በባለፈው ክፍል ስድስት ግራኝ አህመድ በሀገሪቱ እና በቤተክርስቲያን ላይ ያደረሰውን እልቂት እና ጥፋት ተመልክተናል። ዛሬ ደግሞ በዚህ ዘመን የደረሰው የጥፋት ዘመን አሉታዊ አሻራዎችን እንመለከታለን።
ባለፈው ክፍል እንደተመለከትነው ኦትማን ቱርኮች ኢትዮጵያን ልክ እነደሌሎቹ አጎራባች ሀረገራት ሁሉ የእስልምና መነሃሪያ ለማድረግ እና የምዕራብ አውሮፓ የክርስቲያን መንግስታትን በቀይ ባህር ላይ የሚያደርጉባትን ተቀናቃኝነት ለማስወገድ ኢትዮጵያን መቆጣጠር እና እስላማዊ መንግስት እንዲመሰረት ለማድረግ ግራኝን መርዳት እና ክርስቲያናዊ መንግስቱን መውጋት በእቅዱ ውስጥ በማስገባት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ እልቂት እና ጥፋት ሊያስከትል ችሏል። በዚህ በ፲፭ ዓመት ጊዜ ውስጥ በቤተክርስቲያን እና በሀገሪቱ ላይ ያደረሳቸው ጥፋቶች የሚከተሉት ናቸው።
፩. የካህናት እና የቤተክርቲያን ሊቃውንት እልቂት፦ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እንቁ የቤተክርቲያን አባቶች ካህናት ዲያቆናት የቤተክርቲያን ሊቃውንት እና ገዳማውያን መነኮሳት ተጨፍጭፈዋል፤ ታርደዋል፤ አልቀዋል።
፪. የሕዝበ ክርቲያኑ እልቂት፦ በግራኝ እና በሠራዊቱ ብዙ ንፁሐን ክርቲያኖች በሰይፍ ተሰይፈው በጦር ተወግተው እና እጅግ አሰቃቂ በሆነ አገዳደል የግፍ ፅዋ ጨልጠዋል። ብዙዎችም ተገደው ሰልመዋል። የእስልምና ተከታዮችን ተቀብላ በሰላም ያስተናገደች ሀገር እጇ አመድ አፋሽ ሆኖ በበጎ ፋንታ ክፉ ተመልሶላታል።
፫. አቢያተ ክርቲያናት ገዳማት እና አድባራት መቃጠል፦ በሺዎች የሚቆጠሩ አቢያተ ክርቲያናት ገዳማት እና አድባራት ተቃጥለዋል። እነዚህ ቦታዎች በዚያ ዘመን የሀገሪቱ የትምህርት ማዕከላትም ስለነበሩ የነበራቸውን ልዕልና ይዘው መቀጠል ቢችሉ ኖሮ ሀገሪቱ ከፍተኛ የእድገት እመርታ ለማሳየት የሥነ እድገት እና የሥነ ልቦና ጥንካሬ ማዕከላት ሆነው የሀገሪቱ ዘመናዊነት መነሻ መካናት መሆን ይችሉ ነበር። ከዮዲት ጉዲት ዘመን በኋላ የተገነቡ አያሌ የትምህርት ማዕከላት ወደ ባድማነት ተቀይረዋል። የዘመናዊ ዩኒቨርሲቲዎች መመስረቻ መሆን ይችሉ ነበር። ፍፁም እግዚአብሔርን በመፍራት የተመሰረቱ የትምህርት ማዕከላት ስለነበሩ የሕዝቡ ሐይማኖታዊ ተነሳሺነት አይደበዝዝም ነበር።
፬. የመፃሕፍት እና ንዋያተ ቅድሳት መቃጠል፦ አንቱ በተባሉ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የተፃፉ የሐይማኖት የፍልስፍና የሥነ-ህንፃ የሥነ-ጥበብ የዜማ እና የሥነ-መንግስት የሥነ-ህክምና የሥነ-ፈለክ እንዲሁም የሥነ-ልቦና መፃሕፍት ወደ አመድነት ተለውጠዋል።
የግራኝ የጥፋት ዘመን በኋላ የዚህ ዘመን ያስከተለው የረጅም ጊዜ አሉታዊ አሻራዎች ክ/ዘመን ተሻጋሪ ከመሆናቸው የተነሳ ዛሬ ላለንበት የሀገሪቱ ኋላ ቀርነት እና የማንነት ማጣት ጥያቄ እንዲሁም የቤተክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች አይነተኛ መንስኤ ሆኖ በመቀጠል ላይ ነው። ይህ ዘመን ካስተላቸው የረጅም ጊዜ አሉታዊ አሻራዎች የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
፩. የሐይማኖታዊ ባህሎቻችን መለወጥ፦ በዮዲት ጉዲት ዘመን በነበረው የእልቂት ዘመን የባህል “አብዮት” ያላስከተለው የይሁዲዎች ክርስቲያናዊ ባህል ተፅዕኖ ውስጥ በመግባታቸው ልዩነቱን በሚገባ ጠንቅቀው ስላላወቁት እና በወቅቱ የነበረው የዮዲት ጉዲት ዘመቻም የታለመ ግብ ያለው ስላልነበር እንዲሁም የሀገራችን የክርስትና ሐይማኖት ከይሁዲነት የመጣ ስለነበር ኦሪታዊ የሐይማኖት ባህሉ ከይሁዲዎች ጋር ስለሚያመሳስለው ይህ የሐይማኖታዊ ባህል ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖ በሕዝቡ ላይ አላስከተለም ነበር።
ነገር ግን በግራኝ ወረራ ወቅት የተወረረው ክርስቲያናዊ ሕዝብ እና በወራሪው ሃይል መካከል የሰማይ እና የምድር ያህል የሚራራቅ ሐይማኖታዊ ባህል በመኖሩ በተወረሩት አካባቢዎች ሕዝቡ እንዲሰልም ከመገደዱም በላይ ሐይማኖታዊ ባህሉንም እርግፍ አድርጎ በመተው በዝሙታዊ የጋብቻ ሥነ-ስርዐት እና አሕዛባዊ የአኗኗር ዘይቤን እንዲለምድ በወራሪው ሃይል አማካኝነት ግዳጅ ስለተጣለበት ሐይማኖታዊ ባህሉ በመተው እንዝላል እና ግድ የለሽ እንዲሆን ተገዷል። የዚህ ግድ የለሽነት እና ሕዝቡ በአካባቢው ያሉት ቤተክርስቲያናት በመውደማቸው ምክንያት ያልተገባ አሕዛባዊ ፀባይ ውስጥ በመግባት ጣዖታትን ወደ ማምለክ እንዲሸጋገር በር ከፍቷል።
፪. የሐይማኖታዊ ትምህርቶቻችን ይዘት መቀነስ፦ ወቅቱ ባደረሰው እልቂት ምክንያት የሐይማኖት ማመሳከሪያ የነበሩ መፃሕፍት እና ታላላቅ ሊቃውንት መሞት ምክንያት ለ፲፭ ዓመታት ያህል የነበረበትን አሕዛባዊ ልማድ ትቶ ተመልሶ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ በነበረው ርብርብ መንፈሳዊ አገልግሎት ለተጠማው ሕዝብ የሚያገለግሉ እና የሚያስተምሩ የሚቀድሱ እና የሚያቆርቡ መምህራንን ካህናትንና ዲያቆናትን በአጭር ጊዜ ለማፍራት በማቀድ የቤተክርስቲያን አግልጋይነትን ለመሾም የሚጠይቀውን የመንፈሳዊ ብስለት እና የትምህርት ብቃት ስለተቀነሰ ቤተክርስቲያን የተጠበቀውን ያህል ለውጥ ማምጣት የሚችሉ የቤተክርቲያን ጠበቆች የሆኑ ሊቃውንትን ካህናትን እና አባቶችን ማግኘት አልተቻላትም።
ይህም ከዮዲት ጉዲት ዘመን በኋላ የነበረውን የመሰለ የቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን እንዳይደገም እና ቤተክርስቲያንም ሆነ ሀገሪቱ ተመልሳ እንዳታንሰራራ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል። ይህ አሉታዊ ተፅዕኖ በመጀመሪያ ቁጥር ፩ ላይ የተገለጸው አሉታዊ ተፅዕኖ ውጤትም ነበር።
፫. የአውሮፓውያን ሰባኪዎች መምጣት፦ በወቅቱ የነበሩት ሃያላን የአውሮፓ ክርቲያን መንግስታት (ፖርቱጋል እና ስፔን) ከኢትዮጵያ በእስላማዊ ሀገራት ረዳትነት በእስላማዊ ሱልጣን ሀገሪቱ መወረሯን ተገልጾ እርዳታ ቢየጠየቁም በወቅቱ በቀይ ባህር ላይ የነበራቸውን ወደ ህንድ እና ወደ ሩቅ ምስራቅ የሚያደርጉትን የንግድ ጉዞ ተቃናቃኛቸው ኦትማን ቱርኮች መሆናቸውን ስለሚያውቁ በነገሩ ጣልቃ ላለመግባት እና ኦትማን ቱርኮችን ላለማስቀየም ይሁን ወይም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ሀገር በመሆኗ የካቶሊክ ቤተ እምነት ተቀናቃኝ ተደርጋ ተወስዳ የርዳታ ጥያቄው ለ፲፭ ዓመታት ዘግይቶ ሕዝቡ ሁሉ አልቆ ብዙዎች ሰልመው ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ በእስላማዊ ሱልጣን ወታደሮች ተወርራ ታሪኳ ከተቀየረ በኋላ የፖርቱጋል ወታደሮች መጥተው በወይና ደጋ ጣና ሐይቅ አጠገብ በተደረገው ጦርነት ላይ ተሳትፈው አህመድ ገራኝ ስለተገደለ ድሉ በእነርሱ ምክንያት የመጣ አድርገው በመቁጠር በሀገሪቱ ላይ የራሳቸውን ዓላማ የሚያስፈፅሙበት እና ኦርቶዶክሳዊ ሐይማኖት ጠፍታ የሮማ ቤተ እምነት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ በማቀድ “መልእክተኞቻቸውን” ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ባዕድ ትምህረት በማስተማር የእልቂት እና የጥፋት ዘመን ያሰቀቀውንና የሥነ-ልቦና ሰለባ ያጋጠመውን ሕዝብ ግራ ያጋቡት ጀመር። በሀገሪቱም ሁከት እና እልቂት እንዲነሳ በተለይ በአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት ሐሳባቸው በንጉሱ ተቀባይነት ስላገኘ ከንጉሱ ወታደሮች ጋር በመሆን ሕዝቡን እንደጋና “ለማጥመቅ” ታቦታትን ከመንበራቸው ለማስወጣት የተለያዩ የቅዳሴ እና የቤተክርስቲያን ቀኖናዎች በሮማ ቤተ እምነት መሰረት እንዲከለሱ ለማድረግ በአጠቃላይ በቤተክርቲያን ላይ ዶግማዊ እና ቀኖናዊ እንዲሁም ትውፊታዊ ለውጥ ለማምጣት ሌት ተቀን ተግተው ከሦስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ከ፰ ሺህ ሰማእታትን ተሰይፈው እንዲገደሉ እና ምድሪቱ የእሪታ እና የእለቂት የሰቆቃ ምድር እንድትሆን አድርገዋል። በግራኝ ዘመን የደረሰበት ቁስል ሳያገግም በሕዝቡ ቁስል እና የሥነ-ልቦና ስብራት ላይ ሌላ ጥዝጣዜ እና የሞራል ውድቀት እንዲደርስ አድርገዋል። በዚህም ሀገሪቱ እየተዳከመች ሄዳ በመጨረሻ ከአንድ ክ/ዘመን በላይ የመከፋፈል እና የጦርነት ጊዜ የእርስ በእርስ ዝርፊያ እና ቅሚያ የበዛበት የመሳፍንት ዘመን እንድታስተናግድ ጥርጊያ መንገድ ከፍተዋል። ይህንን ታላቅ የምዕራባውያን በሰው ደም እና ህይወት ላይ የቁማር ጨዋታ ትውልድ ከታሪክ ማህደሩ በቀላሉ ሊፍቀው አይቻለውም። ዛሬም ይህንን እያስተናገድን ስለሆነ በዚያ ጊዜ የተከናወነው ግፍ ዛሬም እያየነው የትናንትናውንም የዛሬውንም ህመሙን እንድናዳምጥ እና እንዲሰማን ተገደናል።
…ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment