ግን እግዚአብሔርን በማሳዘን ትእዛዛቱንም በማፍረስ ቆየት ብለውም እርሱን በሌላ ባዕድ አምልኮ በመለወጥ ስላመነዘሩ የደስታ እና የሌሎቹ የህይወት እሴቶች ምንጮች ደረቁባቸው። አንዳንዶቹ በመቅሰፍት ሲያልቁ ሌሎቹ ደግሞ በምድር ላይ ተቅበዝባዥ ሆነው ህይወታቸውን ደስታን በማጣት ተጎሳቁለዋል።
ይህ ሁኔታ እየቀጠለ ሄዶ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም የገባውን ቃል ለመፈፀም ወደ ዚህ ምደር በመጣ ጊዜ ዓለም የደስታ ምንጭ ምን እንደሆነ ግራ በተጋባ እና ደስታን ለማግኘት የደስታ መገኛ መንገዶች ተቃራኒ ሥራዎችን የሚሰራበት ጊዜ ነበር። እንኳን እግዚአብሔርን የማያውቁት አሕዛብ ይቅርና የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚባሉት እስራኤል እንኳ ትክክለኛ የህይወት መስመርን ስተው የመሲህን አመጣጥ ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከመውጣታቸው ጋር አያይዘው በተሳሳተ መንገድ ተስፋ አድርገው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ቤተእስራኤላውያን በሰው ፊት ብቻ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁ ነገር ግን በስውር ሐጢያትን የሚፈፅሙ አስነዋሪ ስራዎችን የሚያደርጉ የተተበተቡ ትእዛዛትን በሌላው ላይ የሚጭኑ እነርሱ ግን በጣታቸው እንኳ ሊነኩት የማይፈልጉ በእግዚአብሔር ላይ አመፀኞች ነበሩ። ከዚህ እንደምንረዳው በዚህ ወቅት ዓለም የደስታ እና የፍቅር የምቾት እና የጤናማ ህይወት መስመሩን ስቶ አሰቃቂ የመገዳደል ወንጀል በበዛበት እና የነፍስ እረፍቷ የሚሆን ሥራ የተመናመነበት ጊዜ እንደነበር ነው። በሮማ ግዛት እና በሌሎች የጣዖት አምልኮ በነበረባቸው የአሕዛብ ነገስታት አገርም ደስታ የሚገኘው የተለያዩ ትርኢቶችን በመመልከት እንደሆነ ይገመት ነበር። በዚህም ምክንያት በተለያየ ምክንያት ወንጀለኛ ናቸው ተብለው የተያዙ እስረኞች በሞት እንዲቀጡ በመወሰን ከአናብስት እና ከአናምርት ጋር በአደባባይ በማታገል ነገስታቱ እና ሹማምንቱ እንዲሁም መኳንንቱ ይህን በመሰለው ትርኢት ደስታን ለማገኘት እና ለመዝናናት ይሞክሩ የነበረበት ዘመን ነዉ። ይህ አሰቃቂ የሆነ የሰው ልጆች ሰቅጣጭ ጩኸት ትርኢቱን ለመመልከት የሚመጣውን ሕዝብ አእምሮ ውስጥ የህልውና ጥያቄ የሚያስነሳ እና ህይወታቸው ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ዋስትና የሌለበት ዘመን ሆኖ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በገዢው በኩልም ይህ ለአእምሮ የማይመች ሥራቸው የህልም ቅዠት እና ሰቆቃ እንጅ ደስታ እና ጤናማ ስሜትን ሊተርፍላቸው አልቻለም።
እንግዲህ አምላካችን ክርስቶስ የተወለደው በዚህ በተዘበራረቀ ዓለም ትክክለኛ የህይወት መስመር ውሉ የጠፋበት ዓለም እና ጊዜ ነው። የህይወት ጣዕም ጠፍቶበት ዓለም ወደ አልጫነት ተቀይሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ከቅድስት ድንግል ማሪያም የተወለደው አካላዊ ቃል ይህንን የዓለም አልጫነት አስወግዶ የሚጣፍጥ ጨው ሆኖ ወደ ጣፋጭነት ቀየረው። ተስፋ የቆረጡ እና “ህይወት ምንድነው?” እስከ ማለት የደረሱ ድውያንን በተአምራቱ ርሁባነ ነፍሳትን በትምህርተ ወንጌሉ በማስተማር ዳግም ሰው የሞት ተሸናፊ አለመሆኑን ከሞት በኋላ ህይወት ያለ መሆኑን እና በትንሳኤ ዘጉባኤ ሞትን ድል ነስተን እንደምንነሳ በማስተማር ሰውን ዳግመኛ ወደ ፀጋ መንፈስ ቅዱስ ልጅነት መለሰው። በኦሪት የተሰጠች ትእዛዝን በማፅናት የፍቅር ትእዛዛትን ለሰው ልጆች የእውነተኛ እና ዘላለማዊ የህይወት እሴቶች መገኛ አድርጐ ከፊት ይልቅ በሐዲስ አፅንቶ ሰጠን። ሰው ሁለት ዓይነት ፍቅር ሲኖረው የመጀመሪያው ሰው ለፈጣሪው ለእግዚአብሔር የሚኖረው ከራሱ የበለጠ ፍቅር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰው እርሱን ለመሰለ ሌላ ሰው የሚኖረው ፍቅር ከራሱ ፍቅር ጋር የተካከለ ነው። ነገር ግን ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን ነገር እግዚአብሔር አነዚህን ሁለቱን የፍቅር ትእዛዛት ሲሰጠን የመጀመሪያው ፍቅር በሁለተኛው እንዲገለጥ ፈቃዱ ስለሆነ ሰው ሁሉ ለተቸገረ እና እርዳታ ለሚያስፈልገው ሁሉ የሚያናደርገው በጐ ሥራ ሁሉ ለእርሱ እንደተደረገ ሆኖ እንደሚቆጠር በስድስቱ ቃላተ ወንጌል ገልጦልናል።
በዚህም ነፍስንም ስጋንም የፈጠረ እግዚአብሔር የህይወት እሴቶችን ከትእዛዛቱ ጋር የተቆራኙ አድርጐ ለራሳችን በምንም ዓይነት መስፈርት እንዳናደላ አእምሮን ያህለ ርቱዕ ዳኛ በላያችን ሾሞ የነፍሳችን ማረፊያ የሚሆን ትእዛዛቱን በመፈፀም ደስታ ፍቅር ጤና እና ምቾትን እንድንላበስ ፈቃዱ ስለሆነ እነዚህን ሥራዎች በመስራት እና ትእዛዛቱን በፍቅር በመፈፀም ዳግመኛ ወደ ህይወት እሴቶች መምጣትን እርሱም ከእርሱም ቀጥሎ በእርሱ ትእዛዝ በሐዋሪያት እና በተከታዮቻቸው አማካኝነት አስረዳን። ህይወትንም ተስፋ አስደረገን።
ዓለምም ታሪኳ ተቀየረ፤ ሰው ዳግመኛ ደስታ እና የህይወት እሴቶች በሙላት በሚገኝበት መንገድ መጓዝ ጀመረ። የዓለም ስልጣኔ እና ውጤታማነት ቀያሿ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። የባርነት ህይወትን እና በሰው ነፍስ በመጫወት ደስታ እና ፈንጠዚያ የማይገኝ መሆኑን በማሳየት ለዓለም አልጫነቱን በማስወገድ።
ይህንን ታሪካዊ ዳራ ለማንሳት ያስፈለገበት አሁን ያለንበት ዘመን ሰው የህይወት ስኬትን ከቁሳዊ ትርፎች ጋር በማያያዝ የተሳሳተ አቅጣጫን እየተከተለ ያለበት ዘመን በመሆኑ ነው። ይህ የአሁኑ የዓለም ሁኔታ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ እንደነበረው ሙሉ ለሙሉ የከፋ ባይሆንም በአብዛኛው የዓለም ክፍል ግን ሁኔታው ከዚያ ጊዜ ይልቅ እየከፋ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
…ይቀጥላል…
Sara Adera
ReplyDeleteከዚህ በላይ ፍቅር የለም
እጅህ ይባረክ!!!