የሮማ ቤተክርስቲያን ውስጣዊ የሐይማኖታዊ የባህል እና የአመለካከት ልዩነትን በውስጧ ከ፮፻ ዓመታት በላይ ስታስተናግድ ኖራ በመጠጨረሻ በላቲን ቋንቋ ተናጋሪ በሆነው የሮማ ምዕራባዊ ቤተክርስቲያን ፓፓ እና የፅርእ ቋንቋ ተናጋሪ የነበረው የምስራቅ የሮማ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በነበረው ፓትሪያርክ እና አንዳንድ የቤተክህነት አለመግባባት እርስ በእርስ ተወጋግዘው ተለያዩ። ሁለቱ ቤተክርስቲያናት ከኦሬንታል ቤተክርስቲያን በብዙ የሚለያዩ ሲሆን እርስ በእርሳቸው ግን ተቀራራቢነት ያላቸው ናቸው።
በአስራስድስተኛው መ/ክ/ዘመን በሮማ ቤተክርስቲያን በነበረው ብልሹ አሰራር እና ስጋዊ አስተሳሰብ ምክንያት ምእመናኑ እና አንዳንድ የመሪነት ደረጃ የተነፈጋቸው ካህናት እና መነኮሳት ባስነሱት ማጉረምረም ሊከሰሰስ እና ሊወቀስ የማይችል ፍፁም ነው ተብሎ በሚታመነው የቤተክርስቲያኒቱ መሪ ፓፓ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ይዞ እንዲነሳ ሉተርን አደፋፈረው።
በእርግጥ ሉተር ባለፈው ክፍል ለመግለጥ እንደተሞከረው እግዚአብሔር በሰጠው አእምሮው ተመራምሮ የሮማ ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን በስጋዊ ሀሳብ እና በፓፓዎቹ ምኞት እና ፈቃድ የምትተዳደር እና መንፈስ ቅዱስ የራቃት መሆኗን ሳይገነዘብ አልቀረም። ነገር ግን ሌላ እርሱ የረሳው ነገር ግን አለ።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሳሪያ በነበረ ጊዜ ሐዋሪያትን ስለራሱ በጠየቃቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ‘” አንተ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” በሎ ሲመልስ ጌታችን የተናገረውን እረስቶታል። ይህም ‘” የዮና ልጅ ስምዖን! አንተ ብፁዕ ነህ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጅ ስጋዊ ደማዊ አልገለጠልህም። አንተ መሰረት እንደሆንክ እኔ እነግርሃለሁ፤ በዚያች መሰረት ላይም ቤተክርስቲያኔን እሰራታለሁ፤ የሲኦል በሮችም አይበረቱባትም።” ማቴ. ፲፮ ፥፲፰
ወደሌላ አማራጭ ከመግባቱ በፊት የቤተክርስቲያን እውነት ለዘመናት ሳይቋረጥ እንደ ጅረት ሲፈስ እና ምእመናኑን ሁሉ ሲያጠጣ የሚኖርባት የሲኦል በሮች የማይበረቱባት እውነተኛዋ ሐይማኖት የሮማ ቤተክርስቲያን አለመሆኗን ካረጋገጠ ያች የሲኦል ደጆች ሊያጠፏት የማይቻላቸው ቤተክርስቲያን የት አለች? ብሎ መጠየቅ ነበረበት።እርሷም በወቅቱ በእስክንድሪያ መንበረ ማርቆስ የምትመራው የመጀመሪያው የሐዋሪያት ስብከት ህያው የሆነ ዶግማ እና ቀኖና እንዲሁም ሐይማኖታዊ ባህል ይዛ ለትውልድ ለማስተላለፍ አደራዋን የተወጣች የኦሬንታል ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ናት።
ሉተር ይህንን ነገር ምንም ሊያስበውም የማይፈልግ ነበር። ይህም ምክንያቱ የተለያየ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ እርሱም በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሳይሆን ሳይገባው ገዳማዊ ህይወትን ጀምሮ የምንኩስና ህይወትን የጠላ እና ለስጋዊ ተግባራት ያጋደለ አቋም ስለነበረው ከሞት ክልል እራሱን ነፃ አውጥቶ እንደ አብርሃም እውነትን ፍለጋ እንኳን እስከ መንበረ ፀባኦት ይቅርና ከሰዎች ጠይቆ ለመረዳት እስከ እስክንድሪያ መንበረ ማርቆስ እንኳን ለመገስገስ የሚያግዝ መንፈሳዊ ብርታት አልነበረውም። ስለዚህ በወቅቱ የአውሮፓ መንግስታት በመስቀል ጦርነት ምክንያት ከገቡበት ከፍተኛ ቀውስ ገና ባለማገገማቸው እና ሕዝቡ ሁሉ በዚህ ከፍተኛ የሞራል ኪሳራ በነበረበት ወቅት ውስጥ ስለነበረ የተገኘውን አማራጭ ከመከተል ወደኋላ የማይል እና በሮማ ቤተክርስቲያን ያለአግባብ ብዝበዛ የተሰላቸበት ዘመን ስለነበረ ሉተር ደፍሮ ጣቶቹን በፓፓው እና በከፍተኛ የቤተ ክህነት ሰዎች ላይ ባለ ፺፱ የተቀውሞ ነጥቦችን አንግቦ በመነሳቱ ብዙ ተከታይ በአጭር ጊዜ ሊያፈራ ችሏል።
ይህ የሉተር ፍልስፍና መላዋ አውሮፓን አጥለቀለቃት። የተለያዩ የሐይማኖት ዶግማና ቀኖና ያላቸው የፈቃዳቸውን መፈፀም የሚችሉበት አዳዲስ ቤተእምነቶች በለመላው አውሮፓ እንደ አሸን ፈላ። ዛሬ ዛሬ በተለያዩ የዜና ምንጮች እንደምንረዳው ይህ የሉተር የሞት መንገድ በመፅሐፍ ቅዱስ ተለይቶ የተቀመጠን አንድ ሀገር በዲን እሳት እስከመጥፋት ያደረሰ ሐጢያት ሳይቀር ‘በደል ሆይ ወዴት አለሽ?” እያሉ በአሰሳ በመፈለግ የቤተእምነታቸው ስርዓት በማድረግ ላይ ናቸው። የሞት መንገድ መሆኑን እንኳን ሐይማኖተኛ ሰው ይቅርና ማንም ሰው እንከተለዋለን እንረዳዋለን በለው በሚያመካኙት መፅሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ከንቱነታቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። የእነ ሉተር ጅምር በዚህ ብቻ አላበቃም። ብዙ ሰይጣኒዝም (ሰይጣንን ማምለክ) የጀመሩ አቢያተ እምነት መነሻቸው ሉተራዊ አስተሳሰብ እና ከሉተር ልጆች አስተሳሰብ የመነጨ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ አስር ሺ በላይ የሚሆኑ አቢያተ እምነቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከሁለት ሺ ሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት የክርስትና እምነት እና በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የምንመራ ነን ይላሉ። እነዚህም ድርጅቶች የወጡት ከሉተራዊ አስተሳሰብ ሲሆን ይህ የሮማ ቤተክርስቲያን እና ሉተራዊ ቤተእምነት በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ባለመሆናቸው እነዚህን ሁሉ ቤተእምነቶች ወለዱ። ነገር ግን ብዙ ሐይማኖት እንደሌለ በመፅሐፍ ቅዱስ በቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች ፬፥፬ - ፮ ላይም እንደተገለፀው አንድ ጌታ አንዲት ሐይማኖት እና አንዲት ጥምቀት ብቻ እንዳለ እንረዳለን። ይህችም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጌታችን እና የመድኃኒታች የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እና እርሱም የባህርይ አምላክ እመቤታችን ድንግል ማሪያምም ወላዲተ አምላክ እንድሆነች ሐዋሪያት ከጌታችን ተቀብለው የሰበኩትን እና ያስተማሩትን ዶግማውን ቀኖናውን እና ህይወቱንም ጭምር ለዘመናት አሻግራ ለትውልድ ያቆየች ብቸኛዋ የኦሬንታል ቤተክርስቲያን እንደሆነች እናምናለን፤ ከብዙ ታሪካዊ እና ሌሎች የሰው አእምሮ መርምሮ ሊደርስበት የሚችለውን እኛው መርምረን እና ከሰው ህሊና በላይ የሆነውን ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በቅዱሳን አባቶቻችን በኩል ተረድተን መንገዳችን ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም የምታስገባ የጠበበችው መንገድ እንደሆነች እናውቃለን።
ከዚህ በፊት በነበሩን ሦስት ተከታታይ ፅሑፎች የቤተክርስቲያንን ታሪክ እና ውጣ ውረድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአጭሩ ተመልክተናል።
በሚቀጥሉት ተከታታይ ክፍሎች ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያሳለፈቻቸውን የፈተና ዘመናት እና አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንቃኛለን።
…ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment