Tuesday, July 5, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል ስድስት)


በባለፈው ለመመልከት እንደሞከርነው ኢትዮጵያ ከዮዲት ጉዲት የጥፋት ዘመን በኋላ የአክሱም ሥርወ መንግስት እየተዳከመ ሄዶ በዛግዌ ሥርወ መንግስት ተተካ። ኢትዮጵያ በዛግዌ ሥርወ መንግስት የተወሰኑ የሀገሪቱ ሰሜናዊ ጫፎች ላይ ያላት ቁጥጥር አነስተኛ ስለነበር በአሁኗ ኤርትራ የቀይ ባህር አዋሳኞች እና በቀይ ባህር ውስጥ ባሉት ደሴቶች ላይ የነበሩ ጎሳዎች የእስልምና ሰለባ በመሆን በኋላም በኢትዮጵያ  መካከለኛው የታሪክ ዘመን ጥቃቅን የእስልምና ሱልጣኖች እንዲመሰረቱ ጥርጊያ መንገድ ከፈተ። የሰሜናዊ የባህር በሮችን በመጠቀምም በመሀል ሀገር ላይ ያሉት የተለያዩ ክፍሎች የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እና የእስልምና እምነት እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል።
እነዚህንና የመሳሰሉትን ድክመቶች ቢያስተናግድም የዛግዌ ሥርወ መንግስት በዮዲት ጉዲት ዘመን በሀገሪቱ እና በቤተክርስቲያኗ ላይ ከደረሰው ጥፋት መልሶ ማንሰራራት ብሎም ሁነኛ የሚባሉ ድንቃድንቅ የአቢያተ ክርስቲያናት መታነፅ እና የቤተክርስቲያን ትምህርት መስፋፋት ትልቅ አስተዋፅኦ የከፈተ እና ኢየሩሳሌምን የሚተካ የአፍሪካ ኢየሩሳሌም (Jerusalem of Africa) እየተባለ የሚጠራውን የላልይበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት የተሰሩበት እና ቤተክርስቲያኗ በሀገሪቱ የነበረውን የሥነ-ፅሑፍ የሥነ-ሕንፃ እና አያሌ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች የመራችበት እና አርአያ የሆኑ ቅዱሳን አባቶችን ንግስናን ከክህነት ጋር አስተባብረው የያዙ በጥበብ እና በመንፈስ ቅዱስ የተመሉ ሆነው ሕዝቡን በቀና መንገድ የመሩ ነገስታትን ለሀገሪቱ ያበረከተችበት ዘመን ነበር።
በሀገሪቱ ሰሜናዊ ጫፍ ያለው ክፍል ለእስልምና ተፅዕኖ ቢደርስበትም በደቡባዊ አቅጣጫ ክርስትና የተስፋፋበት ዘመንም ነበር። በዛግዌ ሥርወ መንግስት ጊዜ የነበረውን ሥራ በኢትዮጵያ ባይሠራ ኖሮ ዮዲት ጉዲትን ተከትሎ የሚመጣው የቤተክርስቲያኗ ዕድል ምን ይሆን እንደነበር መገመት አያዳግትም። የዮዲት ጉዲት ዘመን ከጥላቻ ያለፈ የራሱ ራዕይ እና ግብ ስላልነበረው ሀገሪቱ ወደ ይሁዲነት ባትቀየርም እንደ ዛግዌ ያለ የተደላደለ እና ጠንካራ ሥርወ መንግስት ባናገኝ ምናልባትም በዚህ በተዳከመ ጊዜ የመጣ ርህራሄ የለሽ የኦትማን ቱርክ ሰለባ እንሆንና ቤተክርስቲያኖቻችን በቁስጥንጢንያ (Constantinople) በዛሬዋ ቱርክ ውስጥ የሚገኘውን የቅድስት ሶፍያ ቤተክርስቲያን እጣ ይደርባቸው ነበር። ሀገሪቱም እንደቱርክ እና እንደ ግብፅ የክርስትና መናብርት እንዳልነበሩ ሁሉ ዛሬ እስላማዊ መንግስት ክርስትናን መድረሻ ያሳጡ እንደሆኑት ያለ ዕድል ይገጥማት ነበር። የዛግዌ ሥርወ መንግስት የኦትማን ቱርኮች ዓለምን ያሳድዱ እና ሀገራትን ይወሩ በነበረበት ዘመን ጠንካራ ሥርወ መንግስት ስለነበር ከዚያ ቀጥሎም በሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስት ቢተካም ይህ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስት ጠንካራ ስለነበር የኦትማን ቱርኮችም ሙሉ ሃይላቸው አውሮፓውያንን መውጋት እና የመስቀል ጦርነትን ድል ማግኘት ስለነበር ከትንኮሳ ያለፈ ነገር ባለማድረጋቸው እና ሀገር ውስጥ ያሉ ጥቃቅን ሱልጣኖችን በመርዳት በሀገሪቱ ላይ በቀላሉ ባለድል እንሆናለን ብለው ይገምቱም ስለነበር የእነዚህን ሱልጣኖች ትንኮሳ ተቋቁሞ በሀገሪቱ እና በቤተክርስቲያናችን ላይ የነበረውን አወንታዊ ዕድገት ሊገቱት አልቻሉም።
የዛግዌ ሥርወ መንግስት ከቅዱስ ላልይበላ መሞት ቀጥሎ በነበረው የሥልጣን ሽኩቻ  እየተዳከመ ሄዶ በሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስት ሲተካ የመናገሻ ከተማ ከላስታ ወደ ሸዋ ዞረ። ይህ የመናገሻ ቦታ መዞር በሀገሪቱ ሰሜናዊ ጫፍ የነበረው ቅጥጥር በዚያው ልክ እየላላ በዛግዌ ሥርወ መንግስት የተፀነሱት ሱልጣኖች እየተጠናከሩ መጥተው መኖራችውን የሚያሳውቅ ተፅዕኖ እና ከኦትማን ቱርኮች በሚደረግላቸው ድጋፍ ማዕከላዊ የሀገሪቱ መንግስት ላይ ትንኮሳ ጀመሩ። የሰለሞናዊ ሥርወ መንግስት እንደ ዛግዌ ሥርወ መንግስት እጅግ ጠንካራ ባለመሆኑ በሀገሪቱ ማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ቦታዎች በኢፋት እና በሀረር የተላዩ ሱልጣኖች በቅለው ማደግ ጀመሩ። በዚህም በሰሜንም በምስራቅም አቅጣጫ የሚመጡ የእነዚህን ሱልጣኖች ትንኮሳ መከላከል ለሥርወ መንግስቱ ሌላ የቤት ሥራ ሆኖ ነበር።
እነዚህን ተፅዕኖዎች በመቋቋም ይህ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስት በዛግዌ ሥርወ መንግስት የተጀመረውን ሐይማኖታዊ እድገት ለ፫፻ ዓመታት ያህል ለማስቀጠል ችሏል። ይህ ከ፲ኛው እስከ ፲፭ኛው መ/ክ/ዘመን ያለው ጊዜ ወርቃማው የቤተክርስቲያን ጊዜ ይባላል። ቤተክርስቲያን በዮዲት ጉዲት ከደረሰባት ጥፋት አገግማ ለዛሬ ማንነታችን ትልቅ ድርሻ ያላቸው የቤተክርስቲያን ሥራዎች የፈለቁበት እና ክርስትናን በማስፋፋት እና የተለያዩ ታላላቅ አድባራት እና ገዳማትን በማቋቋም እና መፃሕፍትን በመፃፍ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ታላላቅ ቅዱሳን ያፈራችበት ዘመን ነበርና። እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዘመን ከቤተ ክርስቲያን ጉያ የፈሩ ከዋከብተ ቤተክርስቲያን ናቸው።
ነገር ግን በ፲፭ኛው መ/ክ/ዘመን የመስቀል ጦርነትን ባለድል የሆኑት የኦትማን ቱርኮች ትኩረታቸውን ወደ ቀይ ባህር ዙሪያ በነበሩት አካባቢዎች አድርገው ስለነበር በተለያዩ አቅጣጫዎች የነበሩትን ሱልጣኖች የጦር መሳሪያ እርዳታ በመስጠት ክርስቲያናዊ የሆነውን ማዕከላዊ የኢትዮጵያን ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስት ማዳከም እና በመጨረሻም የማጥፋት እና ሀገሪቱን በሃይል ለማስለም ምስራቅ አፍሪካም በእስልምና እንድትጥለቀለቅ በዚህም በቀይ ባህር ዙሪያ ወደ ሩቅ ምስራቅ እና ሕንድ የሚደረገውን የአውሮፓውያንና የመካከለኛው ምስራቅ የንግድ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እንዲያመች አልመው በመነሳታቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የነበሩት ሱልጣኖች በተለይም የሀረር ሱልጣን ከፍተኛ የሆነ ሃይል አሰባስቦ በተላዩ ጊዜያት ጥቃት መሰንዘር ጀመረ። ማዕከላዊ የሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስትም የእነዚህን ሱልጣኖች ለመመከት ለተወሰኑ ክፍለ ዘመናት ሲከላለከል ከቆየ በኋላ በመጨረሻ እየተዳከመ በመሄዱ እና የሀረር ሱልጣን ከኦትማን ቱርኮች ባገኘው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ስለነበር ድል ፊቷን በማዞር ለግራኝ አህመድ ቀናችለት። በዚህም ክርስቲያናዊ የሰሎሞን ሥርወ መንግስት ከሸዋ እየሸሸ በተለያዩ የጦር አውድማዎች ከግራኝ አህመድ ጋር ጦርነት ቢያካሂድም ድል አልቀናው ስላለ የሥርወ መንግስቱ መናገሻ ወደ ጐንደር ተዛወረ። ግራኝ አህመድም አብዛኛውን የሀገሪቱ ክፍል በቁጥጥሩ ሥር አውሎ ሕዝቡን ሁሉ በሃይል በማስለም ካህናትንና ለመስለም ፈቃደኛ ያልሆኑትን ምዕመናን በመጨፍጨፍ አቢያተክርቲያናትን እና ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሁም መፃሕፍትን በማቃጠል እጅግ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ እስከ ጐንደር ደረሰ። ይህም የጥፋት ዘመን ለ፲፭ ዓመታት ቆየ። ጐንደር በተደረገው የአፄ ገላውዲዎስ እና አህመድ ግራኝ ጦርነት አህመድ ግራኝ በአንድ ፖርቱጋላዊ ወታደር ተመትቶ ስለሞተ ተከታዮቹ ወደ ሀረር ተመልሰው ፈለሱ እና አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ተመልሰው በክርቲያናዊ መንግስት ቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ይህ የአህመድ ግራኝ የጥፋት ዘመን ብዙ እልቂት እና ብዙ ጥፋቶች ያስከተለ ነበር። 

በሚቀጥለው ክፍል በአህመድ ግራኝ የደረሰውን ጥፋት እና ከዚያም ቀጥሎ የፖርቱጋል የሮማ "ቤተ ክርስቲያን" መልዕክተኞች በሀገራችን የደረሰውን ከፍተኛ የመከራ ዘመን እንቃኛለን


         …ይቀጥላል…       

No comments:

Post a Comment