Saturday, August 25, 2012

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አስራ ሁለት)


አቡነ ቴወፍሎስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ

ይህ ተከታታይነት ያለው ፅሁፍ እስከ ክፍል አስራ አንድ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ይህንን ፅሁፍ አንባቢው ያለፈውን ክፍል ሳይረሳው በተከታታይ ሳምንታት ከማቀረብ ይልቅ እየተጓተተ እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቷል፡፡ ይህ ባለመሆኑ በእግዚአብሔር ስም ይቅር እንድትሉኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ ያለፉትን ክፍሎች ለመጎብኘት ከፈለጉ የሚከተሉትን ጠቋሚዎች ተጠቀሙ፡፡

 
ባለፈው ክፍል በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን የነበረውን የቤተክርስቲያን ታሪክ ቃኝተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ቤተከርስቲያን ከአብዮታዊ ደርግ መነሳትና ከዚያ በኋላ የነበረውን ሁኔታ እንቃኛለን፡፡
በ1953 ዓ.ም በሁለቱ ወጣት የኢትዮጵያ ለውጥ ናፋቂ ወንድማማቾች በግርማሜ ነዋይና በመንግስቱ ነዋይ መሪነት በእነ ጀነራል ወርቅነህ ገበየሁ አጋዥነት የተከናወነው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከትሎ በሀገሪቱ የለውጥ ፈላጊ ወጣቶች እየተበራከቱ በመሄዳቸውና ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ብዝበዛና ጭቆና ያስመረረው ያረጀ ያፈጀ ፊውዳል ሥርዓት መሸከም የሰለቸው የተለያየ የሕብረተሰብ ክፍል በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ገበሬዎች አመፅ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተያይዞም በነዳጅ ዋጋ መጨመር የታክሲ ሾፌሮች፣ የተሻለ የኢኮኖሚ ባለመኖሩ ተማሪው፣ መምህራኑ፣ ጦር ሰራውቱና ሌሎቹም የህብረተሰብ ክፍሎች በመታከላቸው ይህን የለውጥ ነውጥ የሚያስባብር አካል ባለመኖሩ ለጊዜው ውጤታማ ሥራ መስራት ሳይቻል የተወሰነ ጊዜ ቆይቶ መጨረሻ ላይ አዲስ አበባ በሚገኘው በአራተኛ ክፍለ ጦር በእነ ሻለቃ አጥናፉ አስተባባሪነት ለተለያዩ የጦር ሻለቆች በጊዜው የነበረውን ለውጥ ለመወያየት እንዲቻል ከአራተኛ ክፍለጦር መልዕክት በመላኩ የጊዜው ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማሪያም ሐረር የሚገኘውን የሶስተኛ ክፍለ ጦር እየመሩ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ የሌሎቹም ክፍለ ጦር ተወካዮች እንዲሁ፡፡
በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የለውጥ ናፋቂው ሕብረተሰብ ለውጥ አራማጅነት ባለታሰበ ሁኔታ በጦር ሰራዊቱ በመመራት ንጉሱን ካልጋቸው አንሸራቶ ካወረደ በኋላ ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደምብሎ የጀመረው ደርግ በመንግስቱ ኃይለማሪያም መሪነት የአብዮቱ ተግዳሮት ተደርገው የተወሰዱ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ሁለቱን የአንድ እናት ኢትዮጵያ ልጆች በሁለት ጐራ ከፍሎ ደም አፋሰሳቸው፡፡ በዚህ ወቅት ማንኛውም የአብዮታዊ ደርግ ተግዳሮት ናቸው ተብሎ የሚታሰቡ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ሌሎቹም ከመቃብር በታች ለማድረግ በማለም የቤተክርስቲያንን በሮችም አንኳኩቶ ሥራዎቿን ሁሉ በአብዮታዊ ደርግ መርህ ለመቃኘት አሰኘው፡፡ በዚህም የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ አቡነ ቴወፍሎስ በወቅቱ ቤተክርስቲያን የማንንም ጣልቃ ገብነት ሳትሻ ራሷን ችል የራሷን አመራርና አስተዳደራዊ ሥራ መስራት እንዳለባት በመገንዘብ የወቅቱን ደርግን ሳያስፈቅዱ ሊቃነ ጳጳሳትን በመሾማቸው ተይዘው በግዞት ቤት እንዲቆዩ ካደረገ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱን አባቶች ይሙት በቃ በግድ አስወስኖ ሳይሞቱ በላያቸው ላይ ሌላ ፓትርያርክ አስመርጦ የግፍ አገዳደል አስገደላቸው፡፡ ሀገሪቱን በሃምሳ ዘጠኙ የኃይለ ስላሴ ሚኒስትሮችና መኳንንት ላይ ደም ማፍሰስ የጀመረው ደርግ በኋላ በቀይ ሽብርና በየ አጋጣሚው በሚሰዋቸው ሰዎች ደም ሀገሪቱ በደም ታለለች፡፡ በኢህአፓና በደርግ መካከል በተደረገው ሽኩቻ ለሀገሪቱ የለውጥ ሀዋሪያ መሆን የሚችሉ የዩኒቨርሲቲና የከፍተኛ ሁለተኛ ተማሪዎች በያሉበት እየታደኑ የጥይት ራት ሆኑ፡፡ የኢትዮጵያ የሚቀጥሉት 50 ዓመታት የለውጥ አድራጊነት መንሰፈስና የእድገት ጉዞ አከርካሪው ተመትቶ እንዳይነቀሳቀስ ወድቆ ቀረ፡፡ በዚህ ዘመን የለውጥ ሐዋሪያነት የተመናመነ፣ የግፍ አገዛዝን እምቢኝ የሚል የጠፋው የዚያ ዘመን ጠባሳ ሰለባዎችና የእነርሱ ልጆች በመሆናችን ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደርግ በሕብረተሰባዊነት ርዕዮተ-ዓለም በመንተራስ የእብሪቱ መጨረሻ ጫፍ ላይ የደረሰበትን ፈጣሪ የለም፤ የእምነት ድርጅቶች መኖር ለሀገር እድገት አዝጋሚነት ምክንያት ሆኖ በመወሰዱ ወጣቶችና ልሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የእምነት ሥርዓታቸውን እንዲተላለፉ፣ ፆም እንዳይጾሙ፣ ቤተክርስቲያን እንዳይሰባሰቡ፣ ወዘተርፈ በተለያዩ ስልቶች እቅዱን ማስፈፀም በመጀመሩ በቀጥታ የኃይል እርምጃ በመውሰድ፣ የርዕዮተ-ዓለም የማስረፅ ሥራ መስራት፣ የልዩ ልዩ የልማት ማኅበራት አባልነትን ለማግኘት እምነት-የለሽ መሆንን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ፣ የቤተክርስቲያንን ይዞታዎች ሁሉ መንጠቅና ምጣኔ-ሀብታዊ አቅም ማሳጣት፣ በልዩ ልዩ ስብሰባዎች ቤተ እምነቶችን ማንቋሸሽና ማጥላላት ወዘተ ነበሩ፡፡ ይህ ጊዜ በተለይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ደርግ ጦር ሰብቆ፣ ወገብ ታጥቆ የተነሳበትና የባህል አብዮት በወጣቱ ላይ እንዲሰርጽ በተገኘው መንገድ ሁሉ የተጋበት ዘመን ስለነበር የለውጥ ምንጭ የመፃያቱ ጊዜ ባለቤት የነበረው ወጣቱ ከእናት ቤተክርስቲያን ተለይቶ ምልክት የለሽ፣ ስደተኛ ሆነ፤ ስደቱም ተመልሶ ላይመጣ ትቷት የሄደውን እናት ቤተክርስቲያኑን ኢየሩሳሌም ሆይ! ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ …. ላይል ምሎ በሞት የተለዩትን ወዳጅ ያህል ከቤተክርስቲያን ራቀ፡፡
ወጣቱ ትውልድ በዚያ ጊዜ ትንሽ የቀረችው ወኔ እናት ሀገሬ ኢትዮጵያ የሚል ጭላንጭል ብርሃንም በወቅቱ ለሃገር ሳይሆን የአብዮቱ ዘብ የቆሙ የጥፋት አምባሳደሮች ሀገሪቱን በደም እንድታቅላላ በማደረግ ያለተመጣጠነ ኃይል ለጥቂጥ የኩራዝ ብርሃን ላይ የአውሎ ነፋስ በሚያህል ኃይል እፍ ድርግም አደረጉት፡፡ ከዚያ በኋላ ወጣቱ የተነሳበትንና የሚደርስበትን በውል ሳይረዳ በቀላሉ ነፋስ በነፈሰበት የሚነዳ የጥፋት ሱሶች ተጠቂና ተስፋ የቆረጠ ሆነ፡፡ የደርግ ዘመን የሥነ-ልቦናና የሞራል ስብራት የሁለትና የሦስት ትውልድ የማይጠግነው ታላቅ ውድቀት ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ወጣቶች ከጥቂቶቹ በስተቀር የአልኮል መጠጥ ሱሰኞች፣ የሲጋራ ሱስ ባሮች ሆነው የተከታዩን ትውልደ መሪና አቅጣጫ አመላካች ባለመኖሩ ጥዝጣዜው ይኸው እስከዛሬ ዘልቆ እስከ አጥንታችን ህመሙ ይሰማናል፡፡
ደርግ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ በጠላትነት የተነሳባትን ያህል በሌሎች ቤተእምነቶች ላይ ትኩረት ባለማድረጉ በተለይ ለኢትዮጵያ መጤ ቤተ እምነቶች አንፃራዊ ነፃነታቸውን በመጠቀም የቤተክርስቲያንን ልጆች እየነጠቁ የአዳራሾቻቸው ታዳሚዎች በማደረግ አያሌ የጥፋት መላዎችን በማቀድና በመተግበር ከፍተኛ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ በ1940ዎቹ የተጀመረው የምዕራባውያን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጥቁር ፅዮናዊነትን ታስከትላለች በሚል ስጋት በወለደው ቤተክርስቲያኗን ከመቃብር በታች ለማድረግ ጥረት እራሱን እየወለደ በደርግ ዘመንና አሁን ባለንበት ዘመን እንደ ሰደድ እሳት ቤተክርስቲያኗን ከውስጥ እና ከውጭ አየለበለበ ይገኛል፡፡
በደርግ አገዛዝ ዘመን በዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሐይማኖታቸውን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለለፍ ወይም በደርግ ዘመን የነበረውን ሐይማኖት የለሽ ህብረተሰብ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ባለመቀበል በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተለያዩ ቅዱሳን ስም ፅዋ ማኅበራትን መስርተው ቅዱሳንን እየዘከሩ ሲቆዩ በ1977 ዓም በተከሰተው የሀገሪቱ ረሃብ የተጠቃውን የትግራይና የወሎ ሕዝብ በለም አካባቢዎች ለማስፈር በነበረው እንቅስቃሴ በመተከል ዞንና በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ለም ቦታዎች የመንደር ምስረታ ሥራ ይከናዎን ነበር፡፡ በዚህ የመንደር ምሥረታ ሥራ ውስጥ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተለያየ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል እናቶች የቤት ዕቃ ማሟላት ኃላፊነት ተጥሎባቸው ስፌት ሰፍተው  እንዲያስረክቡ ኮታ ተጥሎባቸው ስፌት በእያንዳንዱ እማወራ እጅ ተሰፍቶ ተሰብስቧል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ጎልማሶች ደግሞ በመንደር ምስረታው ቦታ ተወስደው ቤት የመስራት ኃላፊነት ስለ ተጣለባቸው በመተከልና በሌሎችም ቦታዎች እነዚህ ተበታትነው የቅዱሳንን ስም በየዶርማቸው ሲዘክሩ የቆዩ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በህብረት ሀገራዊ ራዕይ እንዲሰንቁ እርስ በእርስ ተነጋግረውም ተመሳሳይ አቋም እንዲያራምዱ ዕድል ፈጠራላቸው፡፡ በዚህ የመንደር ምስረታ ጊዜ የነበረው መስተጋብር ግን ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶ ያልተሰራበት ስለነበረ ወዲያው ሀገራዊ ተቋም እውን እንዲሆን አላስቻለውም፡፡ በየግላቸው ሀገራዊ ራዕይ አንግበው የተለያዩት እነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በተለያዩ ገዳማት በመሄድ ከገዳማዊ አባቶች ትምህርት፣ ምክርና ቡራኬ እየተቀበሉ የክረምት ጊዜያቸውን ማሳለፍ በመጀመራቸው ለሚቀጥሉት ተከታይ የየተሞቻው ተማሪዎች ራዕያቸውን በማካፈል ከዓመት ዓመት ተሸጋገረ፡፡ በዚህ ሁኔታ የክረምት እረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ተማሪዎች መካከል አንድ አንዶቹ በዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እየሄዱ በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ከነበሩት ከአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ትምህርትና ቡራኬ፣ እንዲሁም ምክር በማግኘት እነዚያ ተማሪዎች በራዕያቸው ትልቅና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ አስቻሏቸው፡፡
የደርግ መንግስት በሶቪየት ህብረት መፈረካከስ ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ትግልና በውስጥም በኃይል የታሰረው ስልጣን እየላላና አቁዋሙም አየዋዠቀ እን ሻለቃ አጥናፉ አባተ ድብልቅ የኢኮኖሚ ስርዓት ነው የሚበጀን በማለታቸው ብቻ ለሀገሪቱና ለአብዮቱ መሳካት ያደረጉትን ውለታ ሁሉ ከገደል ከቶ እንዲረሸኑ መደረጋቸውን ረስቶ በ1982 ዓ.ም ድብልቅ ኢኮኖሚና ስም ለበስ ዲሞክራሲ በማዋቀር ደርግ ከስሞ ቢሔራዊ ሸንጎ እንዲመሰረት መደረጉ የደርግን የውድቀት ዋዜማ እንደደረሰ አመላካች ነበሩ፡፡ ደርግ ከስሞ የመንግስቱ ኃይለማሪያም ብሔራዊ ሸንጎ ሲመሰረት የደርግ ሥርዓት ከስም ለውጥ በስተቀር ያከናወናቸው ለሀገሪቱ የሚበጁ ለውጥ ባለመኖሩ ከ1982 ጀምሮ ደርግ እንደ ሶቪየት ሕብረት ለመውደቅ እየተንገዳገደ ነበር ማለት ይቻላል፡፡  በዚህ ጊዜ ደርግ በ1983 ዓ.ም የመጨረሻ አማራጭ የትግል ስልት በመንደፍ ከነጻ አውጭ ግንባሮች ጋር የሞት ሽረት ጦርነት ለማከናዎን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በብላቴ የጦር ማሰልጠኛ ተቋም ሰብስቦ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት ሲጀምር በ1977 ዓ.ም በመንደር ምስረታ የተገኘው ዓይነት ዕድል ዳግም በመገኘቱ በዚህ ወቅት ከእነ አባ ጎርጎሪዎስ ካልዕ የተገኘው መንፈሳውና ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬና እውቀት ታክሎበት በብዙ ቅዱሳን ስም ሲዘከር የቆዩት የየግቢው የፅዋ ማኅበራት አንድ ሀገር አቀፍ ማኅበርን አስገኘ፡፡ የእነዚህ ተማሪዎች ሕብረት ቀጥሎ ከደርግ ውድቀት በኋላ በ1984 ዓ.ም በአቡነ ገብርኤል ሰያሚነት ሁላችሁም የምትዘክሩት ቅዱሳንን ነውና ማኅበረ ቅዱሳን ተብሎ እንዲሰየም በማለት ባቀረቡት ሐሳብ መሰረት ግንቦት 1 ቀን 1984 ዓ.ም የቤተክርስቲያን ለራዕዩ ማኅበር ተመሰረተ፡፡
ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ነቢያት፣ ሐዋሪያት፣ ደናግል መነኮሳት የሚዘከሩበት በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ተብሎ በመሰየም መጀመሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እናት ቤተክርስቲያንን እንዲያውቁ ትምህርት በማስተማር፣ የተለያዩ የሥነ-ልቦና የምክር አግልግሎት በማከናዎን፣ እርስ በእርስ እንዲማማሩና እንዲረዳዱ በማድረግ ወጣቱ ትውልድ ደርግ ዘመ እግአብሔርንና እናት ቤተክርስቲያንን ባለማወቅ የተጎዳውን ጉዳት በዚህ በእኛ ዘመን እንዳይደገም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ደርግም በቤተክርስቲያንና በሀገሪቱ ፈርጀ-ብዙ ችግሮችን ለ17 ዓመታት ሲያደርስ ከቆየ በኋላ የተደገፈበት ሥርዓት በሩሲያ ወድቆ ሲንከታከት እርሱም ከሀገሪቱ ተወገደ፡፡ የ17 ዓመታት መሪው መንግስቱ ኃይለማሪያምም ወደ ወዳጅ ሀገሩ ወደ ዚምባብዌ በረረ፡፡ የደርግ ሥርዓትም በዚሁ አከተመ፡፡ ነገር ግን በደርግ ዘመን አንፃራዊ በሆነ እይታ ሲታይ ያደረሰው ጥፋት ሚዛን የሚደፋ በመሆኑና በዘመኑም የነበረው ከሦስት አቅጣጫ የነበረው ጦርነት ፋታ ስለነሳው ሙሉ ኃይልና አቅሙን በሙሉ ለሀገር እድገት ማዋል ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህም ሆኖ በመሰረተ ትምህርት በሀገሪቱ ድንቁርናን ለማጥፋት የወሰደው እንምጃና የልማት ውጥኖቹ በታሪክ ማሕደር ውስጥ ከበጎ ጎኖቹ በአወንታዊነት የሚታሰብባቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ 

ይቀጥላል …

Tuesday, August 21, 2012

ለሕዝብና ለቤተክርስቲያን ሰላምንና መልካም መሪን ከእግዚአብሔር ለምኑ



ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ


ሰሞኑን ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ሁለቱን ዋና ዋና የሀገሪቱን መሪዎች አጥተናል፡፡ እጅግ አስጨናቂ ጊዜ ነው፡፤ በጣምም አስደንጋጭ፡፡ ለሥጋ ለተለዩን መሪዎቻችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያና ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያሳርፍልን፡፡ በምንም በምን መስፈርት የሀገር መሪ እንኳን ወንዝ ዘመንን ያሻግራል፡፡ የኛ መሪዎች ከሁለት አስርት ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ሀገርንና ሕዝብን በመምራት ሰው በመሆናቸው ታሪካዊ ስህተት ሊፀዱ ባይችሉም ማድረግ የሚችሉትን አድርገው ሀገሪቱን አንፃራዊ የሰላም አየር ለመተንፈስ አብቅተዋታል፡፡ ይህ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ታሪክም በዚህ ተግባራቸው ሲያስታውሳቸው ይኖራል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር መለስ በልማትም ጎን ከአፄ ሚኒልክ ወዲህ አንጻራዊ በሆነ ፈጣን የልማት መንገድ እንድትጓዝ ጥሩ የአመራር ሥራ ተጫዉተዋል፡፡ አሁን ዓላምችን ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሂስ መስጠት ስላልሆነ ሂስ ተቀባይ አካል ሰምቶ የሚያስተካክለው በመሆኑ ደካ ጎናቸውን ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ሁናቴ አንፃር እናም ባለድርሻ አካላትም ሊያጤኑት የሚገቡ ነጥቦችን መጠቆም ለነገው መንገዳችን መልካም የብርሃን ጭላንጭል ሊሆኑን ይችላሉ በማለት ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦች መንግስትን የቤተክህነት ባለድርሻ አካላትና ሁላችንንም የሚመለከቱ ሲሆን ከማንኛዉም ተቋም ወይም ግለሰብ ፍላጎትና የግብ አቅጣጫ የተመሳከሩ መሆናቸውን ለማጥናት ጊዜ አተወሰደም፡፡ ብቻ በእኔ አመለካከት መልካም መስለው የታዩኝን እነሆ ብያለሁ፡-

፩. የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በሚመለከት

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከአባ ጳውሎስ በኋላ መሪዋ ማን መሆን አለበት? በሚል ርዕስ በቤተክርስቲያን የፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ለመጠቆም ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ነጥቦች በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስና የቤተክርስቲያን ባለድርሻ አካላት ከግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገቧቸው የሚያስፈልጉ ጉዳዮች፡-

  • 1.      ቤተክርስቲያን እንኳን በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርና ርቱዕ ሐሳብ ባለው ሰው አንገት በሚያስደፋ ሁኔታ በአንድ ወቅት በአንድ አንድ አላዋቂ ሰወች ተፅዕኖ አማካኝነት በሐይማኖት ሕፀጽ ሳይሆን በአስተዳደራዊና በፖለቲካዊ ስህተት ለሁለት ተከፍላ መቅረቷ እጅግ አንጀት የሚበላ ጉዳይ ነው፡፡ እናም የአብዛኛው ኦርቶዶክሳዊ የደስታው ፍፃሜ በዚህ ዘመን እነዚህ ለሁለት የተከፈሉ ሲኖዶሶች ተመልሰው አንድ መሆን ነው፡፡ እናም ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩነቶችን ማጥበብ የሚችሉ አቋሞችን በውይይት በማፅደቅ የሰላም ሂደቱ እንዲቀጥልና በአጭር ጊዜ እንዲፈታ የቤተክርስቲያንንም ታሪክና አንድነት ማደስ ቢችል ምንኛ መልካም ነው? 
  • 2.     መከሩ ብዙ ነው፤ ብዙ የአፍሪካ ሐገራት የኢትዮጵያን እዉነተኛ ሐይማኖት እንድናስተምራቸው እኛን እየጠበቁን እያጣናቸው ነው፤ በአንድ ወቅት ከ1933 እስከ 1980ዎቹ ባሉት ዘመናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለምዕራቡ ዓለም ተግዳሮቶች ተብለው ከተዘረዘሩ አራት ዐብይ ነገሮች አንዷ ነበረች፡፡ ለምን ቢባል አሜሪካና አጋሮቿ በስለላ ድርጅቶቻቸው አማካኝነት የደረሱበት መረጃ እንደሚያሳቸው አፍሪካውያንና አጠቃላይ ጥቁሩ ዓለምን በአንድ ጥላ (እምነት) ስር በማሰባሰብ የጥቁር ፅዮናዊነትን ልታስከትልብን አፍሪካም ወደ ሐያልት ሰልፍ ልመጣብን ትችላለች ብለዉ ይሰጉ ነበር፡፡ አሁን ይህን ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ የተለያዩ ጎሳዎች የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መቀላቀል ይፈልጉ ነበር፤ አሁንም ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን አሁን ያሏት ጳጳሳትም ሆነ መምህራነ ወንጌል እንኳን ለውጭ ሊተርፉ ለሀገርም ከአዲስ አበባ የዘለለ ስራ መስራት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ከሰራን በስደት ያሉ ጳጳሳትና በየምክንያቱ የተሰደዱ የቤተክርስቲያን ሰወች በአንድ ቤተክርስቲያን ጥላ ስር ተሰባስበው እውነትን በማጣት ለተጎዳው ዓለም በተለይም እውነትን ለሚናፍቁት አፍሪካውያን ወንጌልን ለመስበክ መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡
  • 3.     በስደት ለሚኖሩት የሲኖዶስ አባላትና በእነርሱ ለሚመራው የቤተክርስቲያኗ አባላት ደግሞ አንድ ፅንፈኛ አቋም ላይ በመሆን የመከራከሪያና የመደራደሪያ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመደርደር የሰላም ድርድሩ እውነተኛ ፍሬ ለማፍራት የሚችልበትን መንገድ ተወያይቶ በመወሰን የቤተክርስቲያን ታሪክና የትውልዱን ሥነ-ልቦና ሊያቃና የሚችል ፍሬ ሐይማኖት ማፍራት እንድትችሉ እራሳችሁን ብታዘጋጁ መልካም ነው፡፡ የኛ የልጆቻችሁ ዳራችን የተሰነጠቀ በመሆኑ መድረሻችንን በቅጡ ማዎቅ ተስኖናልና ይህን የተሰነጠቀ ዳራችንን የምትደፍኑት እናንተው ናችሁ፤ ተሸንፋችሁ አሸንፉልን እንላለን-ልጆቻችሁ፡፡
  • 4.     ሁሉም የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ምእመናን በሙሉ በፍፁም ዋይታን ልቅሶ እግዚአብሔር ቤቱን መልሶ አንድ ያደርግልን ዘንድ ፀልዩ፤ ለእርቅና ለሽምግልና መልካም ሐሳቦችን በመለገስ ለሰላም አስተዋፅኦ አበርክቱ፤ በቸልታ ዝም ብንል የዚህ ትውልድ አባላት በሙሉ ታሪክ መወቀሳችን አይቀርምና፡፡
  • 5.     ጉዳዩ የሚመለከታችሁ የመንግስት ባለስልጣናት በውጭ በስደት ያለው ሲኖዶስ አባላት ፖለቲካ ስም እየለጠፉ እንዲርቁ ባታደርጉና ለቤተክርስቲያን ሰላም ድጋፍ ብታደርጉ መልካም ነው፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት መስቀል እንጅ ጠመንጃ የላቸውም፡፡ ወዳጅህ ያልሆነውን ፍፁም ወዳጅህና ባለሟል ብታደርገው ከሞት ይጋርድሃል፤ ስላንተም ይሞታል፤ በድየው ሳለ ይህንን አድርጎልኛልና ብሎ ነፍሱን ስላንተ ይሰጣል፡፡ እናም በፍቅር ማሸነፍ ከምንም በላይ አሸናፊነት ነውና በፍቅር የስደት አባቶቻችንን መልሰን ብንጠራቸው መልካም ነው፡፡  


፪. መንግስትንና የኢትዮጵያ ሕዝብን በሚመለከት

የጠቅላይ ሚንስትር መለስ የሃያ አንድ ዓመታት ብዙ ስኬት የተመዘገበበት ሲሆን አንድ አንድ ለኢትዮጵያ የማይሆን ርዕዮተ-ዓለምም የተተገበረበት በመሆኑ ጥቂት ግን ደግሞ ቸል ለማለት የማይቻሉ አንድ አንድ ጥቁር ነጥቦች አሉበት፡፡ አሁን እነዚህ ጥቁር ነጥቦች የትኞቹ ናቸው ብለን አንወያይም፤ ነግር ግን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁናቴ አንፃር ሕዝቡና ባለድርሻ አካላት ከግንዛቤ ውስጥ ቢያስገቧቸው መልካም ነው ያልሁትን እንደሚከተለው እዘረዝራለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ የኔ የግንዛቤ አድማስ የደረሰበትን የሚያንፀባርቅ ነው እንጅ ሌላ ምንም ማለት ዓይደለም፡፡
  • 1.      ከላይ ለቤተክርስቲያን የሰጠሁትን የሰላም ጉዳይ እዚህም እደግመዋለሁ፤ መንግስት በደርግ ዘመን ብዙ ጥፋት ያጠፉ ግለሰቦችን መጀመሪያ የጥቃት ሰለባ የሆኑትን ቤተሰቦች አነጋግሮና እነርሱ ይቅር እንዲሉ አድርጎ የደርግ ባለስልጣናትን ይቅር ያለበት መንገድ ታሪክ የማይረሳው ትልቅ የሞራል ልዕልናና የሥነ-ልቦና ብስለት ያለበት አኩሪ ተግባር ነው፤ ይቅር መባባልን ይቅር ከማያሰኝ ሁኔታ ላይ ይቅርታ በማድረግ በሀገሪቱ የመቶ ዓመታት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ በመሆን አስተማረን፡፡ መሪነት ለሰላም ማለት ይህ ነው፡፡ አሁንም ባለው የፖለቲካ ስርዓትና በሌላም ምክንያት አኩርፈው ከሀገር የወጡ ብዙ ዜጎቻችን ሀገራቸውን ለማየት አንድ የሀገሪቱ የታሪክ ምዕራፍ ተካፋይ ለመሆን የኔ የሚሏት መለያቸው ኢትዮጵያን ማየት፣ ከአየሯም ተንፍሰው መጥገብ፣ ከውሃዋ ጠጥቶ ለመሪካት ዋኝቶ ለመድከም፣ ከሰለጠነው ዓለም የሸመቱትን እውቀት፣ ክሂሎትና ሙያ እንዲሁም ያላቸውን ሀብትና ጉልበት ለሀገር ለማካፈል እጅግ ይናፍቃሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ቅድመ-ሁኔታዎች ያልበዙበት ብሔራዊ የእርቅ ማዕድ አዘጋጅቶ በዚያ ዕድል ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ የሀገር ፍቅር የሚያንቆራጥጣቸው የፈረንጅ ሀገር ኑሮና ሀብት ከዱር ገብቶ ዘፈን የሆነባቸው ሰዎች ቢጠሩበት መልካም መስሎ ታዬኝ፡፡
  • 2.     በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቅድመ-ሁኔታ ሳታበዙ የሰው ጥማት ያለባትን ሀገር በአማካሪነት፣ በመሃንዲስነት፣ በሀኪምነት፣ በድርሰት፣ በትያትር ጥበባት፣ በእርሻ፣ በማዕድን ቁፋሮ፣ በጠፈር ምርምር፣ በፖለቲካ ወዘተርፈ ያገኛችሁትን እዉቀት፣ ክሂሎት፣ ልምድና ሙያ እንዲሁም ሀብትና ጉልበት ከዚህ ከእናት ሀገራችሁ ብታፈሱት አይሻልምን? ባዳ ከላሰው ዘመድ የነከሰው እንደሚባለው የውጭ ሰዎች በሙገሳ ከሚጠሩዋችሁ የኛ ሰው ቢሰድባችሁ አይሻልም ትላላችሁን? በሀገር መኖር የመንፈስ ነፃነት ይሰጣል!!!
  • 3.     ኢትዮጵያውያን መሪያችንን አጥተናል፤ መልካም ጅምሮች ሣይጠናቀቁ፣ የታሪክ ስህተቶች ሳይታረሙ፣ ወዘተ፤ ከሁሉም ነገር አሳሳቢው የሀገር ብሔራዊነት ሳይሆን የጐሳ ብሔርተኝነት የተሻለ ጥንካሬ እንዳላቸው ይሰማኛል- እርግጠኛ ባልሆንም፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ማሰብ ያለብን ጉዳይ የብሔራዊ አንድነት ስሜት ካላዳበርን፣ የኔ ሳይሆን ያንተ ይቅደም ካላልን፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የምንሞትላት ካልሆንን ከሀገር ለክልል፣ ከክልል ለወረዳ፣ ከወረዳ ለቀበሌያችን ከቀበሌያችን ደግሞ ለቤተዘመዶቻችን የምናደላ ከሆንን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንደሆነች መቀጠል ይከብዳታል፡፡ በሀገራችን የራሳቸውን ጉዳይ ለማስፈፀም የሚጥሩ የውጭ ኃይሎች ሰለባ ከመሆን አንድንም፡፡ በኢጣሊያ የአምስት ዓመት ወረራ ጊዜ በሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ ታሪክ ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢጣሊያ የኢትዮጵያን የተለያዩ ጎሳዎች እርስ በእርስ በማጋጨት የመከላከል አቅማቸው እንዲደክም የዘየደችው መንገድ ነበር፡፡ አንድ አንድ አካባቢዎች ይህንን መላ ተቀብለው የኢጣሊ ግዳይ ሲሆኑ እንደ አባ ዶዮ ያሉ አስተዋይ የጎሳ መሪዎች ግን የኢጣሊያን የተንኮል መረብ በጥበብ በጣጥሰው በመጣል እርስ በእርስ በሰላም መኖራቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ ዛሬም ሁላችን እንደ አባ ዶዮ አስተዋይ ከባሕር የሰፋ ሆድ ሊኖረን ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
  • 4.     እግዚአብሔር እጅግ መልካም፣ አስተዋይ፣ ጥበበኛ፣ የሕዝቡን እሮሮ የሚሰማ፣ የሕዝቡ ሕመም ሕመሙ የሚሆን፣ በሣል ሥነ-ልቦና ያለው ብሔራው ኩራታችን የሚሆን መሪ እንዲያድለን ተግተን መፀለይ ይገባናል፡፡ አንድ አንድ ጊዜ ምንም ይምጣ ምን በራሳችን ጉዳይ ቸልተኛ መሆን አይገባንም፡፡ መሪዎችን የሚመርጡ የፓርላማ አባላት፣ ሚንስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት መልካመ የሆነ የራሳቸው ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው መገፋፋት ያስፈልጋል፡፡ እነርሱም ከኛ መካከል የወጡ በመሆናቸው ከሕዝብና ከወገኖቻቸው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመልጡ አይችሉምና፡፡ መልካም ሃሳብ ልንመግባቸው፣ ልንመክራቸው፣ የሀገሪቱን አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲያኖሩ ልናበረታታቸው ይገባል እንጅ የማያይ የማይሰማ ጣዖት እንደሚያመሰግን ካህናተ ጣዖት የሰሩትን መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ አበጀህ! አበጀህ! ልንላቸው አይገባም፡፡ ይህ የጣዖት ካህንነት ጠባይ በቤተመንግስቱም በቤተክህነቱም መሪዎች የሕዝቡን እሮሮ እንዳይሰሙ፣ ከሕዝብ ሂስ እንዲርቁ ወዘተ በማድረግ መሻሻሎች እንዳይኖሩ አይነተኛ እንቅፋት ነው፤ እናም አወዳሾችም ተወዳሾችም ልታስቡበት ይገባል እላለሁ፡፡
   እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ፊትህን ለምሕረት አዙርልን! በደላችንም በዛ! ነገር ግን በድካማችን እንደሆነ እይ! ካንተ የሚሰወር የለምና! ኢትዮጵያ ሀገርህን፣ ሕዝቦቿን ርስትህን ይቅር በል! እንዳንተ ያለ ይቅር ባይ ቸር አምላክ የለምና፤ ሌላ ተስፋ አናደርግም! በግብሩ አንተን ደስ የሚያሰኝ የቤተክርስትያን መሪ የምዕመናን አባት አድለን! የሀገሪቱን ሕዝቦች በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመዋደድ እንዲኖሩ ምሳሌ የሚሆነን፣ ፍርድን የሚያስተካክል፣ ሀገሪቱን በስልጣኔ ጎዳና እንድትገፋ የሚያደርግ ጥበበኛ መሪም ስጠን!!! አ…ሜ…ን…!!!

Thursday, August 16, 2012

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከአባ ጳውሎስ በኋላ መሪዋ ማን መሆን አለበት?

                                    
                       አቡነ ባስሊዮስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ


ቤተክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት ብዙ የውጣ ውረድ እና የመከራ ዘመናትን አሳልፍ ዛሬ ላይ እንደደረሰች ታሪኩ ሙሉ ለሙሉ ያለተጠናቀቀ ቢሆንም የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? በሚል ርዕስ በአስራ አንድ ተከታታይ ክፍሎች በዚህ የመጦመሪያ መድረክ የቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከጉዳዩ አንገብጋቢነት አንጻር ዛሬ በቀጥታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከአባ ጳውሎስ በኋላ መሪዋ ማን መሆን አለበት? በሚል ርዕስ ለመወያያ መነሻ የሚሆኑ ነጥቦችን ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡
የቤተክርስቲያን ሥርዓት እንደሚያዝዘው አንድ ፓትርያርክ በሞት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የሚደረገውን አሰራር በጥቂቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ-ገፅ ላይ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሲኖዶስና ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምን ይላል?  ከተገኘው ለማየት እንሞክር፡-
አቡነ ቴወፍሎስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ


ምዕራፍ አራት
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ
አንቀጽ 13
ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ
1.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት ተመርጦ ይሾማል፡፡
2.    ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ በሚወስነው ቁጥር መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል፣
3.    ለፓትርያርክነት የሚመረጡት ዕጩዎች ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሲሆን ብዛታቸው ከሦስት ያላነሡ ከአምስት ያልበለጡ ይሆናል፡፡
4.    አስመራጭ ኮሚቴው እጩዎችን ጠቁሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀርባል፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ምርጫው እንዲካሔድ ይደረጋል፡፡
5.    መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች የአድባራት አስትዳዳሪዎች ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በዕድሜ ከሠላሳ ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምእመናን ተወካዮች እንዲሁም ዕድሜያቸው 22 አስከ 30 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤው የሚወከሉት ከአንድ ሀገረ ስብከት አሥራ ሁለት ሆነው በሥጋወደሙ የተወሰኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው፡፡
6.    የምርጫው አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይሆናል፡፡
7.    የተመረጠው ፓትርያርክ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትንና ቀኖናዋን ሊጠብቅና አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊያስተዳድር ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡
8.    ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 14
የፓትርያርኩ የማዕረግ ስምና መንበር
1.    ፓትርያርኩ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እገሌ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ይባላል፣ ስሙም በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ይጠራል፡፡
2.    ፓትርያርኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጨ አገር ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን መንፈሳዊ አባት ነው፡፡
3.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበር በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ነው፡፡
አንቀጽ 15
የፓትርያርኩ ሥልጣንና ተግባር
1.    ፓትርያርኩ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል፡፡
2.    በዚህ ሕግ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡
3.    ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 እና በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 13 መሠረት ፓትርያርኩ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ሆኖ ኤጲስ ቆጶሳትን ይሾማል፣ እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ሲስማማበት ለብፁዓን ጳጳሳት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ይሰጣል፡፡
4.    በዚህ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት የተመረጡትን የሥራ ሓላፊዎች ይሾማል፤ በቀደምትነትና በታሪክ የታወቁትን የታላላቅ ገዳማት አበምኔቶችና የከፍተኛ አድባራት አስተዳዳሪዎች በየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት እየተመረጡ ሲቀርቡለት የማዕረግ ስም እየሰጠ ይሾማል፡፡
5.    ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የመንግሥትን ፈቃድ ማግኘት በሚያስፈልግበት ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ በተግባር ላይ ያውላል፡፡
6.    ቅዱስ ፓትርያርኩ በዓበይት ጉዳዮች ላይ ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ አያስወሰነ ይሠራል፡፡
7.    በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጐች፣ የተላለፉ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ሁሉ በተግባር ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡
8.    በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡትን ሕጐችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በፊርማው ያስተላልፋል፡፡
9.    ከመንግሥታውያንም ሆነ መንግሥታውያን ካለሆኑ /ቤቶች ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚቀርቡ ደብደቤዎች ወይም አቤቱታዎችን ደረጃቸውን ጠብቀው በሕግ መሠረት ይፈጸሙ ዘንድ ለጠቅላይ /ቤት ያስተላልፋል፡፡
10.    በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ለማገልገል ወይም የነፃ ትምህርት ለመማር የሚላኩ ካህናት በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 መሠረት ተመርጠው ሲቀርቡ እንዲላኩ ያደርጋል፡፡
11.    ከውጭ የሚመጡትን እንግዶች በውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቅራቢነት እየተቀበለ ያነጋግራል፡፡
12.    ፓትርያርኩ በውጭ አገር በሚደረግ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ለመገኘትና ጉብኝት ለማካሔድ በሚያስፈልግ ጊዜ ስለተልዕኮው ጉዳይ አስቀድሞ በቅዱስ ሲኖዶስና በቋሚ ሲኖዶስ ያስወስናል፡፡

አቡነ ተክለሀይማኖት ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ
 
አንቀጽ 16
የፓትርያርኩ ከማዕረግ መውረድ
1.    ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከተሾመ በኋላ የተቀበለውን ሓላፊነት በመዘንጋት፡-
. የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚያሰነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣
. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ከቁጥር 172 እስከ 208 በተደነገገው መሠረት በደለኛ መሆኑ ከታመነበት፣
. በቃሉ የማይገኝና በዚህ ሕግ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 7 ድንጋጌ መሠረት በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ያልጠበቀ በአጠቃላይ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነትን ያጣ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያስነቅፍ መሆኑ በትክክል ከተረጋገጠ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከሥልጣኑ ይወርዳል፤ በምትኩም ሌላ ፓትርያርክ ተመርጦ ይሾማል፡፡
2.    ከዚህ በላይ በተደነገገው መሠረት ከሥልጣኑ የተገለለ ፓትርያርክ በቀኖና ተወስኖ በገዳም ይቀመጣል፡፡
3.    ከሥልጣን የተገለለው ፓትርያርክ በገዳም አልቀመጥም በቀኖናም አልወሰንም በማለት እምቢተኛ ከሆነ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ይለያል፡፡
4.    ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ሥራውን በማካሔድ ላይ እያለ እሥራትና ግዞት ቢደርስበት ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትመራለች እንጂ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡
5.    ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ ፍትሕ መንፈሳዊ በሚያዝዘው መሠረት ይፈጸማል፡፡

አቡነ መርቆርዮስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ
 
አንቀጽ 17
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
1.    ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡
2.    የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደሥራው ሁኔታ እየታየ 40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይሆናል፡፡
3.    የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ተግባር
. ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉደዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር እየመከረ ያከናውናል፡፡
. በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ሆኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡
/ምንጭ፦ ሕገ ቤተ ክርስቲያን 1991 ./

አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ

ዛሬስ መሪያችንን ለመምረጥ ምን እናድርግ?

ከዚህ ለማየት እንደሞከርነው የአንድ ፓትርያርክ የምርጫ ሂደት ከ 40 እስከ 80 ቀናት ይፈጃል፡፡ በግብፅ አቡነ ሺኖዳ ከዚህ ዓለም ሲለዩ እንደተደረገው ማለት ነው፡፡ ግብፃውያን በዚህ ረገድ በጣም ጥሩ እና የዳበረ ልምድ አላቸው፡፡ ምዕመናኑ ሳይቀር የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ በጸሎት ከመትጋት ጀምሮ ሁነኛ ሰው ለፓትርያርክነት የበቁ ሰዎችን እስከመጠቆም ይደርሳል- የምዕመናን ድርሻ፡፡
አሁን የኛ ቤተክርስቲያን ባለ ድርሻ አካላት ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን እናንሳ፡-
  1.    የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን ቢያን በፀሎት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የፀሎት ጊዜ ቢታወጅ ጥሩ ነው፡፡ ከመካከላችን ንፅሐ ለቦና ያላቸው ሰዎች ጸሎታቸውም ኃይልን የምታደርግ ሰዎች፣ መነኮሳት፣ ደናግል ወዘተ አይጠፉምና፡፡ 
  2.     ቤተክርስቲያን የጸሎት ጊዜ ብታውጅም ባታውጅም ሁሉም ሕዝበክርስቲያን በጸሎት መትጋት ይኖርበታል፤ ስለ ኃጢያታችን ክፉ መሪ እንዳይታዘዝብን ኃጢያታችንን ይቅር እንዲለን ንስሃ እየገባን ከእግዚአብሔር ምሕረትን ዘወትር ልንለምን ይገባል፡፡ 
  3.  ቅዱስ ሲኖዶስ እና ሊቃነ ጳጳሳት የሚመርጧቸው አስመራጭ ኮሚቴ አባላትን ማንነት በትክክል ማጤንና ተገቢ የሆኑትን ሰዎች ብቻ መምረጥ አለባቸው፡፡ በቤተክህነቱ አካባቢ ያሉ ወሮበሎች ይህንን ዕድል ውስጥ ለውስጥ በመሽሎክሎክ ለመጠቀም የማይቆፍሩት ጉድጓድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ ይኖራቸዋል አንልም፡፡ 
  4.  ቅዱስ ሲኖዶስ የፖለቲካ አጀንዳ ካነገቡ ካድሬ-ነክ ሰዎች ጥንቃቄ ማደረግ ይኖርበታል፡፡ በ1983 እና በ1984 ዓ.ም በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ስለተከናዎኑት ታሪካዊ ጥፋቶች የተሟላ መረጃ ቢኖረን ምን አልባት የቤተክርስቲያን ለሁለት መከፈልና ሰላም ማጣት ምክንያቱ ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ 
  5.  ቅዱስ ሲኖዶስ እና ሊቃነ ጳጳሳት አስመራጭ ኮሚቴውን በቅርብ በመሆን ሂደታቸውን መገምገምና ሂስና መመሪያ መስጠትና ማስተካከል ቢችል እጅግ መልካም ነው፡፡ በጸሎት፣ በምክር፣ መረጃ በመስጠትና በመሳሰሉት ደግሞ ሁላችንም ከቅዱስ ሲኖዶስና ከአስመራጭ ኮሚቴው ጎን መቆም ይጠበቅብናል፡፡ 
  6.  ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ አስመራጭ ኮሚቴው የመስሪያ ክልሉን እንዳያጠቡት ማለትም አዲስ አበባና ዙሪያ ገባዋ ብቻ ለእጩዎች ፍለጋ እንዳትዳሰስ እሰጋለሁ፡፡ ሆኖም እጩዎች ከሊቃነ ጳጳሳትና ከጳጳሳት ብቻ ስለሆነ ብዙም ስጋት ላይሆን ይችላል ይህ ጉዳይ፡፡ 
  7.  ከዚህ ከፓትርያርክ ምርጫ ጋር ተያይዞ ሌሎች ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የሚከናዎን ከሆነ ግን በተራ ቁጥር 6 ላይ የተገለጠጸው ጉዳይ ተገቢው ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡ የጳጳሳት ሹመት መዳረሻዎች ከአዲስ አበባና ከዋና ዋና ከተሞች ብቻ የመሆን ከፍተኛ አዝማሚያ አለ፡፡ በተለይም ለመንበረ ፓትርያርኩ ቅርበት ያላቸው እንደ ቅድስት ሥላሴ፣ መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ፣ መናገሻ ገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዎችጊስ፣ ግቢ ገብርኤል፣ ወዘተ ያሉትን አስተዳዳሪዎች በቀጥታ በመውሰድ መሾም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ስለዚህ በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች ብዙ ጥቅም ለማሯሯጥ ከከተማ ወደ ከተማ የማይዋዥቁትን የተረጋጋ መንፈሳዊነት የተላበሱ ገዳማውያንን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ የየአህጉረ ስብከት ሊቃነ-ጳጳሳትና ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የቤተክርስቲያን ጠበቃ ዋልታ መሆን የሚችሉ ሰዎችን ከየአህጉረ ስብከታቸው ከነ ሙሉ መረጃ በማቅረብ የሰው ረሃብ ያለበትን የጳጳሳት ምርጫ ሊያረኩት ይገባል፡፡ 
  8.  መንግስት ከቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ እጁን ማንሳት አለበት፡፡ ምን አልባት የፀጥታ አስከባሪዎች በአንድአንድ እሰጣገባዎች ውስጥ በመግባት ህግዎጦችን ወደ ህግ በማቅረብ ከምዕመናን ጎን ሎቆሙ ይገባ ይሆናል፡፡ ነገር ግን መንግስት በቤተክርስቲያን ውስጥ ምንም ዓይነት ዓላማና ግብ ሊኖረው አይገባም፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ ሆኗል ማለት ግን አይደለም፡፡ ነበርም አልነበርም ለማለት የተሟላ መረጃ ሊኖር ይገባልና፡፡ መንግስት ቤተክርስትያን ነፃ ሆና ወሳኝ መሪዋን በመምረጧ በምታገኘው መንፈሳዊ ዕደገት ሀገር ትባረካለች፤ ሀገር ታሪካዊ ቅርሶቿና ሞራላዊ ልዕልናዋ እንደተከበረ ይቆያል፤ ምዕመናን ግበረ ገብነትን በሚገባ ከተረጋጋች የፀጥታ ወደብ ከሆነችው ቤተክርስቲያን መማር ይችላሉ - እናም የሀገር አደራን በሚገባ ለመሸከም የተገቡ ይሆናሉ፤ የቱሪዝም ገቢና ሌሎች ከዚህ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው የብዙ ብዙ እሴቶችን በሚገባ ጠብቀን ለማቆየት እንችላለን፡፡ 

እናንተስ ምን ትላላችሁ ….?


…ይቀጥላል…