Tuesday, May 22, 2012

ቅድስት ድንግል ማሪያም በነገረ ድህነት (ክፍል ሁለት)


ባለፈው ክፍል ለመመልከት እንደሞከርነው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን በመበደል ከገነት እንደተሰደደ እና በዚህም ተፀፅቶ ንስሃ ቢገባ ቸር የሆነ አምላክ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደገባለት ከድንግል ማሪያምም ተወልዶ እንደሚያደነው ለማየት ሞክረናል፡፡
እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆኖ የጠፋውን ሰው ለማዳን ወደደ?
የሰው ልጅ መጀመሪያ ላይ አምላክ ለመሆን በመሻት ዕፀ-በለስን በመብላት እግዚአብሔርን መበደሉ እና የዚች ሀጢያት በዘር የምትተላለፍ መሆን ሁሉም የሰው ልጅ ሞትን በዘር የሚወርሳት ሆነ፡፡ ይህም የቀደመው በደላችን (ጥንተ አብሶ) ሁላችንም በአዳምና ሔዋን አብራክ ሆነን የበደልን በመሆናችን ነው፡፡ የሰው ልጅ አምላኩን በመበደሉ በዳዩ ተበዳዩን ካሳ መካስ እና የጥልን ግድግዳ ማፍረስ ርቱዕ ፍርድ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበርና ሰው እንደበደለ ሰው መካስ ግድ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ደጋግ አባቶች ለምሳሌ እንደ ኖኅ እንደ አብርሃም እና ሌሎችም ነቢያት ቢነሱም እንኳን ሰውን ልጅ ሁሉ መድኃኒት ሆነው ለማዳን ይቅርና እራሳቸውን የማያድኑ በምድር ላይ መፃተኛ ሆነው አልፈዋል፡፡  ከሰው ልጆችም ይህንን ካሳ መካስ እና ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የሚችል ፍፁም ሰው ባለመኖሩ እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ የሰው ልጆችን በደል ስለሰው መካስ ነበረበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር ለሰው ጆች ያለው ፍፁም ፍቅር ይገለጥ ዘንድ አምላክ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡ ተበዳዩ ለበዳዩ እጅግ ደሃ ለሆነው ሰው ካሳ የሚክስ ምንኛ ቸር አምላክ ቢሆን ነው!
የሰው ልጅ በውድቀቱ ምክንያት ያገኘው የሞት ሞት በክብር ከእርሱ ለሚያንሰው የንስሃ ልብ ለሌለው ለዲያብሎስ ተገዢ አደረገው፡፡ ዲያብሎስም አዳምንና ሔዋንን መከራ አፅንቶ አዳም ግብሩ ለዲያብሎስ፤ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ማለትም አዳምና ሔዋን ለዲያብሎስ ተገዢዎችና ባሮች ናቸውየሚል ፅሑፍ ፅፎ አስፈርሟቸው ይህን የዕዳ ደብዳቤያቸውን አንዱን በዮርዳኖስ ባሕር አንዱን ደግሞ በሲኦል በበርባኖስ ባሕር በጥልቁ ጥሎት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ በጥምቀተ ዮርዳኖስ መጠመቅ፤ በሲኦል ያለውን ለመደምሰስ ደግሞ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መከራ መስቀልን መቀበል፤ መሞትና በአካለ ነፍስ ሲኦል ወረዶ የሰው የዕዳ ደብዳቤ መደምሰስ እና በሲኦል የተጋዙ ነፍሳትን መማረክ ነበረበት፡፡ ስለዚህም አምላክ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡
በአዳም ምክንያት የተረገመች ምድር በቅዱሳን እግሮቹ (በኪደተ እግሩ) ትቀደስ ዘንድ አምላክ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡ ሕዝብና አሕዛብን አንድ ለማድረግ አምላክ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡ አርአያ ሊሆነን አምላክ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡
 እንግዲህ እግዚአብሔር ለአዳም ተስፋውን ከሰጠው በኋላ በምድር ጥሮ ግሮ ይበላ ዘንድ በምድር ይኖር ነበር፡፡ ከሞተ ስጋ በኋላ ደግሞ በሲኦል ለዲያብሎስ የሚገዛና ሆነ፡፡ በነዚህ የመከራ ዘመናት እግዚአብሔር መግቦቱን ከሰው ልጆች ፈፅሞ ያላራቀ በመሆኑ በምድራዊ ሕይወቱ በቸርነቱ ብዛት ለምድር ጠልና ዝናምን እንዲሁም ልምላሜን ሰጥቶ በጥቂት ወዙና ድካሙ ያረሳትንና ያለሰለሳትን ምድር ከጥቅት ዘሮች ብዙ ፍሬዎችን እየሰጠ በየሰከንዱ የሚያስፈልገውን ከባቢ አየር፤ በየሰዓታቱ የሚያስፈልገውን ውሃ በነፃ ያለ ድካም እንዲያገኝ አድርጎ በምድር ሕይወቱን እንዲመራ ረዳው፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉም ፍጥረት ከሚያደርገው ቸርነት በተጨማሪ ለሰው ልጅ ብዙ ፀጋዎችን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅ እንዲያገኝ በዚህም የሰው ልጅ የመዳን ተስፋ እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለው መልካም ግንኙነት ሳይቋርጥ ከዘመን ዘመን እንዲሸጋገር በየዘመኑ የተለያየ እርዳታ እያደረገለት ኖሯል፡፡ ከእነዚህም በመጀመሪያ በዘመነ አበው የእግዚአብሔር ትእዛዛት በሰው ልብ ላይ የተቀረፁ ነበሩ፡፡ በኋላም ሰው ሕግጋቱን እየረሳ እግዚአብሔርን በመበደል ጉዳት ቢያገኘው የተፃፈ ሕግን በሊቀ ነቢያት ሙሴ በኩል ሰጠው፡፡ በዚህም ሰው አሕዛባዊ ልማድን በመልመድ እግዚአብሔርን ዳግመኛ ስለበደለ ፊት ለፊት የሚያስምሩትና የሚገስፁትን ነቢያትን እያስነሳ ከጥፋትና ከእግዚአብሔር ቸርነት ሳይርቅ እንዲኖር ረቶታል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር መግቦቱና መለኰታዊ ጥበቃ ቀጥሎ ባለው አንቀጽ  እንደምንመለከተው ንፁህ ዘርን ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ካለው ዓላማ ጋርም ተያያዥነት አለው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአዳም ልጅ በሴት በኩል ንፁህ ዘርን ጠብቆ ሊያቆይልና ለአሕዛብና ለሕዝብ መድኃኒት የሚሆን አምላክን በማሕፀኗ የምትሸከም ንፅህት ዘርን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊያስተላልፍልን ወዶ የእግዚአብሔርን ሕግጋት የሚጠብቁ ሕዝቦችን በምድር ለየልን፡፡ ዓለም ሁሉ በበደለበት በዘመነ ሰባትካት ይህች ንፅህት ዘር በደል ባልተገኘበት በኖኅ አብራክ ነበረች፡፡ ዓለም ሁሉ እግዚአብሔርን በመርሳት በጣኦት አምልኮ በጠፋበት በአብርሃም ዘመን ይህች ንፅህት ዘር የጣኦትን አምልኮ በመጥላት እግዚአብሔርን በፍጥረቱ ተመራምሮ ያገኘ በአብርሃም አብራክ ውስጥ ነበረች፡፡ እንዲሁም ብኩርናን እጅግ በመሳሳትና በጉጉት ከኤሳው ከወንድሙ በእምነቱ ብዛት በተቀበላት የእግዚአብሔርን ጸጋ በናፈቀ በያዕቆብ አብራክ ውስጥ ነበረች፡፡ በዚህ ሁኔታ ለእግዚአብሔር እራሳቸውን የበለጠ ባስገዙ በሕሊናቸውም በስጋቸውም የተሻለ ንፅህና በነበራቸው ውስጥ ከዘመን ዘመን ያች ንፅሕት ዘር ተሸጋገረችልን፡፡ ለዚያ ነው ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር” (ኢሳ. ፩፥፱) ያለው፡፡
ከላይ እንደተገለጠው የነቢያት መምጣት ሰው ተስፋ በመቁረጥ ከእግዚአብሔር መንገድ እንዳይወጣ ሕግጋትን እንዲጠብቅ ከማስተማር በተጨማሪ ሰው በስባሽ ፈራሽ ሆኖ እንደማይቀር ድህነትን ተስፋ እንዲያደርግ የመልካም ዘመን ትንቢት የምሕረት ዘመን መቅረብን ሊያበስሩ ሊያስተምሩ ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔርም የድህነት ሥራውን ለማከናወን ቀድሞ በነቢያት ትንቢት አናግሮ ሱባኤ አስቆጥሮ መምጣት እንጂ ሃላፊያትንና መፃያትን የሚያውቅ ማእምረ-ኩሉ እግዚአብሔር ሥራዎቹ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ  ፈሳሽ አለመሆኑን ለማሳዎቅ በየዘመናቱ እነዚህን ነቢያት አስነስቷል፡፡ በዚህም ስለሰው ልጅ ድህነት ስለ አምላክ ከድንግል ማሪያም መወለድና ስለ ነገረ መስቀሉ የተለያዩ ነቢያት በተለያዩ ዘመናት ትንቢት ተናገረዋል፡፡ ቀደም ብሎ የመጀመሪያው ትንቢት ከይሲ በተረገመበት በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እራሱ እግዚአብሔር ከተናገረው ጀምሮ (ዘፍ. ፫፥፲፭) ሙሴ ዳዊት፣ ዳንኤል፣ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅየልና ሌሎችም ትንቢትን ተናገረዋል፡፡ ለአበውና ለነቢያትም እመቤታችን ድንግል ማሪያምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ምሳሌዎች እየታዩዋቸው የምሕረት ዘመንን ተስፋ እያደረጉ ኖረዋል፡፡
ደረቅ ሐዲስ በመባል የሚታወቀው ነቢዩ ኢሳይያስ ብዙ ግልፅና የማያሻሙ ትንቢቶችን ስለ ነገረ ድህነት ማለትም ስለ እመቤታችን ድንግል ማሪያምና ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ ይህ ነቢይ በመጀመሪያው ምዕራፍ ነው ገና ስለ እመቤታችን ንፅህናና የቀደመው የሰው ልጅ መተላለፍ (ጥንተ አብሶ) እንደሌለባትና ይህች ንፅሐ ባህርይ የድህነት ዘር ሆና በቅዱሳን ሰዎች አብራክ ተጠብቃ ከትውልድ ትውልድ እንደተላለፈች ሲገልፅ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር” (ኢሳ. ፩፥፱) ያለው፡፡
እስኪ በነቢያት የተነገሩትን ጥቂቶቹን ትንቢቶች እንደሚከተለው እንመልከት፡-
በመቀጠልም “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።”  ኢሳ. ፯፥፲፬
“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ኢሳ. ፱፥፮ 
የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም። የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር። እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።ኢሳ. ፶፫. የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ የቸርነቱን ብዛት የተቀበለውን የመከራ ፅናት ወዘተርፈ ያሳየናል፡፡ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል ከዚህ ከኢሳይያስ ምዕራፍ ሃምሳ ሦስት የትንቢት ክፍል፡፡
“ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም። ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።” ሕዝ. ፵፬፥፩-፪ የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና በዚህ የትንቢት ቃል ተገልጧል፡፡ በሥጋና በነፍስ ድንግል እመቤታችን እንደሆነች ይናገራል፡፡

….ይቀጥላል…

1 comment: