Thursday, August 16, 2012

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከአባ ጳውሎስ በኋላ መሪዋ ማን መሆን አለበት?

                                    
                       አቡነ ባስሊዮስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ


ቤተክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት ብዙ የውጣ ውረድ እና የመከራ ዘመናትን አሳልፍ ዛሬ ላይ እንደደረሰች ታሪኩ ሙሉ ለሙሉ ያለተጠናቀቀ ቢሆንም የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? በሚል ርዕስ በአስራ አንድ ተከታታይ ክፍሎች በዚህ የመጦመሪያ መድረክ የቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከጉዳዩ አንገብጋቢነት አንጻር ዛሬ በቀጥታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከአባ ጳውሎስ በኋላ መሪዋ ማን መሆን አለበት? በሚል ርዕስ ለመወያያ መነሻ የሚሆኑ ነጥቦችን ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡
የቤተክርስቲያን ሥርዓት እንደሚያዝዘው አንድ ፓትርያርክ በሞት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የሚደረገውን አሰራር በጥቂቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ-ገፅ ላይ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱስ ሲኖዶስና ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምን ይላል?  ከተገኘው ለማየት እንሞክር፡-
አቡነ ቴወፍሎስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ


ምዕራፍ አራት
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ
አንቀጽ 13
ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ
1.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት ተመርጦ ይሾማል፡፡
2.    ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ በሚወስነው ቁጥር መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል፣
3.    ለፓትርያርክነት የሚመረጡት ዕጩዎች ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሲሆን ብዛታቸው ከሦስት ያላነሡ ከአምስት ያልበለጡ ይሆናል፡፡
4.    አስመራጭ ኮሚቴው እጩዎችን ጠቁሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀርባል፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ምርጫው እንዲካሔድ ይደረጋል፡፡
5.    መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች የአድባራት አስትዳዳሪዎች ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በዕድሜ ከሠላሳ ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምእመናን ተወካዮች እንዲሁም ዕድሜያቸው 22 አስከ 30 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤው የሚወከሉት ከአንድ ሀገረ ስብከት አሥራ ሁለት ሆነው በሥጋወደሙ የተወሰኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው፡፡
6.    የምርጫው አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይሆናል፡፡
7.    የተመረጠው ፓትርያርክ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትንና ቀኖናዋን ሊጠብቅና አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊያስተዳድር ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡
8.    ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 14
የፓትርያርኩ የማዕረግ ስምና መንበር
1.    ፓትርያርኩ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እገሌ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ይባላል፣ ስሙም በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ይጠራል፡፡
2.    ፓትርያርኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጨ አገር ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን መንፈሳዊ አባት ነው፡፡
3.    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበር በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ነው፡፡
አንቀጽ 15
የፓትርያርኩ ሥልጣንና ተግባር
1.    ፓትርያርኩ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል፡፡
2.    በዚህ ሕግ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡
3.    ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 እና በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 13 መሠረት ፓትርያርኩ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ሆኖ ኤጲስ ቆጶሳትን ይሾማል፣ እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ሲስማማበት ለብፁዓን ጳጳሳት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ይሰጣል፡፡
4.    በዚህ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት የተመረጡትን የሥራ ሓላፊዎች ይሾማል፤ በቀደምትነትና በታሪክ የታወቁትን የታላላቅ ገዳማት አበምኔቶችና የከፍተኛ አድባራት አስተዳዳሪዎች በየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት እየተመረጡ ሲቀርቡለት የማዕረግ ስም እየሰጠ ይሾማል፡፡
5.    ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የመንግሥትን ፈቃድ ማግኘት በሚያስፈልግበት ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ በተግባር ላይ ያውላል፡፡
6.    ቅዱስ ፓትርያርኩ በዓበይት ጉዳዮች ላይ ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ አያስወሰነ ይሠራል፡፡
7.    በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጐች፣ የተላለፉ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ሁሉ በተግባር ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡
8.    በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡትን ሕጐችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በፊርማው ያስተላልፋል፡፡
9.    ከመንግሥታውያንም ሆነ መንግሥታውያን ካለሆኑ /ቤቶች ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚቀርቡ ደብደቤዎች ወይም አቤቱታዎችን ደረጃቸውን ጠብቀው በሕግ መሠረት ይፈጸሙ ዘንድ ለጠቅላይ /ቤት ያስተላልፋል፡፡
10.    በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ለማገልገል ወይም የነፃ ትምህርት ለመማር የሚላኩ ካህናት በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 መሠረት ተመርጠው ሲቀርቡ እንዲላኩ ያደርጋል፡፡
11.    ከውጭ የሚመጡትን እንግዶች በውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቅራቢነት እየተቀበለ ያነጋግራል፡፡
12.    ፓትርያርኩ በውጭ አገር በሚደረግ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ለመገኘትና ጉብኝት ለማካሔድ በሚያስፈልግ ጊዜ ስለተልዕኮው ጉዳይ አስቀድሞ በቅዱስ ሲኖዶስና በቋሚ ሲኖዶስ ያስወስናል፡፡

አቡነ ተክለሀይማኖት ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ
 
አንቀጽ 16
የፓትርያርኩ ከማዕረግ መውረድ
1.    ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከተሾመ በኋላ የተቀበለውን ሓላፊነት በመዘንጋት፡-
. የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚያሰነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣
. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ከቁጥር 172 እስከ 208 በተደነገገው መሠረት በደለኛ መሆኑ ከታመነበት፣
. በቃሉ የማይገኝና በዚህ ሕግ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 7 ድንጋጌ መሠረት በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ያልጠበቀ በአጠቃላይ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነትን ያጣ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያስነቅፍ መሆኑ በትክክል ከተረጋገጠ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከሥልጣኑ ይወርዳል፤ በምትኩም ሌላ ፓትርያርክ ተመርጦ ይሾማል፡፡
2.    ከዚህ በላይ በተደነገገው መሠረት ከሥልጣኑ የተገለለ ፓትርያርክ በቀኖና ተወስኖ በገዳም ይቀመጣል፡፡
3.    ከሥልጣን የተገለለው ፓትርያርክ በገዳም አልቀመጥም በቀኖናም አልወሰንም በማለት እምቢተኛ ከሆነ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ይለያል፡፡
4.    ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ሥራውን በማካሔድ ላይ እያለ እሥራትና ግዞት ቢደርስበት ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትመራለች እንጂ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡
5.    ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ ፍትሕ መንፈሳዊ በሚያዝዘው መሠረት ይፈጸማል፡፡

አቡነ መርቆርዮስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ
 
አንቀጽ 17
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
1.    ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡
2.    የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደሥራው ሁኔታ እየታየ 40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይሆናል፡፡
3.    የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ተግባር
. ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉደዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር እየመከረ ያከናውናል፡፡
. በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ሆኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡
/ምንጭ፦ ሕገ ቤተ ክርስቲያን 1991 ./

አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ

ዛሬስ መሪያችንን ለመምረጥ ምን እናድርግ?

ከዚህ ለማየት እንደሞከርነው የአንድ ፓትርያርክ የምርጫ ሂደት ከ 40 እስከ 80 ቀናት ይፈጃል፡፡ በግብፅ አቡነ ሺኖዳ ከዚህ ዓለም ሲለዩ እንደተደረገው ማለት ነው፡፡ ግብፃውያን በዚህ ረገድ በጣም ጥሩ እና የዳበረ ልምድ አላቸው፡፡ ምዕመናኑ ሳይቀር የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ በጸሎት ከመትጋት ጀምሮ ሁነኛ ሰው ለፓትርያርክነት የበቁ ሰዎችን እስከመጠቆም ይደርሳል- የምዕመናን ድርሻ፡፡
አሁን የኛ ቤተክርስቲያን ባለ ድርሻ አካላት ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን እናንሳ፡-
  1.    የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን ቢያን በፀሎት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የፀሎት ጊዜ ቢታወጅ ጥሩ ነው፡፡ ከመካከላችን ንፅሐ ለቦና ያላቸው ሰዎች ጸሎታቸውም ኃይልን የምታደርግ ሰዎች፣ መነኮሳት፣ ደናግል ወዘተ አይጠፉምና፡፡ 
  2.     ቤተክርስቲያን የጸሎት ጊዜ ብታውጅም ባታውጅም ሁሉም ሕዝበክርስቲያን በጸሎት መትጋት ይኖርበታል፤ ስለ ኃጢያታችን ክፉ መሪ እንዳይታዘዝብን ኃጢያታችንን ይቅር እንዲለን ንስሃ እየገባን ከእግዚአብሔር ምሕረትን ዘወትር ልንለምን ይገባል፡፡ 
  3.  ቅዱስ ሲኖዶስ እና ሊቃነ ጳጳሳት የሚመርጧቸው አስመራጭ ኮሚቴ አባላትን ማንነት በትክክል ማጤንና ተገቢ የሆኑትን ሰዎች ብቻ መምረጥ አለባቸው፡፡ በቤተክህነቱ አካባቢ ያሉ ወሮበሎች ይህንን ዕድል ውስጥ ለውስጥ በመሽሎክሎክ ለመጠቀም የማይቆፍሩት ጉድጓድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ ይኖራቸዋል አንልም፡፡ 
  4.  ቅዱስ ሲኖዶስ የፖለቲካ አጀንዳ ካነገቡ ካድሬ-ነክ ሰዎች ጥንቃቄ ማደረግ ይኖርበታል፡፡ በ1983 እና በ1984 ዓ.ም በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ስለተከናዎኑት ታሪካዊ ጥፋቶች የተሟላ መረጃ ቢኖረን ምን አልባት የቤተክርስቲያን ለሁለት መከፈልና ሰላም ማጣት ምክንያቱ ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ 
  5.  ቅዱስ ሲኖዶስ እና ሊቃነ ጳጳሳት አስመራጭ ኮሚቴውን በቅርብ በመሆን ሂደታቸውን መገምገምና ሂስና መመሪያ መስጠትና ማስተካከል ቢችል እጅግ መልካም ነው፡፡ በጸሎት፣ በምክር፣ መረጃ በመስጠትና በመሳሰሉት ደግሞ ሁላችንም ከቅዱስ ሲኖዶስና ከአስመራጭ ኮሚቴው ጎን መቆም ይጠበቅብናል፡፡ 
  6.  ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ አስመራጭ ኮሚቴው የመስሪያ ክልሉን እንዳያጠቡት ማለትም አዲስ አበባና ዙሪያ ገባዋ ብቻ ለእጩዎች ፍለጋ እንዳትዳሰስ እሰጋለሁ፡፡ ሆኖም እጩዎች ከሊቃነ ጳጳሳትና ከጳጳሳት ብቻ ስለሆነ ብዙም ስጋት ላይሆን ይችላል ይህ ጉዳይ፡፡ 
  7.  ከዚህ ከፓትርያርክ ምርጫ ጋር ተያይዞ ሌሎች ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የሚከናዎን ከሆነ ግን በተራ ቁጥር 6 ላይ የተገለጠጸው ጉዳይ ተገቢው ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፡፡ የጳጳሳት ሹመት መዳረሻዎች ከአዲስ አበባና ከዋና ዋና ከተሞች ብቻ የመሆን ከፍተኛ አዝማሚያ አለ፡፡ በተለይም ለመንበረ ፓትርያርኩ ቅርበት ያላቸው እንደ ቅድስት ሥላሴ፣ መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ፣ መናገሻ ገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዎችጊስ፣ ግቢ ገብርኤል፣ ወዘተ ያሉትን አስተዳዳሪዎች በቀጥታ በመውሰድ መሾም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ስለዚህ በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች ብዙ ጥቅም ለማሯሯጥ ከከተማ ወደ ከተማ የማይዋዥቁትን የተረጋጋ መንፈሳዊነት የተላበሱ ገዳማውያንን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ የየአህጉረ ስብከት ሊቃነ-ጳጳሳትና ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የቤተክርስቲያን ጠበቃ ዋልታ መሆን የሚችሉ ሰዎችን ከየአህጉረ ስብከታቸው ከነ ሙሉ መረጃ በማቅረብ የሰው ረሃብ ያለበትን የጳጳሳት ምርጫ ሊያረኩት ይገባል፡፡ 
  8.  መንግስት ከቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ እጁን ማንሳት አለበት፡፡ ምን አልባት የፀጥታ አስከባሪዎች በአንድአንድ እሰጣገባዎች ውስጥ በመግባት ህግዎጦችን ወደ ህግ በማቅረብ ከምዕመናን ጎን ሎቆሙ ይገባ ይሆናል፡፡ ነገር ግን መንግስት በቤተክርስቲያን ውስጥ ምንም ዓይነት ዓላማና ግብ ሊኖረው አይገባም፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ ሆኗል ማለት ግን አይደለም፡፡ ነበርም አልነበርም ለማለት የተሟላ መረጃ ሊኖር ይገባልና፡፡ መንግስት ቤተክርስትያን ነፃ ሆና ወሳኝ መሪዋን በመምረጧ በምታገኘው መንፈሳዊ ዕደገት ሀገር ትባረካለች፤ ሀገር ታሪካዊ ቅርሶቿና ሞራላዊ ልዕልናዋ እንደተከበረ ይቆያል፤ ምዕመናን ግበረ ገብነትን በሚገባ ከተረጋጋች የፀጥታ ወደብ ከሆነችው ቤተክርስቲያን መማር ይችላሉ - እናም የሀገር አደራን በሚገባ ለመሸከም የተገቡ ይሆናሉ፤ የቱሪዝም ገቢና ሌሎች ከዚህ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው የብዙ ብዙ እሴቶችን በሚገባ ጠብቀን ለማቆየት እንችላለን፡፡ 

እናንተስ ምን ትላላችሁ ….?


…ይቀጥላል…

2 comments:

  1. በፅሁፉ ሙሉ ይዘት እሰማማለሁ፤ ግን አንድ ነገር ለኔ ግልፅ አይደለም፤- ያሉት መረጃወች እንዳሉ እንወሰድና ከአባ ጳውሎስ በፊት የነበሩት አባት በህይወት እያሉ ወደ ምርጫ መግባት ሌላ ታሪካዊ ስህተት መድገም ነው ባይ ነኝ !!! እንደኔ የቀደሙት አባት ወደቦታቸው መመለስ አለባቸው፤፤ ይህ ደግሞ የቤተክርስቲያንን ቀኖና ከመጠበቅ አንፃር ለህዝበ ክርስቲያኑ አንድ ትልቅ ድል ነው፤፤ ምርጫ ተደርጎ መልሰው ቢሰየሙ እንኳ ለኔ ከቀኖና ቤተ-ክርስቲያን አንፃር ትርጉም የለውም፡፤ በምርጫ እርሳቸውን መልሶ መሰየሙ ከተፅእነኖ አንፃር ቲኒሽ ጥቅም ቢኖረውም ግን ዞሮ ዞሮ ቀኖናውን ከማፍረስ ጋር ሲነፃፀር ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤መወዳደርም አይችልም፤፤ ደግሞ መጋፈጥ እንጅ ለዛ ብሎ ወደዛ አዝማሚያ ከተሄደ ትርፉ ትዝብት ነው የሚሆነው፤፤ እናም ይህ ባይሆን መልካም ነው ብየ አምናለሁ፤፤ እናንተስ???

    እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ይሁን!!!

    ReplyDelete
  2. what is the need to say ...if a comment liable to be confirmed for visibility is access denied. Glad to see so!

    ReplyDelete