Thursday, May 3, 2012

ሰው በምድር ሲኖር ሊያተርፍ የሚያቅደው ምንድ ነው? (ክፍል አራት)




ባለፈው ክፍል ሦስት እግዚአብሔርን መውደድ እና ሕግጋቱን ማክበር እውነተኛ የደስታ የጤናማነት እና የምቾት ብሎም የውጤታማነት ምንጮች የመጀመሪውን ቦታ የሚይዝ እና ከሁሉም መቅደም ያለበት መሆኑን እና እግዚአብሔርን የሚወድ ሕግጋቱንም የሚጠብቅ በምድር ሕይወቱ የተባረከ ደስተኛ ጤነኛ ሆኖ መኖር የሚችል መሆኑን ተመልክተናል፡፡
ዛሬ ሁለተኛውን እውነተኛ የደስታ የጤናማነት እና የምቾት ብሎም የውጤታማነት ምንጭ እነሆ!


 2.  ሰዎችን ሁሉ መውደድ እና ለሌሎች ሰዎች ቅን እና መልካም መሆን
በመጀመሪያው ክፍል እንደተመለከትነው ሰው ቁሳዊ ነገሮችን በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልጉት ቢሆንም ጤናማ ሕይወት እና ሰላማዊ ኑሮ ግን የተረጋጋ የመንፈስ ነጻነት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ የህንን ገንዘብ ለማድረግ ደግሞ ሰው የደስታው መጠንና የተረጋጋ ነጻ አስተሳሰቡ የሚመነጨው ለሰው ሁሉ መልካም በመሆንና መልካም ነገር በማደረግ ነው፡፡ ፍቅርን የምታውቅ ልባዊት ነባቢት እና ህያዊት ነፍስ ያለችው ሰው ዘመኑ ሁሉ ደስተኛ የሚሰራው መልካም ሥራ ሁሉ የሚከናወንለት ውጤታማ እንዲሁም ጤናማ ይሆናል፡፡
ሰው እግዚአብሔር በሰጠው ጥበብ በመጠበብ ውስን በሆነችው እውቀቱ እና ክሂሎቱ የሚሰራቸው የእጁ ሥራ የሆኑት የፈጠራ ውጤቶቹ ለምሳሌ መኪና አውሮፕላን እና የመሳሰሉት እርሱ በፈለገው መንገድ እንዲታዘዙት እና እንደሚፈልገው እንዲቀሳቀሱለት አዲርጎ ይሰራቸዋል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር መልካም እና ክፉውን ለመለየት የሚችልበት ማመዛዘኛ አእምሮ ያህል ቀጥተኛ አካል አድሎታል፡፡ ነገር ግን ሰው በሰራቸው የፈጠራ ውጤቶቹ እና በሰሪው መካከል እና በእግዚአብሔር መካከል አራት ዐቢይ ልዩነቶች አሉ፡-
፩∙ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሙሉ ነጻነት የሰጣቸው መሆኑ፡- ልዑል እግዚአብሔር የነጻነት አምላክ ነው የሚባለው ሁሉም ሰው በዚህ ምድር የወደደውን ማድረግ እንዲችል ነጻነት ሰቶታል፡፡ እግዚአብሔር የወደድነውን እምነት ብንከተል የፈለግነውን አስተሳሰብ ብናራምድ ሕግጋቱን ለሚጠብቁት እና ለባለሟሎቹም ሆነ ለሀጥአን እኩል ዝናምን ያዘንማል ፀሐይን ያወጣል፤ ነፋሳትን (ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ከባቢ አየርን) አድሏል፡፡ ሀጥኡን እስከ ሕይወቱ ፈጻሜ ድረስ በንስሃ እስኪመለስ ይጠብቀዋል እንጂ ፈጥኖ ቅጣትን አይቀጣውም (የሌሎች የፅድቅ ሥራ መሰናክል ካልሆነ በቀር)፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔር ቸር እና ሩህሩህ አምላክ ስለሆነ ሰው ባለማወቅ የቀናች መንገድን ባለመከተል እንዳይጎዳ ክፉ እና ደጉን ለይተን እናውቅ ዘንድ ማሰቢያ ማመዛዘኛ አእምሮን አድሎናል፡፡ ሰው በአእምሮው በመጠቀም ክፉና ደጉን ለይቶ በመመርመር መልካም የሆነውን የመመምረጥ ኃላፊነት አለበት፡፡
ነገር ግን ሰው በፈጠራ ጥበቡ ለሰራቸው መገልገያዎቹ እንዲህ ዓይነት አንጻራዊ ነጻነት አልሰጣቸውም፤ ሊሰጣቸውም አይችልም፡፡
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የሚያከናውነው መለኮታዊ ጥበቃ፡-  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሊቀ ሐዋሪያት ቅዱስ ጵጥሮስ እንዳሳየው የሰው ልጆች ሕይወት ብቻ ሳይሆን ጠፈርና ሰማያት እንዲሁም በእነዚህ ውስጥ ያሉት አካላት ሁሉ በእጁ የተያዙ ናቸው፡፡ ለሽርፍራፊ ደቂቃዎች እንኳን ሳያንቀላፋ ለፈጥረቱ ሁሉ መለኮታዊ ጥበቃ ያከናውናል፡፡ ለሕይወታዊ ነገሮች በየጊዜው እና በየሰኮንዱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ እና ምግባቸውን (ምግብ፣ውሃ፣አየር፣ወዘተርፈ) ያዘጋጃል፤ ያድላቸውማል፡፡
እንደሌሎቹ ፍጥረታት ሁሉ ለሰው ልጆችም ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ በማድረግ እስከ ሕይወት ፈጻሜያቸው ድረስ መለኮታዊ ጥበቃ ያደርግላቸዋል፡፡
ነገር ግን ሰው ለእጆቹ ሥራዎች እንደ እግዚአብሔር ጥበቃ እና እንክብካቤ አያደርግላቸውም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ይሸጣቸዋል፤ ይጥላቸዋል፤ ያፈርሳቸዋል፤ ወዘተርፈ፡፡
፫. እግዚአብሔር ሰውን ዘላለማዊ እና ሕያው አድርጎ የፈጠረው በመሆኑ፡- እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ከሰባት ባህሪያት ነው፡- ከአራቱ ባህሪያተ ሥጋ እና ከሦስቱ ባህሪያተ ነፍስ፡፡ በባህርየ ሥጋው ዐረፍተ ዘመን የሚገታው ቢሆንም ሕያዊት ነፍስ ያለችው ሰው ዘላለማዊ እና ሕያዊት ናት፡፡ በዐረፍተ ዘመን የተገታው ሥጋም ቢሆን በኋለኛው ዘመን በትንሳኤ ዘጉባኤ ከነፍስ ጋር ተዋህዶ ላይሞት ይነሳል እንጂ ፈርሶ በስብሶ አይቀርም፡፡ በዚህም ሰው ዘላለማዊ እና ሕያው ሆኖ የተፈጠረ ነው እንላለን፡፡
ነገር ግን ሰው የሰራቸው የሥራ ውጤቶቹ ዘላለማዊ አይደሉም፡፡ ሕያው የሆነ የሥራ ውጤት ከነ አካትው የለውም፡፡  
፬. እግዚአብሔር ሰውን መልካም ሲሰራ የሚደሰት የሕሊና እራካታ ያለው አድርጎ የፈጠረው በመሆኑ፡- በቁጥር እንደተመለከትነው ሰው የተፈጠረው አራት ባህሪያተ ሥጋ እና ሦስት ባህሪያተ ነፍስ እንዲኖሩት ሆኖ ነው፡፡ በሥጋ ባህርይው እንስሳትን ሲመስል በነፍስ ባህርይው ማእምረ ኩሉ (ሁሉን አዋቂ) እግዚአብሔርን ይመስላል፡፡ የነፍስ ባህርያት ነባቢነት (መናገር) ልባዊነት (ማሰብ ማመዛዘን መቻል) እና ሕያውነት (ዘላለማው ሕይወት ያለው) ናቸው፡፡
እንግዲህ ሰው በተወሰነው የመጠበብ ችሎታው የሚሰራቸውን እቃዎች እና የእጁን ሥራዎች ለትእዛዛቱ ታዛዥ (ለፈለገው ዓላማ የተመቹ) አድርጎ እንደሚሰራቸው ሁሉ እግዚአብሔር ደግሞ ወሰን ልኬት በሌለው ጥበቡ ሰውን ለትእዛዛቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ታዛዥ እንዲሆን አድርጎ ሳይሆን የሰራው ነጻ አስተሳሰብ እንዲኖረው ነጻነትን፣ ክፉና ደጉን ለይቶ እንዲወስን ልባዊነትን፣ መልካም ሲሰራ እና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲኖር ወሰን የሌለው በጊዜና በቦታ ያለተወሰነ ሀሴት (ደስታ)ና የሕሊና እርካታ እንዲያገኝ፣ ወደ ከፋ መንገድ እግሮቹ ሲያቀኑ መልካም ያልሆኑ ተግባራትን ሲሰራ ደግሞ ሕሊናዊ ወቀሳ እንዲደርስበት (የራሱ ሕሊና እንዲገስፀው) እና ሰላማዊ ሕይወት ከእርሱ እንዲርቅ አድርጎ ነው የፈጠረው፡፡
ስለዚህ ባለፈው ክፍል ቁጥር 1 ላይ እግዚአብሔርን መውደድ እና ትእዛዛቱን መጠበቅ ከእግዚአብሔር የፍቅር ትእዛዛት የመጀመሪያው የፍቅር ትእዛዝ ሲሆን በዚህ ክፍል ቁጥር 2 ላይ የቀረበው ሰውን ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መውደድ እና ለሰው ሁሉ መልካም ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው የፍቅር ትእዛዝ ነው፡፡ እነዚህን ትእዛዛት ያለምንም ማመንታት የምንፈጽም ከሆነ እግዚአብሔር በሕሊናችን ዳኝነት አማካኝነት ሰላማዊ ሕይወትን፣ ደስታን፣ ሕሊናዊ ምቾትን፣ ጤናማ ኑሮን ይሸልመናል፡፡ ከእነዚህ ትእዛዛት ፈቀቅ ስንል፤ ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሳናስገዛ ስንቀር ደግሞ ሁልጊዜ ተቅበዝባዥ እና ቁሳዊ ነገር ሞልቶ በተረፈው ቤታችን ታማሚ፣ ሰላማችን የተነፈገን፣ የሰከነ መንፈስ የሌለን ደካሞች እንሆናለን፡፡
ሰው ቁሳዊ ነገሮች የሚያስፈልጉት በቁመተ ሥጋ ለመቆየት ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህ አላስፈላጊ ናቸው አይባልም፡፡ ነገር ግን በብዙ እና በመስገብገብ የምንሻቸው ከሆነ ለሰላማችን እና ለምድራዊ ሕይወታችን የምንፈልጋቸውን ሰላም፣ ጤና፣ ምቾት፣ እና እርካታን ያሳጡናል፡፡ ስለዚህ ሰው ከቁሳዊ ነገሮች በተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ (መንፈሳዊ ነገርም) አስፈላጊው ነው፤ በተለይ ከላይ ለተጠቀሱት ሰው በምድራዊ ሕይወቱ ያስፈልጉኛል ብሎ የሚያስባቸውን እሴቶች ለማግኘት፡፡
እንግዲህ ሰው በዚህ ምድር ሲኖር ሰላማዊ፣ ጤናማ፣ ምቾት ያለው፣ እርካታ የተሞላበት፣ የሰከነ ሕይወት ለመኖር የሚመኝ ከሆነ ለልጆቹም የእነዚህን እሴቶች ምንጮች ለማውረስ ከፈለገ ዘመኑን በሙሉ ባለፈው ከፍል በቁጥር 1 እና በዚህ ክፍል ቁጥር 2 የተመለከቱትን ትእዛዛተ እግዚአብሔር መፈፀም አለበት፡፡
 
         ……. ተጠናቋል….

No comments:

Post a Comment