Wednesday, June 29, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አምስት)

ክርስትና በኢትዮጵያ በ፬ኛው መ/ክ/ዘመን ጀምሮ በነበረው እጅግ ጠንካራ የወንጌል እና የክርስትና ትምህርት መስፋፋት ብዙ ሕዝብ ከንጉሳውያን ቤተሰብ ጀምሮ እየተጠመቀ የክርትና ሐይማኖት ተከታይ ሆነ። ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ እስከተሾመበት እስከ አብርሃ ወአፅብሃ ዘመነ መንግስት ድረስ የወንጌል ዜናዋ በሀገራችን ቢነገርም ሕዝቡን ግን በማጥመቅ የመንፈስ ቅዱስ ልጆች እንዲሆኑ ማድረግ አልተቻለም ነበር። በመካከለኛው ምስራቅ እና በሮማ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ርቱዐነ ሐይማኖት አባቶች በሮም ቤተክርስቲያን አማካኝነት በኬልቄዶን ጉባኤ የተጀመረው ኢ-ፍትሐዊ ድብደባ እና እንግልት በ፭ኛው መ/ክ/ዘመንም ሐይማኖታችንን አንክድም ምስክርነታችን አይታጠፍም ባሉት ቅዱሳን አባቶች ላይ ስለቀጠለ ዘጠኙ (ተሰዐቱ) ቅዱሳን የሮማ ቤተክርስቲያን ታስተዳድራቸው ከነበሩት ከተለያዩ የሮም ግዛት ተሰደው በእግዚአብሔር መሪነት ወደ ኢትዮጵያ መጡ።
እነዚህ ቅዱሳን ወደኢትዮያ ከመጡ በኋላ ግዕዝ ቋንቋን በሚገባ አጥንተው የተለያዩ ቅዱሳት መፃሕፍትን ወደ ግዕዝ በመተርጎም ወንጌልን ለሕዝቡ እንዲስፋፋ ወንጌል በማስተማር የተለያዩ ገዳማትን በመመስረት ሥርዐተ ምንኩስናን በማስተማር እና በማስፋፋት የቤተክርስቲያንን ትምህርት (ግብረ ዲቁና እና ምስጢረ ክህነትን) በማስተማር ወዘተ የቤተክርቲያኗ የመሪነት ሚና በመንፈስ ቅዱስ እና በተለያዩ አገራዊ ጉዳይ ከፍተኛ እመርታ እንዲያሳይ አድርገዋል። እነዚህ ቅዱሳን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባፈሯቸው ሊቃውንት አማካኝነት በአራቱም አቅጣጫ ትምህርተ ሐይማኖት በሚገባ ተጠናክሮ ቀጠለ። እንግዲህ በዚህ ጊዜ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃያል የነበረችበት እና በስልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰችበት ጊዜም ነበር። በዚህ ጊዜ የተለያዩ ቅዱሳን አባቶች የወጡበት ሲሆን ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ያሬድን ኢትዮያ የወለደችው በዚህ ጊዜ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከ፬ኛው መ/ክ/ዘመን እስከ ፰ኛው መ/ክ/ዘመን ድረስ ከፍተኛ እድገት ያስመዘገበችበት እና በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ አወንታዊ የመሪነት ሚናዋን የተጫወተችበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል። በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭም በየመን የናግራን ሰማእታትን በይሁዲዎች መጨፍጨፍ ያስቆመች ብርሃኗ ከሕዝቧ ተርፎ ለዓለም ያበራበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል።
በዚህ ሁኔታ እያለች ነው እንግዲህ በመካከለኛው ምስራቅ የተነሳው የእስልምና ማዕበል በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖውን እያሳረፈባት የመጣው። እስልምና በ፯ኛው መ/ክ/ዘመን በአረቢያ ምድር ተጠንስሶ በሀገሬው ሰዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው "ነብዩ" መሀመድ ተከታዮቹን ኢትዮጵያ ውስጥ በየዋህነቱ እና በእንግዳ ተቀባይነቱ የታወቀ ንጉስ አለ እና ወደዚያ ሽሹ በማለት ወደ ሀገራችን ሲልካቸው ሀገራችን በመልካም ሁኔታ ተቀብላ ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ አስተናገደቻቸው። ይህም በወንጌል ከተፃፉት ስድስቱ ቃላተ ወንጌል አንዱ እንግዳ ሆኜ ብመጣ ተቀብላችሁኛል የሚለውን መተግበሯ ነበር። ኢትዮጵያ ይህን በማድረጓ በቁራን ላይ አደራ ተቀባይ እና ባለውለታ ተደርጋ ትፃፍ እንጅ በወቅቱ ከነበረው የእስልምና አፍራሽ ስራዎች ልትድን አልቻለችም። በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ እንዲገታ እና ቀስ በቀስ ሀገሪቱ እየተዳከመች እንድትሄድ በኋላም የእስልምና መሪዎች ሰለባ እንድትሆን የማዳከም እቅድ ተነድፎ በሙስሊም መሪዎች ተተገበረ። በዚህ የተነሳ ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ለምነቱን ከማጣቱ በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴው እክል ሲገጥመው የአክሱም ሥርወ መንግስት ቀስ በቀስ እየተዳከመ መጣ።
ከዚህ በሀገሪቱ ማዕከላዊ መንግስት መዳከም ተከትሎ በ፱ኛው መ/ክ/ዘመን ዮዲት የተባለች አይሁዳዊት ሴት (ከፈላሻ ዘር) በሀገራችን ላይ ከፍተኛ የጥፋት ዘመን አዋጅ አውጃ ብዙ ቤተክርስቲያናት አድባራት ገዳማት ቤተመዛግብት ንዋተቅድሳት መፃሕፍት እና አልባሳት ተቃጥለዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ዲያቆናት ካህናት መምህራን መነኮሳት እና ገዳማውያን ተሰውተዋል። ለ፵ ዓመታት ባደረሰችው የጥፋት ዘመቻ ብዙ የቤተክርስቲያን መረጃዎች ጠፍተዋል። ይህ የዮዲት ጉዲት ዘመን በሀገራችን ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ከፍተኛ ጥፋት ያስከተለ እና ለረጅም ዘመናት የቆየ የሰቀቀን እና በሀገራችን ከነበሩት የቤተክርስቲያን አሰቃቂ የመከራ ዘመናት የመጀመሪያው ነው። በዚህ አሰቃቂ የግፍ እና የመከራ ዘመን የአክሱም ሥርወ መንግስት እጅግ ተዳክሞ የቤተክርስቲያኗ ትምህርትም ለ፵ ዘመናት ተስተጓጉሎ ቆየ።
የዮዲት ጉዲት ዘመን በቅርሶች እና መፃሕፍት መውደም በክርቶያኖች መጨፍጨፍ እና በአቢያተ ክርስቲያናት መቃጠል ከፍተኛ የሞራል እና የሥነልቦና ውድቀት ቢያጋጥምም የሐይማኖታዊ ባህል መዛባት እና የረጅም ጊዜ ጠባሳ በሕዝቡና በክርትና ሐይማኖት ላይ አልተወም። ይህም በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፦
፩. በዚያ ጊዜ የነበረው የሕዝቡ የሥነልቦና ጥንካሬ በዚያ ጊዜ የነበረው ሕዝብ እና መንግስትም ቢሆን ለዓለማዊ ኑሮ ዋጋው አነስተኛ እና ከሞት በኋላ ያለው ህይወት አማራጭ የሌለው በሌላ ዝባዝንኬ እና እራስን በመደለል ሊታለፍ እና ሊናቅ የማይችል መሆኑ ሕዝቡ በሚገባ የተረዳው ሀቅ ነበር። በዚህ የተነሳ ሐይማኖትን ከመተው እና ሐይማኖታዊ ያልሆነ ድርጊት እና ሥራን በወቅቱ በነበረችው ጨካኝ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ከመበገር ይልቅ ሞቶ የህይወት አክሊልን መቀበል የሚመርጥ ለፅድቅ የጨከነ ልብ ያለው ሕዝብ ነበር ማለት ይቻላል።
፪. የበኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩት አይሁዶች (ፈላሾች) ከክርቲያኖች ጋር የነበራቸው የባህል ውርርስ እና መመሳሰል፦ አይሁዶች ከክርቲያኖች ክርቲያኖች ደግሞ ከልደተ ክርስቶስ በፊት በነበራቸው ኦሪታዊ ሐይማኖታዊ ልምድ የተነሳ በነበረው የባህል መመሳሰል የዮዲት ጉዲት የጥፋት ዘመቻ የባህል አብዮት አልነበረውም።
፫. የዮዲት የጥፋት ዘመቻ በውል የታወቁ ግቦች ስላልነበሩት፦ ከክርትና ወደ ይሁዲነት በሃይል ለመቀየር ከመታሰቡ በቀር ከጭፍን ጥላቻ የመነጨ ስለነበር የራሱ ግብ ያለው ዘመቻ ስላልነበር ስር ነቀል የሐይማኖታዊ ባህል ለውጥን መሰረት ያደረገ አልነበረም።
፬. ከጥፋት ዘመኑ ማለፍ በኋላ የተከናወነው የመልሶ ማቋቋም ከፍተኛ ጥረት የተለያዩ ቅዱሳን በቃላቸው ያጠኑትን በብራና ላይ በመፃፍ እና በተለያየ ምክንያት ከጥፋት የተረፉትን ደግሞ በማባዛት አዳዲስ መፃሕፍትንም ፅፎ ለተላዩ በሐገሪቱ በሚገኙ ት/ቤቶች በማሰራጨት የተቃጠሉ አቢያተክርስቲያናትን መልሶ በማቋቋም እና በመገንባት ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ በዚህ ዘመን የደረሰው የጥፋት ቁስል ወዲያውኑ ሊያገግም ችሏል። ይህም ወርቃማው የሥነፅሑፍ ዘመን ተብሎ የታወቀውን ብዙ አባቶቻችን እስከዛሬ የምንገለገልባቸውን መፃሕፍት የፃፉ እና ወንጌልን በድፍረት የጣኦት አምልኮ ያመልኩ ከነበሩ መሳፍንት እና የተለያዩ ጎሳዎች ድረስ የተሰበከበትን ዘመን አስከትሏል። ይህ ዘመን ቤተክርስቲያን ተመልሳ ያበበችበት ዘመን ነበር።
በእስልምና እና በዮዲት ጉዲት አሰቃቂ ዘመን አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት የአክሱም ሥርወ መንግስት እየተዳከመ ሄዶ መጨረሻ የዛግዌ ሥርወ መንግስት ተመስርቶ የአክሱም ሥርወ መንግስት ሕልውና በዚሁ አከተመ። የዛግዌ ሥርወ መንግስትም የመናገሻ ከተማውን ከአክሱም ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ላስታ አዛወረው።
ኢትዮጵያ በዛግዌ ሥርወ መንግስት አስተዳደር ከሀገሪቱ ሰሜናዊ ጫፍ በአንፃራዊነት ወደ ደቡብ በመሸሿ ምክንያት ሰሜናዊ የኤርትራ ክፍለ ግዛቶች የእስልምና ተከታይ ነጋዴዎች መፈንጫ እንድትሆን በር የከፈተ ሲሆን በሀገሪቱ ላይ ያሉትን የንግድ ወሳኝ መስመሮችንና የባህር በሮችን ለመቆጣጠር አዳጋች ስለነበረ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትም የዚያኑ ያህል አዝጋሚ እንዲሆን ተገዷል። በባህር በር አካባቢ ያሉ የሀገሪቱ ጎሳዎች የእስልምና ሰለባ መሆን እስልምና ወደ ሀገሪቱ በወላሉ የመግቢያ እና የመቦረቂያ በር ክፍት ሆኖ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ በቤተክርስቲያን እድገት ላይ አሳርፏል። በርግጥ የሀገራችን ልዕልና ከአክሱም ሥርወ መንግስት ጊዜው ጋር ሲመዛዘን ያነሰ ቢሆንም ሀገሪቱ በዛግዌ ሥርወ መንግስትም የሀገራችን የሞራል ልዕልና እና የኪነጥበብ እድገት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት እና ሐይማኖታዊ እድገትም እንደተመዘገበ በዘመኑ ከተሰሩ ሥራዎች ምስክርነት እና ከተለያዩ የታሪክ ድርሳናት መገንዘብ ይቻላል።
በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ በዛግዌ ሥርወ መንግስት የነበረው የሐይማኖታዊ እድገት ተመልሶ ማበብ እና የመካከለኛው ዘመን የሀገሪቱን ታሪክ እንቃኛለን።
...ይቀጥላል…



Thursday, June 23, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አራት)

ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታታይ ፅሑፎችን ለመመልከት እንሞክራለን።
የኢትዮጵያን የክርስትና አመጣጥ እና አምልኮተ እግዚአብሔር ስንመለከት ታሪኩ ከክርስቶስ ልደት በፊት ብዙ ሺ ዘመናትን አቋርጦ ወደ ኋላ ይወስደናል ይህም ኢትዮጵያ በሦስቱም ዘመናት እግዚአብሔርን እያመለከች የምትኖር ብቸኛ ሀገር ያደርጋታል። ውም በዘመነ ሕገ-ልቦና በዘመነ ኦሪት እና በዘመነ ወንጌል ናቸው። የኢትዮጵያን በዘመነ ሕገ-ልቦና እግዚአብሔርን ታመልክ እንደነበር የሚያሳየው በዘፀአት ላይ የተፃፈው የሙሴ ወደ ምድያም ምድር መሰደድ እና በዚያም የካህኑ የዮቶር በጐች ጠባቂ እንደነበር የካህኑ የዮቶርን ልጅም አግብቶ እንደነበር በዚህም በኋለኛው ዘመን እስራኤልን ከግብፅ ባርነት አውጥቶ እየመራ ወደ ከነአን ምድር ሲወስዳቸው ኢትዮጵያዊቱን በማግባቱ በእህቱ በማሪያም እና በወንድሙ በአሮን ተቃውሞ እንደገጠመው ያሳያል። ዮቶር ካህን መሆኑ የሚያስረዳው በኢትዮጵያ ከሙሴ ወደ ካህኑ ዮቶር መምጣት በፊት በውል የተረዳ እና ለብዙ ጊዜ የቆዬ አምልኮተ እግዚአብሔር እንደነበር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካህኑ እና የሳሌም ንጉስ መልከጼዴቅ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እና ኢየሩሳሌምንም መመስረቱ በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ፀንቶ የቆየ አምልኮተ እግዚአብሔር እንደነበር ያሳያል።
በመፅሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ክፍሎች እንደተገለጠው ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ እንኳን የተወሰደው ኩሽ የተባለ የኖህ የልጅ ልጅ (የካም ልጅ) የመሰረታት ሀገር መሆኗን እና በስሙም ኩኝ ተብላ የምትጠራ ሀገር እንደነበረች ኢትዮያ የሚለው ስያሜም ብሉያት መፅሐፍትን ከእብራይስጥ ወደ ፅርዕ ቋንቋ የተረጎሙ ሰብአው ሊቃናት ኩሽ የሚለውን በተለያዩ የብሉያት መፅሓፍት ያለውን የሀገሪቱ ስም ኢትዮያ ብለው እንደተረጎሙት ይህም የኩሽ ሌላው ስሙ ከሆነው ኢትዮስ የተወሰደ መሆኑን እንገነዘባለን።
ኦሪት ሕግ በሲና ምድረ በዳ በሙሴ በኩል ከተሰጠ ከ፪፻ እስከ ፫፻ ዓመታት ጊዜ በኋላም ንጉስ ሰሎሞን የእስራኤል ንጉሳቸው በነበረበት እና በኢትዮያም ንግስት ማክዳ በነገሰችበት ዘመን የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም የኢትዮያ ንግስት በተጓዘችበት ጊዜ ከንጉስ ሰሎሞን ፀንሳ ስለተመለሰች ቀዳማዊ ሚኒሊክን ወለደች። ቀዳማዊ ንጉስ ሚኒሊክም ፳፪ ዓመት በሞላው ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄዶ ከአባቱ ዘንድ ለ፫ ዓመት ያህል ሥርዓተ ንግስናን ተምሮ ሕገ ኦሪትን እና ከሙሴ እስከ ሰሎሞን ያሉትን የብሉያት መፃሕፍት ይዞ ፫፻፲፰ ሌዋውያን ካህናትንና ወደ ፲፪ ሺ የእስራኤል የበኩር ልጆችን አስከትሎ ወደ ኢትዮያ መጣ።
በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ሀገራችን ኢትዮያ ከሕገ-ለቦና ወደ ዘመነ ኦሪት የተሸጋገረችው። በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ ካሉት የተለያዩ ማስረጃዎች በተጨማሪ ሀገራችን በዘመነ ኦሪት አምልኮተ እግዚአብሔር ስትፈፅም የነበረች መሆኗን እስከ አሁን ህያው በሆኑት የኦሪት መስዋዕት ሲሰዋባቸው የነበሩ የተለያዩ አድባራት እና ገዳማት እንዲሁም በውስጣቸው የሚገኙት ንዋተ ቅድሳት ቋሚ ማስረጃዎች መረዳት ይቻላል። ከዚህ መተጨማሪ የሕዝቡ አኗኗር እና ሐይማኖታዊ ባህሉ የኦሪት ዘመን ትላልቅ አሻራዎች ናቸው።
ኢትዮያ ከእስራኤል ጋር በነበራት ጥብቅ ግንኙነት ከሰሎሞን በኋላ የተፃፉትን የነቢያት መፃሕፍት በየጊዜው ተከታትላ በማስገባትና ሁሉም መፃሕፍት ወደ ግዕዝ ቋንቋ ተተርጉመው ሕዝቡ እንዲገለገልባቸው ስታደርግ እና እግዚአብሔር ጋር የነበራትን ጥብቅ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ችላለች። እንዲያውም በአንድ ወቅት ናቡከደነፆር እስራኤልን በማረከ እና ኢየሩሳሌምን ባቃጠላት ጊዜ በእስራኤል የነበሩት ከዚህ ዘመን በፊት የጠፉ የብሉያት መፃሕፍት ምንጭ በመሆን የቅዱሳት መፃሕፍትን መጥፋት ታድጋለች።
ኢትዮያ በነቢያት የተነገረውን እና በብሉያት መፃሕፍት የተፃፈውን የመሲህ ክርስቶስ መምጣት ነቅታ እና ተግታ ተስፋዋን እየተጠባበቀች ሳለ ከብዙ ዘመን በፊት በነበረ የኢትዮያ ንጉስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ገላጭነት ቅድስት ድንግል ማሪያም ከተወደደው ልጇ ጋር ሆኖ የተሰራ ስዕለ አድህኖ ያለበት የኮከብ ቅርፅ ሰርቶ ዓለምን ሊያድን የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ከዚህች ቅድስት ንፅህት ድንግል በሥጋ እነደሚወለድ ለልጆቹ ነግሯቸው። ይህ ትንቢት ሲፈፀም ይህ ኮከብ ካለበት ተነስቶ ብርሃን እያበራ መሲሁ ከተወለደበት ቦታ እንደሚሄድ እና ይህ ክስተት ሲከሰት ተከትለው ሄደው እንዲሰግዱለት እና ግብርም እንዲገብሩለት አደራ ትቶላቸው እንደሞተ እና ይህ አደራ ከልጅ ልጅ እየተላለፈ ጌታችና መድኒታችን በቤተልሔም ከእመቤታችን ሲወለድ የነበረው የኢትዮያ ንጉስ ባዜን የተተወለትን አደራ ተቀብሎ ወርቅ እጣን እና ከርቤ ይዞ ኮከቡን ተከትሎ ወደ ቤተልሔም እንደሄደ በመንገድም ሌሎች የፋርስ እና የባቢሎን ነገስታት አብረውት እንደሄዱ ወንጌልም ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ብሎ ከሚጠራቸው አንዱ የኢትዮያ ንጉስ እንድሆነ ይነገራል።
እንዲሁም በሐዋሪያት ሥራ ላይ እንደተገለጠው የኢትዮያ ንግስት ህንደኬ ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሰግድ እና ሊሳለም እንደሄደ በዚያም በጌታችን ፈቃድ እና በሐዋሪያው በፊሊስ አስተማሪነት እና አጥማቂነት የወንጌል ዜናዋ ወደ ኢትዮያ ጌታችና እና መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአረገ በአስረኛው ቀን እንደተሰበከ እንረዳለን ይህም የቤተክርስቲያን ልደት ተብሎ በሚጠራው እና በሐዋሪያት ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ቀን የኢትዮያ ቤተክርስቲያንም በዚያችው እለት በኢየሩሳሌም በነበረው ጃንደረባዋ ልደቷ ሆነ። ጌታችና መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋሪያትን “እናንተስ እኔ ማን እንደሆንኩ ታላላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ሰዓት ቅዱስ ጥሮስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ የመሰከረውን ቃል ይህ የኢትዮያ ጃንደረባም ፊልስን “እንዳልጠመቅ ምን ይከለክለኛል?” ብሎ ሲጠይቀው “ብታምን ተፈቅዷል” ባለው ጊዜ “ኢየሱስ ክርቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ” በማለት የቅዱስ ጥሮስ መልስ እና እምነት የቤተክርስቲያን መሰረት የሆነ ዐለት እንደሆነ ሁሉ የቅዱስ ጥሮስን እምነት ይህ ጃንደረባ ይዞ በመገኘቱ ለኢትዮያ ቤተክርስቲያን የማይነቃነቅ መሰረት ሆኖ በዚች ቀን የኢትዮያ ቤተክርስቲያንም ተወለደች።
ከቤተ አይሁድ ተለይታ ክርስቶስን በመቀበል እና ከሌሎች በዓለም ላይ ከሚገኙት አቢያተ ክርትያናት ተለይታ ከአምልኮት እግዚአብሔር ወደ አዳም ተስፋ ፍፃሜ ወደ ሆነው ክርስትና ተሸጋገረች። ይህ የወንጌል ዜና በዚህ ጃንደረባ አማካይነት መጀመሪያ ከቤተመንግስቱ ሰዎች ጀምሮ እስከ ተራው ሕዝብ የተዳረሰ ሲሆን በኢትዮያ ወንጌል ተስፋፍቶ መፃሕፍት በስፋት እየተተረጎሙ ትምህርት በስፋት መሰጠት የተጀመረበት እና ሕዝቡ ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ እንዲወለድ ማጥመቅ የተጀመረው በ፬ኛው መ/ክ/ዘመን ሶሪያዊው ቅዱስ ፍሬምናጦስ በቅዱስ አትናቲዎስ እጅ ጵጵስና ተሹሞ ወደ ኢትዮያ በተመለሰ ጊዜ ነበር። ከዚህ ዘመን ጀምሮ ደግሞ የሐዲሳት መፃሕፍት ከተለያዩ ቋንቋዎች ወደ ግዕዝ እየተተረጎሙ በስፋት ትምህርት ለሕዝቡ ሁሉ መሰጠት የተጀመረበት እና ክርስትና ተጠናክሮ የተጀመረበት ነበር።
በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ ከዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮያ መምጣት በኋላ በኢትዮያ የነበረውን ሁኔታ እንመለከታለን።
…ይቀጥላል…

Saturday, June 18, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል ሦስት)

የሮማ ቤተክርስቲያን ውስጣዊ የሐይማኖታዊ የባህል እና የአመለካከት ልዩነትን በውስጧ ከ፮፻ ዓመታት በላይ ስታስተናግድ ኖራ በመጠጨረሻ በላቲን ቋንቋ ተናጋሪ በሆነው የሮማ ምዕራባዊ ቤተክርስቲያን ፓፓ እና የፅርእ ቋንቋ ተናጋሪ የነበረው የምስራቅ የሮማ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በነበረው ፓትሪያርክ እና አንዳንድ የቤተክህነት አለመግባባት እርስ በእርስ ተወጋግዘው ተለያዩ። ሁለቱ ቤተክርስቲያናት ከኦሬንታል ቤተክርስቲያን በብዙ የሚለያዩ ሲሆን እርስ በእርሳቸው ግን ተቀራራቢነት ያላቸው ናቸው።
በአስራስድስተኛው መ/ክ/ዘመን በሮማ ቤተክርስቲያን በነበረው ብልሹ አሰራር እና ስጋዊ አስተሳሰብ ምክንያት ምእመናኑ እና አንዳንድ የመሪነት ደረጃ የተነፈጋቸው ካህናት እና መነኮሳት ባስነሱት ማጉረምረም ሊከሰሰስ እና ሊወቀስ የማይችል ፍፁም ነው ተብሎ በሚታመነው የቤተክርስቲያኒቱ መሪ ፓፓ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ይዞ እንዲነሳ ሉተርን አደፋፈረው።
በእርግጥ ሉተር ባለፈው ክፍል ለመግለጥ እንደተሞከረው እግዚአብሔር በሰጠው አእምሮው ተመራምሮ የሮማ ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን በስጋዊ ሀሳብ እና በፓፓዎቹ ምኞት እና ፈቃድ የምትተዳደር እና መንፈስ ቅዱስ የራቃት መሆኗን ሳይገነዘብ አልቀረም። ነገር ግን ሌላ እርሱ የረሳው ነገር ግን አለ።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሳሪያ በነበረ ጊዜ ሐዋሪያትን ስለራሱ በጠየቃቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ‘ አንተ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” በሎ ሲመልስ ጌታችን የተናገረውን እረስቶታል። ይህም ‘የዮና ልጅ ስምዖን! አንተ ብፁዕ ነህ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጅ ስጋዊ ደማዊ አልገለጠልህም። አንተ መሰረት እንደሆንክ እኔ እነግርሃለሁ፤ በዚያች መሰረት ላይም ቤተክርስቲያኔን እሰራታለሁ፤ የሲኦል በሮችም አይበረቱባትም።” ማቴ. ፲፮ ፥፲፰
ወደሌላ አማራጭ ከመግባቱ በፊት የቤተክርስቲያን እውነት ለዘመናት ሳይቋረጥ እንደ ጅረት ሲፈስ እና ምእመናኑን ሁሉ ሲያጠጣ የሚኖርባት የሲኦል በሮች የማይበረቱባት እውነተኛዋ ሐይማኖት የሮማ ቤተክርስቲያን አለመሆኗን ካረጋገጠ ያች የሲኦል ደጆች ሊያጠፏት የማይቻላቸው ቤተክርስቲያን የት አለች? ብሎ መጠየቅ ነበረበት።እርሷም በወቅቱ በእስክንድሪያ መንበረ ማርቆስ የምትመራው የመጀመሪያው የሐዋሪያት ስብከት ህያው የሆነ ዶግማ እና ቀኖና እንዲሁም ሐይማኖታዊ ባህል ይዛ ለትውልድ ለማስተላለፍ አደራዋን የተወጣች የኦሬንታል ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ናት።
ሉተር ይህንን ነገር ምንም ሊያስበውም የማይፈልግ ነበር። ይህም ምክንያቱ የተለያየ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ እርሱም በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሳይሆን ሳይገባው ገዳማዊ ህይወትን ጀምሮ የምንኩስና ህይወትን የጠላ እና ለስጋዊ ተግባራት ያጋደለ አቋም ስለነበረው ከሞት ክልል እራሱን ነፃ አውጥቶ እንደ አብርሃም እውነትን ፍለጋ እንኳን እስከ መንበረ ፀባኦት ይቅርና ከሰዎች ጠይቆ ለመረዳት እስከ እስክንድሪያ መንበረ ማርቆስ እንኳን ለመገስገስ የሚያግዝ መንፈሳዊ ብርታት አልነበረውም። ስለዚህ በወቅቱ የአውሮፓ መንግስታት በመስቀል ጦርነት ምክንያት ከገቡበት ከፍተኛ ቀውስ ገና ባለማገገማቸው እና ሕዝቡ ሁሉ በዚህ ከፍተኛ የሞራል ኪሳራ በነበረበት ወቅት ውስጥ ስለነበረ የተገኘውን አማራጭ ከመከተል ወደኋላ የማይል እና በሮማ ቤተክርስቲያን ያለአግባብ ብዝበዛ የተሰላቸበት ዘመን ስለነበረ ሉተር ደፍሮ ጣቶቹን በፓፓው እና በከፍተኛ የቤተ ክህነት ሰዎች ላይ ባለ ፺፱ የተቀውሞ ነጥቦችን አንግቦ በመነሳቱ ብዙ ተከታይ በአጭር ጊዜ ሊያፈራ ችሏል
ይህ የሉተር ፍልስፍና መላዋ አውሮፓን አጥለቀለቃት። የተለያዩ የሐይማኖት ዶግማና ቀኖና ያላቸው የፈቃዳቸውን መፈፀም የሚችሉበት አዳዲስ ቤተእምነቶች በለመላው አውሮፓ እንደ አሸን ፈላ። ዛሬ ዛሬ በተለያዩ የዜና ምንጮች እንደምንረዳው ይህ የሉተር የሞት መንገድ በመፅሐፍ ቅዱስ ተለይቶ የተቀመጠን አንድ ሀገር በዲን እሳት እስከመጥፋት ያደረሰ ሐጢያት ሳይቀር ‘በደል ሆይ ወዴት አለሽ?” እያሉ በአሰሳ በመፈለግ የቤተእምነታቸው ስርዓት በማድረግ ላይ ናቸው። የሞት መንገድ መሆኑን እንኳን ሐይማኖተኛ ሰው ይቅርና ማንም ሰው እንከተለዋለን እንረዳዋለን በለው በሚያመካኙት መፅሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ከንቱነታቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። የእነ ሉተር ጅምር በዚህ ብቻ አላበቃም። ብዙ ሰይጣኒዝም (ሰይጣንን ማምለክ) የጀመሩ አቢያተ እምነት መነሻቸው ሉተራዊ አስተሳሰብ እና ከሉተር ልጆች አስተሳሰብ የመነጨ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ አስር ሺ በላይ የሚሆኑ አቢያተ እምነቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከሁለት ሺ ሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት የክርስትና እምነት እና በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የምንመራ ነን ይላሉ። እነዚህም ድርጅቶች የወጡት ከሉተራዊ አስተሳሰብ ሲሆን ይህ የሮማ ቤተክርስቲያን እና ሉተራዊ ቤተእምነት በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ባለመሆናቸው እነዚህን ሁሉ ቤተእምነቶች ወለዱ። ነገር ግን ብዙ ሐይማኖት እንደሌለ በመፅሐፍ ቅዱስ በቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች ፬፥፬ - ፮ ላይም እንደተገለፀው አንድ ጌታ አንዲት ሐይማኖት እና አንዲት ጥምቀት ብቻ እንዳለ እንረዳለን። ይህችም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጌታችን እና የመድኃኒታች የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እና እርሱም የባህርይ አምላክ እመቤታችን ድንግል ማሪያምም ወላዲተ አምላክ እንድሆነች ሐዋሪያት ከጌታችን ተቀብለው የሰበኩትን እና ያስተማሩትን ዶግማውን ቀኖናውን እና ህይወቱንም ጭምር ለዘመናት አሻግራ ለትውልድ ያቆየች ብቸኛዋ የኦሬንታል ቤተክርስቲያን እንደሆነች እናምናለን፤ ከብዙ ታሪካዊ እና ሌሎች የሰው አእምሮ መርምሮ ሊደርስበት የሚችለውን እኛው መርምረን እና ከሰው ህሊና በላይ የሆነውን ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በቅዱሳን አባቶቻችን በኩል ተረድተን መንገዳችን ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም የምታስገባ የጠበበችው መንገድ እንደሆነች እናውቃለን።
ከዚህ በፊት በነበሩን ሦስት ተከታታይ ፅሑፎች የቤተክርስቲያንን ታሪክ እና ውጣ ውረድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአጭሩ ተመልክተናል።
በሚቀጥሉት ተከታታይ ክፍሎች ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያሳለፈቻቸውን የፈተና ዘመናት እና አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንቃኛለን።
…ይቀጥላል…

Saturday, June 11, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል ሁለት)

በእናት ቤተክርስቲያን ከ፷ ዓ.ም እንከ ፫፻፲፪ ዓ.ም ድረስ እጅግ አስከፊ እልቂት እና የስደት ዘመን የነበረ እና እጅግ ብዙ የቤተክርስቲያን ቅርሶች የወደሙበት ቢሆንም በዚህ ዘመን የነበሩት የክርስቲያኖች ሕብረት እጅግ የሚያስቀና አንዱ ሌላውን ለማዳን እራሱን አሳልፎ በመስጠት መድኃኒታችን ክርስቶስን የመሰሉበት የፍቅር ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። ምንም እንኳ በዚህ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በቁጥር አናሳ ቢሆንም ፍሬው ግን ገለባ የሌለበት ንፁሕ እና ሚዛን የሚመታ የክርስትና ሕይወት የታየበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ሊከተለኝ የሚወድ መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ ‘ ብሎ ያዘዘንን ትእዛዝ በተግባር በማሳየት የተለያዩ ሰዎችን ወደ ሕይወት ጎዳና መመለስ ከሚቻልበት ሁኔታ በቀር በመድረክ እና በአደደባባይ ሰላማዊ ስብከት እና ትምህርት መስጠት እጅጉን አሰቸጋሪ የነበረበት ዘመን ነበር።
ይህ ዘመን አልፎ ቤተክርቲያን አንጻራዊ ሰላም ባገኘችበት ዘመን መልኩን ለውጦ የመጣው የዲያብሎስ ውጊያ አርዮሳውያንን አስነስቶ ምናልባትም በዐላውያን መንግስታት ከነበረው የበለጠ በቤተክርስቲያን ላይ ጉዳት አድርሶባታል። የአርዮሳውያን ተንኮል መልኩን እየቀያየረ ቆይቶ ንስጥሮስ ባስነሳው የኑፋቄ ትምህርት ላይ አባቶቻችን በኤፌሶን ተሰብስበው ያወገዙት ቢሆንም ይህንን መሰረት ያደረገ ሌላ የኑፋቄ ትምህርት ለማራመድ የቄልቄዶን ጉባኤ ላይ እራሳቸው ጉባኤ ጠርተው ፍትህ የጠፋበት ርትዕ ሐይማኖት ጠበቃ የነበሩ አባቶቻችን ጥርሳቸው እስኪረግፍ ጺማቸው እስኪነጭ የግፍ ግፍ ተደርጎባቸው የሮማን ንጉሳዊ ቤተሰብ ፍላጎት ያንፀባረቀው እና ይህንን የሮማን ወታደራዊ ኃይል መከታ ያደረገው በሮማ ጳጳስ ሊዮን ትእዛዝ ተደብድበዋል፤ በኋላም ግዞት ቤት ተለይተው እንዲታሰሩ ተደርገው በዚያው በእስር ላይ እንዳሉ አርፈዋል።
በዚህ ጊዜ (፬፻፶፩ ዓ.ም) ነው እንግዲህ ቤተክርስቲያን ለሁለት የተከፈለችው። በሰላሙ ጊዜ የተነሳው የውስጥ ጠላት ቤተክርስቲያንን ለሁለት ከፍሎ የጥፋት ልጆችን መለመለ። በእስክንድሪያ መንበረ ፓትሪያርክ ስር የነበሩት ኦርቶዶክሳዊት እና ርቱዕ የሆነች ሐይማኖትን ፍፁም ተዋህዶን ስትሰብክ የምዕራቡ እና በሮማ መንበረ ፓትሪያርክ በሊዮን ሥር እራሷን ዓለማቀፋዊት ነኝ ለማለት ‘ካቶሊክ” ብላ እራሷን ሰይማ ሁለት ባህርይን መስበክ ጀመረች። ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰዎች ክብር ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደረገ እና ሥጋዊ ፍላጎታቸው ጐልቶ የታየበት ሥርዓትም አረቀቁ።
በዚህ ሁኔታ የሮማ ቤተክርስቲያን ሰባት ዓለማቀፋዊ የቤተክርስቲያን ጉባኤዎች አሉኝ፤ የእምነት መሰረቴ እነዚህን መሰረት ያደረገ ነው ትላለች። ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ቤተክርሰቲያን ከመከፈሏ በፊት አርዮስን፣ መቅዶንዮስን እና ንስጥሮስን ለማውገዝ የተደረጉትንም ይጨምራል። እነዚህ ሦስት ጉባኤዎች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የምትቀበላቸው ብቸኛ ዓለማቀፋዊ ጉባኤዎች ሲሆኑ ከዚያ በኋላ የሮማ ቤተክርስቲያን አራት ዓለማቀፋዊ ጉባኤያት (የውሾች ጉባኤ እየተባለ የሚጠራው የኬልቄዶን ጉባኤን ጨምሮ) አከናውናለች። ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከእነዚህ ጉባኤዎች መካከል ተሳትፎ የነበራት በጉባኤ ኬልቄዶን ብቻ ቢሆንም በዚህ ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቸል ተብሎ የሰዎች የግል ፍላጎት የተነፀባረቀበት እና ፍትህ የተጓደለበት የነገስታቱ ኃይል ተፅእኖ የፈጠረበት የሮማ መንበር የበላይነትን በመንፈስ ቅዱስ ፍቃድ ሳይሆን በንጉሳዊ ቤተሰቦች እና በሮማ የካህናት ቢሮክራሲ ፍላጎት ከእስክንድሪያ መንበረ ማርቆስ ለመንጠቅ የተሞከረበት የሰው አካል እስኪጎድል ድብደባ እና እንግልት የተፈፀመበት በመሆኑ በዚህ ጉባኤ የተከናወኑ ክንውኖችንም ሆነ ውሳኔዎች አትቀበላቸውም። ሌሎቹ ሦስቱ ግን በሮማ በብቸኝነት የተከናወኑ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ የሮም ቤተካህናት እና ንጉሳውያን የፈለጉትን የደነገጉበት በመሆኑ አትቀበለውም።
የሮማ ቤተክርስቲያን የሦስቱን የመጀመሪያ ዓለማቀፋዊ ጉባኤዎች እጋራለሁ ውሳኔዎቹምንም እቀበላለሁ ብትልም ውሳኔዎችን ግን ሽራቸዋለች። በኒቂያ ጉባኤ ሠለስቱ ምእት የወሰኑትን ሐይማኖት የሚጻረር ሐይማኖት ደንግጋቸች። ምንታዌነትን ስርዋፅ አስገብታ የአባቶች ውሳኔ ነው ትላለች። በዚህም ማንም ቀና አእምሮ ያለው ሰው ከ”ሐይማኖቶች” መካከል ትክክለኛውን ምረጥ ቢባል ታሪካዊ አመጣጣቸውን በሚገባ መርምሮ ወጥነት የሌለው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚዋዥቅ ሐይማኖት”ን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚመራ ቀጥተኛ ሐይማኖት አለመሆኑን ጠንቅቆ ይረዳል። ለታረካዊ የቤተክርቲያን የመጀመሪያ የመከፋፈል አደጋን እንዴት እንደነበር በአጭሩ እንዲህ ከተረዳን የሁለቱን ልዩነት በሚገባ ለማሳየት ግን ጊዜ ስለሚያንስ እግዚአብሔር ከፈቀደ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።
በዚህ አኳኋን ቤተክርስቲያን ለሁለት ከተከፋፈለችበት ጊዜ ጀምሮ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ህያው የሆነውን የሐዋሪያት ስብከትን መሰረት ያደረገ እና ሐዋሪያት የሰበሰቧትን ቤተክርስቲያንን ምንም ዝንፍ ሳያደርጉ ጠብቀው በትምህርታቸው በህይወታቸው በተጋድሏቸው እና መፃሕፍትን በመፃፍ እና የተለያዩ የቤተክርስቲያን ሥርዐቶችን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በመሥራት ለትውልደ ትውልድ ሳይቋረጥ ለዘመናት እንደሚፈስ ንፁሕ ወንዝ ከኛ ዘመን አደረሷት።
ይህችን ቀጥተኛ ሐይማኖት ይዘው የሚገኙ አምስቱ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Orthodox Churches) የሚባሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ አርመን፣ ሶሪያ እና ህንድ ናቸው። ነገር ግን ሌሎች የምስራቅ (Eastern Orthodox Churches) የሚባሉም አሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ዶግማና ቀኖና የኛዎቹ (Oriental Orthodox Churches) ቤተክርስቲያናት ከሚከተሉት ዶግማና ቀኖና ይለያል። እነዚህ የምስራቅ (Eastern Orthodox Churches) የሚባሉት ከ፬፻፶፩ ዓ.ም እስከ ፲፻፶፬ ዓ.ም ድረስ በሮማ ቤተክርስቲያን ስር የቆዩ ሲሆኑ በ፲፻፶፬ ዓ.ም ከሮማ ቤተክርስቲያን ተገንጥለው የወጡ ነገር ግን በብዙ የዶግማ እና ቀኖና ይዘታቸው ከሮማ ቤተክርስቲያን ጋር አንድ የሆኑ በጥቂቱ ልዩነት ያላቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው።
በዚህ ሁኔታ በሮማ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ምእመናን እና አንዳንድ ካህናት እንዱሁም መነኮሳት በቤተክርሰቲያኗ ያለውን የሥርዓትና የመሠረተ እምነት ብልሹነት እና አላግባብነት እንዱሁም የጳጳሳቱን የቅንጦት ኑሮ እና የመመለክ አባዜ በመመልከት በተላያየ ጊዜ ከቤተክርስቲያኗ እየተገነጠሉ እነርሱ የመሰላቸውን ሌላ ‘ሐይማኖት” እየደነገጉ ብዙ የጥፋት ልጆችን ልታፈራ ችላለች። በሰው እንጅ በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ባለመሆኗ አንድነቷን አስጠብቃ መቆየት ተሳናት።
ከሮማ ቤተክርስቲያን እንደ አሸን የፈሉ የምንፍቅና ጐራዎችን አወጣጥ በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን።
…ይቀጥላል…

Wednesday, June 8, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አንድ)

በመጀመሪያ ደረጃ ዓለማቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችውን የፈተና እና የመከራ ዘመናት ብንመለከት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን በሥጋ በዚህ ዓለም በተገለጠ ጊዜ ሰይጣን እቡያን በሆኑ በአይሁድ ካህናት እና በፃፎችና ፈሪሳውያን ላይ አድሮ በእግዚአብሔር ቸርነት ለሕዝቡ ሁሉ ሲሰጥ የነበረውን የነፍስ ፈውስ የሆነውን የወንጌል ትምህርት እና የደዌ ሥጋ ፈውስ ደግሞ ተአምራቱን እነዲቃወሙ አደረጋቸው። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ዓለሙን ሁሉ እንዲሁ በመውደዱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ምቀኝነትን ታግሶ ወንጌልን ሰብኮልን በዚህ ዓለም ኑሮው ምሳሌውን ትቶልን መርገመ ሥጋን እና መርገመ ነፍስን በጥምቀቱ እና በሞቶ ድል ነስቶልን በትንሳኤውም ትንሳኤ ሙታንን ተስፋ አስደርጎን ክብርት ቅድስት ድንግል እናቱን እናት አድርጎ ሰጥቶን በሐዋሪያት በኩል ለትውልደ ትውልድ የሚተላለፈውን ሥርዓቱን አስረክቦን በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ።
በዐረገ በአስረኛው ቀንም መቶ ሃያው ቤተሰብ በፅርሃ ፅዮን ተሰብስበው ሳለ መንፈስ ቅዱስ ተልኮ ሐዋሪያትና አርድዕትን በዚያ በማርቆስ እናት ቤት የተሰበሰቡትን ሁሉ የወንጌል ትምህርት ያስተምሩ ዘንድ የበቁ አደረጋቸው። ይህ ቀንም የቤተክርስቲያን የልደት ቀን ተብሎ ይጠራል።
ዓለም መድኃኒቷን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳልተቀበለችው ሁሉ ሐዋሪያትም በወንጌል ትምህርትን በሚያስፋፉበት እና በሚያስተምሩበት አገር ሁሉ ቀና መንገድ አልጠበቃቸውም። ትምህርታቸው በመጀመሪያ በቤተ አይሁድ የተጀመረ ሲሆን ለምቀኝነት እንቅልፍ የማይተኙት አይሁድ የክርስቲያን ማኅበርተኞችን ያገለግሉ ዘንድ ከተሾሙት መካከል ቀዳሜ ሰማእት ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። በሌሎቹም ላይ እስራት ግርፋት እና መከራ አፀኑባቸው።
በዚህ ጊዜ የማኅበሩ አባላት በየቦታው ተሰደዱ። ነገር ግን እነዚህ የተበታተኑት ክርስቲያኖች በየሄዱበት ሁሉ የክርስትናን ትምህርት በደረሱበት ሁሉ አስፋፉት። በዚህ ጊዜም ወንጌል ትምህርት ለዓለም ተዳረሰች።
የቤተክርስቲያን ፈተና ከቤተ አይሁድ የሚመጣ ብቻ አልነበረም። ሐዋሪያት አርድእት እና ሐዋሪያነ አበው በተለያዩ የዓለም ከተሞች እየተዘዋወሩ ክርስትናን ሲያስፋፉ እና ወንጌልን ሲያስተምሩ ጣዖት አምላኪ የነበሩ አሕዛብ እና ዐላውያን ነገስታት በወንጌል መልእክተኞች ላይ ከፍተኛ እና አሰቃቂ የሆነ ስቃይ እና እንግልት አድርሰውባቸዋል። ለጣዖታቱ አገልጋይ የነበሩ ካህናት እና የአሕዛብ ነገስታት ከጣዖታት መስዋእት ከሚገኘው ገቢ የተጠቃሚነታቸው ተግዳሮት የነበረችውን እና ባዕድ አምልኮን እያወገዘች የሰበከችውን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ደፋ ቀና አሉ። ከዘመነ ሐዋሪያት ንጉስ ቆስጠንጢኖስ እስከ ነገሰበት እስከ ፬ኛው መ/ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ቤተክርስቲያን በዋሻ ከመሬት በታች ተወስና እስከ መኖር ያደረሳት ለህሊና እጅግ የሚዘገንን በክርቲያኖች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ እና ዘመቻ በተለያየ መልክ ተካሂዷል።
በዚህ ዘመን ከቤተ አይሁድ እና ከአሕዛብ ና ዐላውያን ነገስታት የሚመጣው ፈተና የቤተክርስቲያ የውጭ ፈተና ሲሆን ቤተክርስቲያን በወቅቱ ውስጣዊ ፈተናም ነበረባት። ከእነዚህም መካከል ከቤተ አይሁድ ወደ ክርስትና የተመለሱት ምእመናን እና ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና የተመለሱት ምእመናን መካከል የተፈጠረው ልዩነት ነው። ከቤተ አይሁድ የመጡት አሕዛብ ሳይገረዙ የቤተክርስቲያን ልጆች መሆን አይገባቸውም በሚል የተነሳው እና የቤተ አይሁድ እና የኦሪት ስርዐት ለማስቀጠል የነበራቸውን ሐሳብ ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና የተመለሱት ምእመናን በመቃወማቸው የከረረ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር። ይህም በሐዋሪያት የመጀመሪያው ሲኖዶስ እልባት ያገኘ ሲሆን ከቤተ አይሁድ የተመለሱት ብዙዎቹ ይህንን የሐዋሪያት ውሳኔ በመቃዎም ከክርስትና የወጡ ነበሩ።
ከዚህ በተጨማሪም የግሪክ የጥንት ፍልስፍና ይዘው የገቡ አንዳድ ወገኖች መዳን በእዉቀት ነው በማለት ግኖስቲዝም የሚባል ይክርስትና ትምህርትን ከግሪክ ፍልስፍና ጋር ያጣመረ አስተሳሰብ ይዘው ብቅ ማለት ሌላው የቤተ ክርስትያን ፈተና ነበር
ቤተ ክርስቲያን የተላዩ ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎችን አሳልፋ ከንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ስትደርስ በአንፃራዊነት ከውጫዊ ፈተና ፋታ ያገኘችበት እና የቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ ዘመን ነበር። በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ከመንግስት ግብር ነጻ የሆነችበት እና ምእመናን በይፋ ክርስቲያናዊ የአምልኮ ስርዐታቸውን በነጻነት ማከናወን የቻሉበት ዘመን ነበር።
በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ውጫዊ ሰላም ብታገኝም ውስጣዊ ፈተናዋ ግን በሰይጣን አቀናባሪነት መልኩን ለውጦ እጅግ በረቀቀ መንገድ ኑፋቄን ይዞ ብቅ አለ። አርዮስ በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ላይ ጥርጥር የሚነዛ ትምህርትን በማስተማር እና በግጥም እና በሌሎች የሥነ-ጽሑፍ መንገዶች በየመንገዱ እና በየአገኘው አጋጣሚ ውሃ ለሚቀዱ ወይዛዝርት እና ቆነጃጅት እንዱሁም ከብት ለሚያግዱ ወጣቶች ህፃናት እና ገበሬዎች ሁሉ እያነበበ እሳስነበበ እንዱሁም በልዩ ልዩ ዜማ እያዜመ የኑፋቄ ትምህርቱን እየነዛ ቤተክርስቲያንን መበጥበጥ ጀመረ። በሦስቱ ምእት ሊቃውንት እና ቅዱሳን አባቶች በጉባኤ ኒቂያ ተመክሮ አልመለስም በማለቱ ተወግዞ ቢለይም ተከታዮቹ ቤተክርቲያንን እንቅልፍ ነስተዋት በቅዱሳን አባቶቻችን ላይ ብዙ መከራ አጽንተውባቸዋል።
የአርዮስ ኑፋቄ በኒቂያ ጉባኤ ተወግዞ ቢለይም ሌሎች አርዮስን ምሳሌ ያደረጉ ልዩ ልዩ የኑፋቄ ሰዎች እርሱን ተከትለው በምስጢረ ስጋዌ እና በመንፈስ ቅዱስ ህልውና ላይ የጥርጥር ትምህርት አስነስተው በተለያዩ ጉባኤዎች አባቶቻችን መክረው አልመለስም በማለታቸው በአንድ ቃል አውግዘው ለይተዋቸዋል። ቤተክርስቲያን እነዚህን መናፍቃን ለማውገዝ እና ሐይማኖትን መሰረት ለመወሰን ያደረገቻቸው ጉባኤያት (ጉባኤ ኒቂያ - አርዮስን ለማውገዝ ጉባኤ ቁስጢንጢንያ - መቅዶንዮስን ለማውገዝ እና ጉባኤ ኤፌሶን - ንስጥሮስን ለማውገዝ) ናቸው። በእነዚህ ጉባኤያት መናፍቃኑን አውግዘው የሐይማኖት መሰረት የሆነውን ጸሎተ ሐይማኖትን ሰርተውልን አልፈዋል።

...ይቀጥላል...

Wednesday, June 1, 2011

ሰው በምድር ሲኖር ሊያተርፍ የሚያቅደው ምንድ ነው?

እነሆ እኔነቴ እና እኔ በየቀኑ በሚኖረን የህይወት ተቃርኖ ጊዜ ሁልዜ አንድ ጥያቄ በአእምሮዬ ይመጣል። ይኸውም ”ሰው በምድር ሲኖር ሊያተርፍ የሚያቅደው ምንድ ነው?‘ የሚል ነው። የማቅደው እና ያቀድኩትን ለማግኘት የማደርገው እየተለያየብኝ።

ሰው በህይወት ዘመኑ ለህይወቱ ጠቃሚ መሆኑን ለይቶ ያልተረዳውን ጠቃሚውንም ጐጅውንም እንዲኖረው ይመኛል፤ ይፀልያልም። ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ነገሮች እንዲኖሩት የሚሻው ለምን እንደሆነ ሲጠየቅ የሚመልሰው መልስ ሁልጊዜ ይገርማል።
ለምሳሌ አንድ ሰው እጅግ ባለፀጋ ሌላው ደግሞ ፈላጭ ቆራጭ መሪ አንዱ ደግሞ እጅግ ሊቅ እና እርሱ የደረሰበት የእውቀት ደረጃ ሌላ የማይደርስበት እና የዓለም ህልውና በእርሱ ክሂሎት እና እውቀት ጥገኛ ወዘተርፈ ሊሆን ይችላል።
ለምን ይህንን እንዲኖርህ ወደድክ ተብሎ ሲጠየቅ በምድር ላይ ጤናማ ደስተኛ እና ምቾት ያለው ህይወት መኖር እንደሚፈልግ እና እነዚህ ነገሮች እርሱ ለእነዚህ ጉዳዮች ማሟያ እንደሚጠቀምባቸው ሳያቅማማ ይናገራል።
ነገር ግን የጤናማ ህይወት ምንጭ ምንድነው? ገንዘብ ነውን? ወይስ ፈላጭ ቆራጭነት ነውን? ወይስ እውቀት ነውን?
የደስታ ምንጭስ ወዴት ነው? ገንዘብ ደስታ ይሆናልን? ስልጣንስ ደስታ ሆይ ወደ እኔ ና! ይለው ዘንድ ይችላልን? ወይስ እውቀት ደስታን በፋብሪካ ሊያመርተው ይችላልን?
የምቾትስ መገኛ ምንድነው? ገንዘብ ወይስ አዛዥነት ወይስ እውቀት?
እነዚህ ደስታ፥ጤናማነት እና ምቾት ምንድናቸው? መገኛቸውስ ምንድነው?
ልዑል እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ሰባት ባህሪያት እንዲኖሩት አድርጎ ነው የፈጠረው። ” ወይቤ ፡ እግዚአብሔር ፡ ንግበር ፡ ሰብአ ፡ በአርአያነ ፡ ወበአምሳሊነ - እግዚአብሔርም፡አለ፦ሰውን፡በመልካችን፡እንደ፡ምሳሌአችን፡እንፍጠር ‘ ዘፍ. ፩፥፳፮ ተብሎ እንደተፃፈ።
አራት ባህሪያተ ሥጋ እና ሦስቱ ባህሪያተ ነፍስ አሉት። አራቱ ባህሪያተ ሥጋ እንስሳትን ሲያስመስሉት ሦስቱ ባህሪያተ ነፍስ ደግሞ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን ያስመስለዋል። ስለዚህ ደስታ ጤናማነት እና ምቾትን ስናስብ ሰው ሁለት ዓይነት ደስታ ጤናማነት እና ምቾትን እናገኛለን። ስጋዊ እና ነፍሳዊ።
የሰው የማስታወስ እና የመናገር የማመዛዘን ችሎታ ከነፍስ ባህሪያት የተገኙ በመሆናቸው ስጋዊ ደስታ ጤናማነት እና ምቾት የስጋ ስሜቶች በመሆናቸው እነዚህ ሲጐድሉ ተመለሶ መጎሳቆሉ አይቀሬ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በብርድ ጊዜ የብርድ መከላከያ እና ምቾት ያላቸው በውድ ዋጋ የተገዙ አልባሳትን ቢለብስ እና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቢራቆት ቀደም ብሎ የለበሰውን ልብስ በማስታወስ መፅናናት ይሳነዋል። ይህ ልብስ የፈጠረው ጊዜያዊ ስሜት ከልብሱ መውለቅ ጋር አብሮ ይጠፋል። ሌሎችም ቁሳዊ በሆኑ ነገሮች ለሰውነታችን የምናደርጋቸው ተግባራት ዘላለማዊ የሆነ ምቾት ደስታ እና ጤናማነት ሊፈጥሩልን አይቻላቸውም።
ሰው ከሌሎች እንስሳት ተለይቶ መናገር (ነባቢነት) ማመዛዘን (ልባዊነት) እና ዘላለማዊ ህይወት (ህያውነት) አለው። በእነዚህ በሦስቱ ባህሪያተ ነፍስ አምላኩ ይመስላል፤ በምድር በስባሽ ፈራሽም ሆኖ አይቀርም። ስለዚህ በእነዚህ በባህሪያተ ነፍሳችን ልንረዳው የምንችለው ነገር ሁሉ ዘላለማዊ ሀብታችን እና ትርፋችን ነው። እንግዲህ እውነተኛ ጤናማነት ደስተኝነት እና ምቾት ከየት ይገኛሉ የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ እነዚህን ነገሮች በባህሪያተ ነፍሳችን እንዴት መረዳት እና ለባህሪያተ ነፍሳችን ገንዘብ ማድረግ እንችላለን ወደሚል ጥያቄ መቀልበስ እንችላለን። ምክንያቱም በነፍስ ባህሪያት ልንገነዘበው እና ልናጣጥመው የምንችለው ነገር ለዘለቄታው አብሮን የሚኖር በመሆኑ ነው።
ለምሳሌ ደስተኝነትን እንመልከት። አንድ ሰው ደስታን በቁሳዊ ነገሮች በገንዘብ እና በመሳሰሉት ነገሮች ማግኘት አይችልም። ቢገኝም ስጋዊ ባህሪያችን ብቻ የሚያጣጥመው ያ አስገኚው ሲጠፋ አብሮ የሚጠፋ ጊዜያዊ ስሜት ብቻ ነው የሚሆነው። ነገር ግን አንድ ሰው በአእምሮው ውስጥ ደስታ እና እርካታን የሚፈጥረው መልካም ሀሳብን ለአእምሮው ሲመግበው ነው። መልካም ሀሳብ እና መልካም ሥራ የአእምሮ ምግቦች ናቸው። እነዚህ መልካም ሀሳቦች እና ሥራዎች የሚገኙት ደግሞ ለሰው ሁሉ ቅን እና ደግ በመሆን ነው። ቅንነት እና ደግነት ደግሞ ከፍቅር የሚመነጩ ናቸው። ለማይወደድ ሰው ቅን እና ደግ መሆን ከቶ ከባድ ነው።
አንድ ሰው ሁልጊዜ አብሮት የሚኖር የልብ መረጋጋት እና ደስታን ገንዘብ ለማድረግ ሰውን ሁሉ እንዲሁ መውደድ ነው። ጠላቱን እንደራሱ አድርጎ የሚወድ ልብ ደስታ ዘላለማዊ ነው። በራሱ ላይ ባለድል ነውና። ሰውን ሁሉ ለመውደድ እራስን ማሸነፍ ትህትናን መልመድ እና መንፈሳዊ አባቶቻችን ታሪክ እኛም እንደ አቅማችን መለማመድ ያስፈልገናል።
ሰው ለባዊ ፍጡር በመሆኑ ከራሱ ስህተት የተነሳ የሚመጣበትን የአእምሮው ትችት መሸሽ ከቶ አይቻለውም። እግዚአብሔር እኛን ለባዊ አድርጎ ሲፈጥረን አእምሮን ያህል ርቱዕ ዳኛ በላያችን ሾሞብናል። እናም በጨለማ ተጋርዶ በስውር መጥፎ ሥራ በመስራት ብዙ ሀብት ብናፈራ በሰዎች ላይም ግፍ ብናበዛ ከእግዚአብሔር እና ከአእምሯችን ልናመልጥ አይቻለንም። ስለሆነም ሞልቶ በተረፈው ቤታችን ብቸኛ ሐዘንተኛ እንሆናለን።
ሌሎች የህይወት እሴቶችም ከዚህ ተለይተው የሚታዩ አይደሉም። ለስጋ ብቻ የሚመች ነገር ግን ለባህሪያዊ ነፍሳችን የማይመች ስራ ብንሰራ ስጋ የተደረገለትን ሁሉ በአጭር ጊዜ ረስቶ ለነፍስ ወቀሳ አሳልፎ ይሰጠናል። ምቾትም ሆነ ጤናማነት ሁሉም ከልብ ይመነጫሉ። በጐ ሥራ በመስራት በልቡ ሀሴት የሞላ ሰው አስጨናቂ ጉዳይ የለበትም። ጭንቀት ከሌለበት ደግሞ ሙሉ ሰውነቱ ጤናማ ይሆናል። ጤናማ ሰውነት ደግሞ ሁልጊዜ ምቾት ይሰማዋል። ”እነደ ንፁህ ህሊና የሚመች ትራስ አይገኝም!‘ አይደል የሚሉት አበው። ምንም ጥርጥር የለውም፤ ውስጣዊ ሰላም ከአፍኣ (ውጫዊ) ምቾት እጅጉን ይበልጣል። ምክንያቱ ደግሞ አፍአዊ ደስታን በስጋችን ውስጣዊ ደስታችንን ደግሞ በልባችን (በነፍሳችን) እንገነዘበዋለንና ነው።
እንግዲህ አንባቢ ሆይ! በምድራዊ ህይወትህ/ሽ ደስታን ምቾትን ጤናማነት እና የህሊና እርካታን ለማትረፍ ካቀድህ/ሽ የሚከተሉትን መመሪያዎች ተግብር/ሪ፦
፩ኛ. ፈጣሪህ/ሽ እግዚአብሔርን ውደደው/ጂው፤ ባለህ/ሽ ጊዜ ሁሉ እርሱ የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ የከፈለውን መስዋእትነት እና ላንተ/ቺ ያለውን ፍቅር አስብ/ቢ። በዙሪያህ/ሽ ያሉት በህይወት እንድትኖር/ሪ ያደረጉህ/ሽ ነገሮች ሁሉ የእርሱ ሀብቶች ሲሆኑ ያለምንም ዋጋ እንደሰጠህ/ሽ አስታውስ/ሽ።
፪ኛ.ሰውን ሁሉ እንዱሁ ውደደው/ጂው፤ አንተ/ቺ ለሰው ስለምታደርገው/ጊው ውለታ እና በጎ ሥራ አቅድ/ጅ እንጅ የማንኛውንም ሰው ስጦታ ተስፋ አታድርግ/ጊ። ስጦታውን ሳታገኝ ብትቀር/ሪ የኑሮህ/ሽ ዋጋ ምንጭ የሆነውን ለዚያ ሰው ያለህን/ሽን ፍቅር ያቀዘቅዝብሃልና/ብሻልና። በምንም ዓይነት መንገድ ለራስህ/ሽ አታዳላ/ይ።
፫ኛ. ቁሳዊ ነገሮችን አብዝተህ/ሽ አትመኝ፤ ከማንኛውም ሰው ወይም ከፈጣሪህ/ሽ ይልቅ ለእነዚህ ቁሳዊ ነገሮች የበለጠ ፍቅር እንዳይኖርህ/ሽ እራስህን/ሽን በየጊዜው መርምር።
፬ኛ. ሁል ጊዜ አእምሮህን/ሽን በማይጠቅም ሐሳብ እንዳይባዝን እራስህን/ሽን በጸሎት እና በሥራ ባተሌ አድርግ/ጊ። በተግባር የሚለወጥ ሐሳባ ቢኖርህ/ሽ በእቅድህ/ሽ ውስጥ ፃፈው እንጅ በበጐ አስጀምሮ የተከተልከው/ሽው ሐሳብ መንታው እየበዛ ህልም ከሚመስል ቅዠት ውስጥ እንዳያስገባህ/ሽ የሞት እናት የሆነውንም ሐጢያት ጣዕም አጉልቶ እንዳያሳይህ/ሽ።
፭ኛ. መንፈሳዊነት እንደ ክሂሎት የሚዳብር ነው፤ እናም ተለማመደው/ጂው። ቁጣን ለማስወገድ፥ ትሁት እና ታጋሽ ለመሆን፥ የአፍህ/ሽ ቃላት ቅንነት እና መልካምነትን የሚያሰዩ ቁጣን የሚያበርዱ እንዲሆኑ፥ፍቅር እና ሌሎች የመንፈስ ፍሬዎች ገንዘብህ/ሽ እንዲሆኑ ተለማመድ/ጅ።
፮ኛ. ቅዱሳት መፃሕፍትን በየጊዜው አንብብ/ቢ፤ መልካም የሆነውን ሁሉ ለመረዳት ልብንም በሐይማኖት ለማቅናት ያስፈልጉሀልና/ሻልና። የዘነጋኸውን/ሽውን ለማስታወስ በቀዘቀዝክበት/ሽበት ነገር ለመነቃቃት ያገለግሉሃል/ሻል።
፯ኛ. ስንፍናን አስወግድ/ጅ፤ ለሥጋ ምግብነት የሚጠቅሙህ/ሽ እና በጐ ሥራ ለመስራት የሚያገለግሉህ/ሽ ነገሮችን ለማሟላት ተግተህ/ሽ ሥራ/ሪ። ነገር ግን ይህንን ምክንያት አስደርጐ የሚበልጥ ዋጋ እንዳያሳጣህ/ሽ ተጠንቀቅ/ቂ። ጸሎትህን/ሽን እንዳያታጉልብህ/ሽ፤ ከሌሎች ይልቅ ለራስህ/ሽ መድሎን እንዳያስደርግህ/ሽ፤ መልካም ሥራን እሰራለሁ አስብሎ መበደልን እንዳያስለምድህ/ሽ እራስህን/ሽን ጠብቀው/ቂው።
እንዲህ ያለ የፍቅር ህይወት ኖረህ/ሽ እየው/ይው። በህይወት ዘመንህ/ሽ ሁሉ ልታተርፈው/ፊው ያቀድኸውን/ሽውን ሁሉ ታገኛለህ/ሽ።