Saturday, October 9, 2010

እነሆ ስንዱ እግዚአብሔር ያቀረበውን የምድር በረከቶች ተጠቅመሽ እግዚአብሔር የሰጠሽን እጅ አንቀሳቅሰሽ ፣ እግዚአብሔር በሰጠሽ አእምሮ አስበሽ ሠርተሽ ...... አግኝተሻልና እግዚአብሔርን አመስግኚ።


አንድ ጎደኛዬ በቅዱስ ላሊበላ ሥዕላት ያጌጤ መድሃፍ፤ በገጹ መሃል ላይ በቢጫ መደብ በጥቁር ቀለም "መጽሃፈ ብልሃት" ተብሎ የተጻፈበት መጽሃፍ ይዞ አየሁኝና መጽሃፉን ተውሼ ማንበብ ጀመርኩኝ።መጽሃፉ በሙሉጌታ ዘርፈ የተጻፈ ነው።ርዕሱ አትኩሮቴን ስቦታል ማንም ሰው ብልሃትን ማግኘት የሚጠላ የለምና ። መጽሃፉን ማንብብ ቀጥያለሁኝ። መጽሃፉ ለዝግጁዋ ስንዱ የተጻፈ ነው።ማን ናት ይህች ዝግጁዋ ስንዱ?ዝግጁዋን ለመሆንስ ምን ያስፈልጋል?አእምሮዬ ውስጤን ጠየቀው ምልሱንም የማወቅ ጉጉቴ ይበልጥ ጨመረ።የመጀመሪያው ገጽ ላይ ደመቅ ብሎ ጠቆር ባለ ቀለም "እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው" ይሚለው ጥቅስ ተጽፎል ።ማንበቤን አላቆረጥኩም መግቢያውን እንደሚከተለው አነበብኩት።
መግቢያ
ሰው በኑሮው እግዚአብሔርን ሲለምን መልካም ነው።ሰዎች በውድቀት ያልሆኑት ነገር የለም። ሰው በኑሮው ሰውን ሲለምን መልካም አይደለም።አንዲት አገር ስለኑሮዋ እግዚአብሔርን ስትለምን ትባረካለች፤ሌላ አገርን ስትለምን ወድቃለች።ኢትዮጵያን ምን ነካት? ምነው ሰዎቿስ በደዌ የተጠቁ፣ በግብጽ መቅሰፍት የተቀሰፉ፣ቀን እንደጨለማ ሆኖባቸው የሚዳብሱ፣ የሰባውን በሬያቸውን ብልት ያጡ ፣ሰማይ ሊወድቅባቸው ያንዣበበባቸው ውንዞችም የደረቁባቸው ሆኑ? ለዚህ ጥያቄ መልሱ የተሰጠው የዛሬ ሶስት ሺህ አመት ነው። ኢትዮጵያ ከውደቀችበት ልትነሳ ትችላለችን? አዎን ትችላለች፣ ለዚህም መልሱ የተሰጠው የዛሬ ሶስት ሺህ አመት ነው።ካለፉት 150 አመታት ወዲህ የኢትዮጲያ ሰዎች በውድቀት ያልሆኑት ነገር የለም ።ከዚህ ውድቀቶች ውስጥ አንዱ ሌላው ዓለም የሚያውቀው የእደጥበብ ሥራ ለነሱ እንቆቅልሽ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ስዎች ልብስ በመርፌ ይሰፋሉ፤ መርፌውን መስራት ግን አይችሉም። በድምጽ ማጉያ ይናገራሉ ፤ድምጽ ማጉያውን መስራት አይችሉም። መኪና ይነዳሉ፤ መኪና መስራት አይችሉም። በአውሮፕላን ይበራሉ፤ አውሮፕላን መሥራት አይችሉም። ብረት ይቀጠቅጣሉ በረት አያቀልጡም። አያቶቻቸው ያውቁት የነበረው ሙያ እንኳን ለልጆቹ እንግዳ ነው። የአክሱምን ሃውልቶች የሠሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው። አሁን ያሉት ኢትዮጵያውያን ናቸው። አሁን ያሉት ኢትዮጵያውያን ምን እንደሆነ አያውቁትም። እንደ ገንዳ ተፈልፍለው የተሠሩ የአክሱም ንጉሦች የሚቀበሩበትን የሚያሰደንቁ ድንጋዮች የገጠሙ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ አሁን ያሉት ኢትዮጵያውያን ድንጋዮቹ እንዴት እንደተሰሩ፤እንዴት እንደተገጠሙም አያውቁም።

ይልቁንስ የውጭ አግር ሰዎችን ምን እንደሆነ ንገሩን እያሉ ይለምናሉ።በላሊበላ የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአንድ አለት ፈልፍለው የሠሩ ኢትዮጲያውያን ናቸው፤ አሁን ያሉ የኢትዮጲያ ሰዎች የውጭ አገር ሰዎችን እባካችሁ አባቶቻችን የሠሩት ምን እንደሆነ ማዎቅ የሚያስችል አእምሮ የለንምና ኑ ንገሩን እያሉ ይማጸናሉ።
አባቶቻቸው የሚያስቡ የነበሩ የአሁኖቹ የኢትዮጲያ ሰዎች ምን ተወሰደባቸውና ማሰብ አቆሙ?አንድ ሰው ወላጆቹ የተውለትን ቅርስ በዓይኑ እያየ ምን እንደሆነ የማያውቅበት ምክነያት ምንድን ነው? ለመሆኑ የኢትዮጲያ ሰዎች ሰፈራቸውን ውብ አድርገው መያዝስ ለምን ተሳናቸው?ሠርተው የሚበሉት ነገር ማግኘትስ ለምን አቃታቸው?እያልኩ ሳመላልስ ፣አእምሮየም እረፍት ስላጣ ፣ የችግሩን መንሰዔና መፍተሄ አውቅ ዘንድ፣የሰሎሞንን ያህል ባይሆንም ከሰው ደረጃ በታች ለወደቁት ኢትዮጲያውያን ወገኖቼ ትርፍ የሚሆን ጥበብን እንዲያድለኝ እግዚአብሔርን ለመንኩት።ሰማኝም። የእሳት ልጆች አመድ የሆኑበት የምክነያት ጎርፍ እየጠራ ይታየኝ ጀመር።
ኢትዮጲያውያውን እንኳን ሌላ ወላጆቻቸው የተውላቸው ቅርሶች ምን እንደሆኑ ማዎቅ እስኪሳናቸው ድረስ የወደቁበት ምክነያት ብዙ ነው።በአስኳላ ትምህርት የሰለጠኑ ሰዎች የኢትዮጲያ ችግሮች ምንጮች ናቸው ብለው የሚዘረዝሯቸው ነጥቦች ከምክነያቶቹ ውስጥ የሉበትም።እንዲያውም ከምክነያቶቹ ውስጥ ዋነኛውም ባይሆን አንደኛው የአስኳላ ትምህርት አሰጣጥ ዘዴ እና የትምህርቱ ዓይነት እራሱ ነው።የአስኳላ ትምህርት እውቀት የሚገኝበት ቢመስልም እውቀት እራሱ በአስኳላ ትምህርት ሊደበቅ እንደሚችል የኢትዮጲያ ሰዎች ማስተዋል አለባቸው።

ስለኤሌትርክ ትምህርት ወይም ደግሞ ስለ ግድብና ተርባይን የሚማር ሰው በኢትዮጲያ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ብዙ ሂሳብና ቲዮሪዎችን ይማራል።ብዙ የሂሳብ ልምምድና የሳይንስ ቃላቶችን በማዝጎድጎድ ትምህርቱን አጠናቀቀ ተብሎ የሚደገስለት ተማሪ ዋናውን ቁምነገር እሱም ኤሌትሪክ እንዴት እንደሚመነጭ የምትገልጸውን ቁልፍ ሚስጢር ወይም ብልት ሳያውቅ ነው።በኢትዮጵያ የአስኳላ ትምህርት የሚማሩ ሰዎች ከትምህርቱ ለኢትዮጵያ የሚአጠቅመውን ብልት ሳያገኙ እንዲያው ትርፍና ፍሬ በማያስገኙ ዲስኩሮች ጊዜያቸውን ይገፋሉ።በዲስኩሮች ብዛትም ለእድገት ቁልፍ የሆነችው ብልት ከነሱ ትደበቃለች።በኢትዮጲያ የአስኳላ ትምህርት የላይኛው ጣራ ድረስ ሳይቀር የተማሩት ሁሉም ባይሆኑ ኣብዛኞቹ ከትምህርቱ ያገኙት የጋራ ሙያ ቢኖር ለትችት ችኩልነት ፣ ለሙያ ስንኩልነትን ነው።በዚህም ምክነያት ሥራ ሲሰሩ አይታዩም።ሌሎችንም እንዳይሰሩ የሚያደርጉበት ብዙ አመል አብቅለዋል።የተሠራ እንኳን ቢገኝ ለወገናቸው ጥቅምን ሳያስገኙ ያባክኑታል።ያለፈትን አርባ አመታት ታሪክ እንኳን በመቃኜት ያስኳላ ትምህርትን የቀሰሙ የኢትዮጲያ ሰዎች በያሉበት ስለአመጽ የሚሰለፍ፣ስለምርት የሚያንቀላፋ መሆናቸውን ማየት ይቻላል።ይህ ወቀሳ አይደለም።እነዚህ ሰዎች የተማሩትን ሆኑ እንጂ በራሳቸው አላጠፈም።መፍትሄው ያለው ትምህርቱን ከማስተካከል ነው።የዚህ መጽሐፍ ዓላማም ይህ ነው።
የዚህ የአንደኛ መጽሐፍና የሚከተሉት መጻሕፍቶች ዓላማ የኢትዮጲያ ሰዎች ከልጅነታቸው ጅምሮ በሙያና እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲያድጉ ማድረግ ነው።ከሙያ ውስጥ እግዚአብሔርን መፍራት ከጎደለ ሙያው ለጥፋት ይውላልና ሙያ እግዚአሔርን ከመፍራት አንድም ጊዜ ሊነጠል አይገባውም፡፡ሙያ ደግሞ ሥራ ነው እንጂ ሌሎች ሰዎች ሲሰሩ ማየት አይደለም።የኢትዮጵያ ልጆች እንደ ዳዊት በገና እንዲደረድሩ ማድረግ ነው።ይህ መጽሐፍ የተለያዩ በውጭ አገር የሚሠሩ፤ ኢትዮጵያውያን ግን ሊሠሯቸው እንግዳ የሆኑባቸውን የሙያ ውጤቶች የአሠራር ብልሃት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊገባው በሚችል መንገድ አቅርቧል።እነዚህ ብልሃቶች በትምህርት ቤቶች በትምህርት እንዲሰጡና የኢትዮጲያ ሰዎችም በየቤታቸው እንዲሰሯቸውና እንዲገለገሉባቸው ወይም ለገበያ እንዲያቀርቧቸው ነው።በኢትዮጵያ አንድ ልጅ ቢያንስ በሰባት ዓመቱ አከባቢውን ማጽዳትን፣ በአሥር ዓመቱ ራዲዮን መሥራትን፣በአስራ አራት አመቱ የዉኃ ማጣሪያ መሥራትን ፣በአስራ ስድስት አመቱ ሞፈርና ቀንበርን አሻሽሎ ማረስን፣በአስራ ስምንት አመቱ ሰረገላ መሥራትን በግብር ማሳየት አለበት።የሙያዎቹ አይነቶች ይለያዩ እንጂ፣የኃላ ኃላ አንድም ሳይቀር እያንዳንዱን ኢትዮጲያዊ ሰዎች የሙያ ባለቤት ማድረግ ነውና የእግዚአብሔር እርዳታ ይጨመርበት።



መግቢያውን እንደጨረስኩኝ በቀጥታ ደራሲው ማን ነው?የሚል ጥያቄ አእምሮዬ ውስጥ ስለተፈጠረብኝ ስለደራሲው ማንነት ማገላበጥ ጀመርኩኝ።ስለ ደራሲው በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ይህንን አገኘሁኝ።
“ ሰለ ደራሲው
ደራሲው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምሕንድስና ሙያ ሰልጥኖ በኢትዮጵያ በመሐንድስነት ሲሰራ ከቆየ በኃላ ወደ አሜሪካን አገር በመሄድ በሳንታ ክላራ ዩኒቨርሲቲ የመግነጢስ አዘጋገብ ምሕንድስና ትምህርትን እንዲሁም የምርምር ሥራ ንድፍና ሂሳባዊ ትንታኔ ትምህርትን ተምሯል።ከዚህም በኃላ በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በምሕንድስና አመራር ሙያ ሰልጥኗል።ላለፈት አስራ ሰባት አመታትም በልዩ ልዩ የረቂቅ ቴክኖሎጂ ኩባንያወች ውስጥ በምርምር መሐንዲስነት፣በዋና መሐንዲስነት እና በከፍተኛ የምርምር መሐንዲስነት ሲሰራ ቆይቷል።በትርፍ ጊዜ ትምህርትም በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የንድፍ ሃሳባዊ ፊዚክስ ትምህርትን ተምሯል።ደራሲው የአራት የረቂቅ ቴክኖሎጂ ግኚቶች ባለቤት ሲሆን የግኚቶቹም ህጋዊ መረጃዎች ወይም ፓተንቶች በአሜሪካ የፓተንት ድርጅትና በዓለም አቀፍ የምሁራን ንብረት ድርጅት በዚህ መጽሐፍ ደራሲ ስም ሰፍረዋል።”

ሙሉ መጽሐፉን ካነበብኩኝ በኃላ ብዙ ነገሮችን በውስጤ አሰብኩኝ አሰላሰልኩኝ ቀለል ባለ መንገድ ብዙ ቁምነገሮችን ያስጬብጣል። በተለየ መልኩ "....እነሆ ስንዱ እግዚአብሔር ያቀረበውን የምድር በረከቶች ተጠቅመሽ እግዚአብሔር የሰጠሽን እጅ አንቀሳቅሰሽ ፣ እግዚአብሔር በሰጠሽ አእምሮ አስበሽ ሠርተሽ ...... አግኝተሻልና እግዚአብሔርን አመስግኚ።" የሚለው ቃል በአእምሮዮ እስካሁን ያቃጭላል።….
አንባቢያን መጽሃፉ በጣም ጠቃሚና አስተማሪ ስለሆነ ገዝታችሁ እንድታነቡት በአክብሮት እጋብዛለሁኝ።
መልካም ንባብ።