Wednesday, May 16, 2012

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል ዘጠኝ)


ያለፉትን ተከታታይ ክፍሎች ለማንበብ ከፈለጉ፡- 
   ባለፈው ክፍል ለመመልከት እንደሞከርነው የቤተ ክርስቲያንና የሀገሪቱ የኋሊት ዕድገት በግራኝ አህመድ ዘመን ተጀምሮ ቁልቁል እያደገ እስከ ዘመነ ፋሲል ድረስ የቆዬ ሲሆን በዘመነ ፋሲል ለጥቂት ዘመናት ቢሆንም ሀገሪቱም ሆነ ቤተ ክርስቲያን መጠነኛ ማንሰራራት የተየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በዘመነ ፋሲል የተጀመሩት አዎንታዊ ለውጦች ዘመነ መሳፍንት ሲመጣ ተመልሰው ተዳፍነዋል፡፡ በዚህም ከግራኝ አህመድ ወረራ በኋላ የሀገሪቱም ሆነ የቤተ ክርስቲያን የትንሳኤ ዘመን ሳይታደሉ የኋሊት እድገት እየታየ የዘመነ መሳፍንት ማብቂያ የአፄ ቴወድሮስ ዘመን ደረሰ፡፡
ዛሬ የምንመለከተው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ ከአፄ ቴወድሮስ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ያለውን ነው፡፡  
ቤተክርስቲያን አንፃራዊ መሻሻል ያሳየችበት ዘመን በአፄ ቴወድሮስ ዘመን ጀምሮ እስከ አፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት የቆየ ሲሆን ነገስታቱ ቤተክርስቲያኗን ተጠግተው አንፃራዊ ጉዳትም አድርሰውባታል፡፡ ለምሳሌ፡- በዘመነ ቴወድሮስ እና በዘመነ ዮሐንስ የእስልምና እምነት ተከታዮችን በግድ ለማጥመቅ ባደረጉት ሙከራ ሁለት ዐበይት ጥፋቶችን በቤተክርስቲያን ላይ አድርሰዋል፡፡
. የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና ከሚፈቅደው ውጭ በኃይል በመጠቀም ወንጌልና ጥምቀት ለማስፋፋት በመሞከራቸው የቤተክርስቲያን  ሕግን ተላልፈዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗም በታሪክ “ተወቃሽ” እንድትሆን አድርጓል፡፡
. በተለይም በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ጊዜ በዚህ የኃይል ድርጊት ያኮረፉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከሀገሪቱ በመሰደድ ወደ ሱዳን ሔደው ከደርቡሾች ጋር ወደ ግብፅ ሄደው ከግብፅ ጋር በማበራቸው የተለያዩ የስለላ ስራ በመስራት እና የባዕዳንን ጦር በመምራት ሀገሪቱን ለተለያዩ ጦርነቶች የዳረጉ ሲሆን ከግብፅ ጋር የተደረጉ ጦርነቶችን በድል የተወጡት አፄ ዮሐንስ በመተማ ጦርነት ከደርቡሾች ጋር በተደረገው ጦርነት ግን የራሳቸውን ሕይወት ሳይቀር ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ከዚህ ከመተማ ጦርነት በኋላ ደርቡሾች እስከ ጎንደር ከፍተኛ ቦታዎች ድረስ ዘልቀው በመግባት አያሌ ቤተክርስቲያናትን ቤተ መዛግብትን መፃሕፍትን እና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን ያቃጠሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችም ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ዘመንም በኢትዮጵያ አራተኛው ዘመነ ሰማእታት ሆኖ አልፏል፡፡
ከአፄ ቴወድሮስ ዘመን እስከ አፄ ሚኒልክ ዘመን ቤተክርስቲያንም ሆነ ሀገሪቱ አንፃራዊ እድገት ቢያስመዘግቡም እድገቱ ግን አዝጋሚ እና ያለፈውን ዘመን ጠባሳ የሚነጣ ያለፈውን ዘመን አሉታዊ እድገት የሚቀለብስ አልነበረም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ ዘመናት (ከዘመነ ሱስንዮስ ጀምሮ) ከአውሮጳውያን ሀገራት ጋር የተለሳለሰ ግንኙነት በመፍጠር ጠንካራ መንግስታዊ አስተዳደር ለመመስረት በነበራቸው አቋም የአውሮጳ ዘመን አመጣሽ ቤተእምነቶች “መልእክተኞች” ሀገሪቱን የጎበኙበትና እምነታውን ከማስፋፋት  በተጨማሪ የስለላ ሥራ የሰሩበት ዘመንም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የተነሱት የሐይማኖት ኑፋቄዎችና የኦርቶዶክስ አባቶች ፍትጊያ በመካከለኛው ምስራቅበአውሮጳ እና በሰሜን አፍሪካ ብቻ የተወሰኑ በመሆናቸውና ወሬው ኢትዮጵያ ቢመጣም በሊቃውንቱ መካከል የሚቀርና መልስ የሚሰጥበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናን በአንፃራዊነት ንፁህ ህሊና ያላቸው በእምነታውም ጠንካራ እንዲሆኑ ይህ እሴትም ብዙ ክፍለዘመናትን ተሻግሮ እስከ አስራ ዘጠነኛው መቶ ክ/ዘመን የደረሰ ነበር፡፡ ከላይ የተጠቀሰው መንታ ዓላማ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ያሉት የአውሮጳ ሀገራት “መልእክተኞች” የሕዝቡን ንፁህ ህሊና በማርከስ ከኑፋቄ ትምህርቶች ጋር እንዲተዋወቅ በር ከፍተዋል፡፡
ከላይ ከተመለከትናቸው ከአፄ ቴወድሮስ እስከ አፄ ሚኒልክ በነበሩት ዘመናት አፄ ቴወድሮስ በከፈተው የኢትዮጵያ አንድነት የቤተክርስቲያን አንድነትም በበለጠ ተጠናክሯል፡፡ ቤተክርስቲያንና ኢትዮጵያ በተለይ በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት በበለጠ የተሻለ እድገት አሳይተዋል፡፡ በተለይ በደቡብ በምስራቅና በደቡብ ምዕራብ አፄ ሚኒልክ ባደረጉት የግዛት ማስፋፋት ቤተ ክርስቲያንም ብዙ አሕዛብን እያጠመቀች የመንፈስ ቅዱስ ልጆች ማድረግ ችላ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን የሀገሪቱ የአንድነት ምልክት (Uniting Figure) በመሆን ሕዝቡን ሁሉ አንድ ዓላማ ያለው እንዲሆን የምትሰራ የግብረ ገብነት እና የሀገር ወዳድነት ስሜትን በሕዝቡ የልብ ፅላት ላይ የምትቀርፅ በመሆን ታላቅ ስጦታን አበርክታለች፡፡ ይህም በአደዋ ጦርነት ወቅት ቤተክርስቲያን ያደረገችውን አስተዋፅኦ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በጦርነቱ ወቅት የሕዝቡ የሥነ-ልቦና ጥንካሬ ምንጭ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ ሳትደፈር የመቆየቷ ሚስጢር ይኸው ነው፡፡
ከዚህ ላይ ግን የቤተ ክርስቲያንን ስም ጥላሸት ለመቀባት አንዳንድ አላዋቂዎች በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት ያደረገችውን በደቡብ በምስራቅና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አሕዛብን የማጥመቅ ሥራ በግድ እንደባርነት ቀንበር የተጫነባቸው ለማስመሰል ታሪክን የማያውቁ ወይም ደግሞ ሆን ብለው ታሪክን ለመፋቅ ታጥቀው የተነሱ ሰዎችና ድርጅቶች መኖራቸውን እየተመለከትንና እየሰማን ነው፡፡ በአፄ ሚኒሊክ ግዛት ለማስፋፋት ከአካባቢያዊ መሪዎች ጋር ጦርነት ማድረጋቸው አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሐይማኖትን በግድ እንዲቀበሉ የማስገደድ ስራ በስፋት የተሰራው በወሎና በጎንደር በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ በዘመነ ዮሐንስ አራተኛ ብቻ ነው፤ በአፄ ሚኒልክ ዘመን እንዲህ ዓይነት ታሪክ አልነበረም፡፡ ይህ የቅርብ ጊዜ ጥላሸት የመቀባጥ ክስተት ከጥቂት ዘመናት ጀምሮ የመጣ ፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ እንጅ እውነት አለመሆኑን እራሳቸው የፖለቲካው አቀንቃኞች ይገነዘቡታል ባይ ነኝ፡፡ 
(Source: Wikipedia, the free encyclopedia)
ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ እንኳን ለኢትዮጵያ ይቅርና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ብርሃን ፈንጣቂ፤ የአፍሪካ ሕዝቦች የድል ችቦ ለኳሽ ናቸው፡፡ አንድ አንድ በዘመኑ መስፈርት ተለክተው አጥፍተዋል ተብለው ሊወቀሱ የሚችሉበት ሳንካዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ስለ ሦስት ዐብይ ምክንያቶች ታሪክ እርሳቸውን ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ መሪዎች ውስጥ በቀዳሚነት እንዲቀመጡ ታሪክ ያስገድዳል፡፡
. የአደዋ ጦርነት ባለድል ጀግና፤ የአፍሪካ አሸናፊነት የተስፋ ፋና ወጊ፤ የአፍሪካ ነፃነት ነጋሪት ጎሳሚ በመሆናቸው፤  
. የሀገሪቱ ዘመናዊነት በር ከፋች በመሆናቸው የሰሯቸው እና ያስጀመሩዋቸው ዋና ዋና ሥራዎቻቸው ለትውልደ ትውልደ የማይዘነጉ ዘወትር የሚታወሱ ዐበይት ሥራዎች በመኖራቸው፤
. የሰሯቸው ጥፋቶች ቢኖሩም እንኳ ከሰሩት ደግነትና መልካም ሥራዎች ጋር ሲነፃፀር ኢምንት በመሆኑና ሥራቸው መመዘን ያለበት እርሳቸው በኖሩበት ዘመን መስፈርት በመሆኑ ናቸው፡፡
አፄ ሚኒልክ ለቤተክርስቲያን ቀናኢ በመሆናቸውና ቤተክርስቲያንም በእርሳቸው ዘመን በነበራት አንፃራዊ ሰላም የተሻለ እድገት ማሳየት ችላ ነበር፡፡ የአሕዛብ እናት ለመሆን የቻለችበት የሩቅ ሰዎችን ጥሪ ተቀብላ በእናትነት ያቀፈቻቸው ብዙ ጎሳዎችና ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በዚህም የተሻለ ሐዋሪያዊ ሚናዋን ባለፈው አምስት ክ/ዘመናት ውስጥ በተሻለ ሁኔታ በአፄ ሚኒልክ ጊዜ ተወጥታለች ማለት ይቻላልማለት ይቻላል፡፡     

… ይቀጥላል…

2 comments:

  1. This is good story about our church and the leaders. Even though it is too difficult to separate the religion and politics in history of Eth, in my opinion many of them have did non-religious work, like killing, slavery, Partitioning, discrimination (inequality in ethnic,resources, etc). Hence, in criteria of religion many are not pass the exam. Let evaluate their act either in religious perspective or political perspective, many of them not be blessed in both. So, this will affect some innocent Orthodox followers to be ashamed and wrongly take an action like to change religion, etc with some of the acts of those politicians. So, let leave alone religious activity for other and activity of leading country to politicians.

    ReplyDelete
  2. በዊልቸር ከሚገፋ ፖለቲካ፤ዘመን ተሻጋሪው ታሪካችን ይሻላል!

    ReplyDelete