አቡነ ቴወፍሎስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ |
ይህ ተከታታይነት ያለው ፅሁፍ
እስከ ክፍል አስራ አንድ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ይህንን ፅሁፍ አንባቢው ያለፈውን ክፍል ሳይረሳው በተከታታይ ሳምንታት
ከማቀረብ ይልቅ እየተጓተተ እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቷል፡፡ ይህ ባለመሆኑ በእግዚአብሔር ስም ይቅር እንድትሉኝ በትህትና
እጠይቃለሁ፡፡ ያለፉትን ክፍሎች ለመጎብኘት
ከፈለጉ የሚከተሉትን ጠቋሚዎች ተጠቀሙ፡፡
1. ክፍል አንድ
4.
ክፍል አራት
9.
ክፍል ዘጠኝ
10.ክፍል አስር
11.ክፍል አስራ አንድ
ባለፈው ክፍል በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን
የነበረውን የቤተክርስቲያን ታሪክ ቃኝተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ቤተከርስቲያን ከአብዮታዊ ደርግ መነሳትና ከዚያ በኋላ የነበረውን
ሁኔታ እንቃኛለን፡፡
በ1953 ዓ.ም በሁለቱ ወጣት የኢትዮጵያ ለውጥ
ናፋቂ ወንድማማቾች በግርማሜ ነዋይና በመንግስቱ ነዋይ መሪነት በእነ ጀነራል ወርቅነህ ገበየሁ አጋዥነት የተከናወነው የመፈንቅለ
መንግስት ሙከራ ተከትሎ በሀገሪቱ የለውጥ ፈላጊ ወጣቶች እየተበራከቱ በመሄዳቸውና ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ብዝበዛና ጭቆና
ያስመረረው ያረጀ ያፈጀ ፊውዳል ሥርዓት መሸከም የሰለቸው የተለያየ የሕብረተሰብ ክፍል በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በገበሬዎች አመፅ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተያይዞም በነዳጅ ዋጋ መጨመር የታክሲ ሾፌሮች፣ የተሻለ የኢኮኖሚ ባለመኖሩ ተማሪው፣
መምህራኑ፣ ጦር ሰራውቱና ሌሎቹም የህብረተሰብ ክፍሎች በመታከላቸው ይህን የለውጥ ነውጥ የሚያስባብር አካል ባለመኖሩ ለጊዜው
ውጤታማ ሥራ መስራት ሳይቻል የተወሰነ ጊዜ ቆይቶ መጨረሻ ላይ አዲስ አበባ በሚገኘው በአራተኛ ክፍለ ጦር በእነ ሻለቃ አጥናፉ
አስተባባሪነት ለተለያዩ የጦር ሻለቆች በጊዜው የነበረውን ለውጥ ለመወያየት እንዲቻል ከአራተኛ ክፍለጦር መልዕክት በመላኩ የጊዜው
ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማሪያም ሐረር የሚገኘውን የሶስተኛ ክፍለ ጦር እየመሩ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ የሌሎቹም ክፍለ ጦር ተወካዮች
እንዲሁ፡፡
በዚህ ሁኔታ የተጀመረው የለውጥ ናፋቂው
ሕብረተሰብ ለውጥ አራማጅነት ባለታሰበ ሁኔታ በጦር ሰራዊቱ በመመራት ንጉሱን ካልጋቸው አንሸራቶ ካወረደ በኋላ “ያለምንም
ደም ኢትዮጵያ ትቅደም”
ብሎ የጀመረው ደርግ በመንግስቱ ኃይለማሪያም መሪነት የአብዮቱ ተግዳሮት ተደርገው የተወሰዱ የርዕዮተ ዓለም
ልዩነቶች ሁለቱን የአንድ እናት ኢትዮጵያ ልጆች በሁለት ጐራ ከፍሎ ደም አፋሰሳቸው፡፡ በዚህ ወቅት ማንኛውም የአብዮታዊ ደርግ
ተግዳሮት ናቸው ተብሎ የሚታሰቡ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ድርጅቶችና ሌሎቹም ከመቃብር በታች ለማድረግ በማለም የቤተክርስቲያንን
በሮችም አንኳኩቶ ሥራዎቿን ሁሉ በአብዮታዊ ደርግ መርህ ለመቃኘት አሰኘው፡፡ በዚህም የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ አቡነ ቴወፍሎስ
በወቅቱ ቤተክርስቲያን የማንንም ጣልቃ ገብነት ሳትሻ ራሷን ችል የራሷን አመራርና አስተዳደራዊ ሥራ መስራት እንዳለባት በመገንዘብ
የወቅቱን ደርግን ሳያስፈቅዱ ሊቃነ ጳጳሳትን በመሾማቸው ተይዘው በግዞት ቤት እንዲቆዩ ካደረገ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱን አባቶች
ይሙት በቃ በግድ አስወስኖ ሳይሞቱ በላያቸው ላይ ሌላ ፓትርያርክ አስመርጦ የግፍ አገዳደል አስገደላቸው፡፡ ሀገሪቱን በሃምሳ
ዘጠኙ የኃይለ ስላሴ ሚኒስትሮችና መኳንንት ላይ ደም ማፍሰስ የጀመረው ደርግ በኋላ በቀይ ሽብርና በየ አጋጣሚው በሚሰዋቸው
ሰዎች ደም ሀገሪቱ በደም ታለለች፡፡ በኢህአፓና በደርግ መካከል በተደረገው ሽኩቻ ለሀገሪቱ የለውጥ ሀዋሪያ መሆን የሚችሉ
የዩኒቨርሲቲና የከፍተኛ ሁለተኛ ተማሪዎች በያሉበት እየታደኑ የጥይት ራት ሆኑ፡፡ የኢትዮጵያ የሚቀጥሉት 50 ዓመታት የለውጥ አድራጊነት
መንሰፈስና የእድገት ጉዞ አከርካሪው ተመትቶ እንዳይነቀሳቀስ ወድቆ ቀረ፡፡ በዚህ ዘመን የለውጥ ሐዋሪያነት የተመናመነ፣ የግፍ
አገዛዝን እምቢኝ የሚል የጠፋው የዚያ ዘመን ጠባሳ ሰለባዎችና የእነርሱ ልጆች በመሆናችን ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደርግ በሕብረተሰባዊነት
ርዕዮተ-ዓለም በመንተራስ የእብሪቱ መጨረሻ ጫፍ ላይ የደረሰበትን ፈጣሪ የለም፤ የእምነት ድርጅቶች መኖር ለሀገር እድገት
አዝጋሚነት ምክንያት ሆኖ በመወሰዱ ወጣቶችና ልሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የእምነት ሥርዓታቸውን እንዲተላለፉ፣
ፆም እንዳይጾሙ፣ ቤተክርስቲያን እንዳይሰባሰቡ፣ ወዘተርፈ በተለያዩ ስልቶች እቅዱን ማስፈፀም በመጀመሩ በቀጥታ የኃይል እርምጃ በመውሰድ፣
የርዕዮተ-ዓለም የማስረፅ ሥራ መስራት፣ የልዩ ልዩ የልማት ማኅበራት አባልነትን ለማግኘት እምነት-የለሽ መሆንን እንደ ቅድመ ሁኔታ
ማስቀመጥ፣ የቤተክርስቲያንን ይዞታዎች ሁሉ መንጠቅና ምጣኔ-ሀብታዊ አቅም ማሳጣት፣ በልዩ ልዩ ስብሰባዎች ቤተ እምነቶችን
ማንቋሸሽና ማጥላላት ወዘተ ነበሩ፡፡ ይህ ጊዜ በተለይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ደርግ ጦር ሰብቆ፣ ወገብ ታጥቆ የተነሳበትና
የባህል አብዮት በወጣቱ ላይ እንዲሰርጽ በተገኘው መንገድ ሁሉ የተጋበት ዘመን ስለነበር የለውጥ ምንጭ የመፃያቱ ጊዜ ባለቤት የነበረው
ወጣቱ ከእናት ቤተክርስቲያን ተለይቶ ምልክት የለሽ፣ ስደተኛ ሆነ፤ ስደቱም ተመልሶ ላይመጣ ትቷት የሄደውን እናት
ቤተክርስቲያኑን ኢየሩሳሌም ሆይ! ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ …. ላይል ምሎ በሞት የተለዩትን ወዳጅ ያህል ከቤተክርስቲያን ራቀ፡፡
ወጣቱ ትውልድ በዚያ ጊዜ
ትንሽ የቀረችው ወኔ እናት ሀገሬ ኢትዮጵያ የሚል ጭላንጭል ብርሃንም በወቅቱ ለሃገር ሳይሆን የአብዮቱ ዘብ የቆሙ የጥፋት
አምባሳደሮች ሀገሪቱን በደም እንድታቅላላ በማደረግ ያለተመጣጠነ ኃይል ለጥቂጥ የኩራዝ ብርሃን ላይ የአውሎ ነፋስ በሚያህል
ኃይል እፍ ድርግም አደረጉት፡፡ ከዚያ በኋላ ወጣቱ የተነሳበትንና የሚደርስበትን በውል ሳይረዳ በቀላሉ ነፋስ በነፈሰበት የሚነዳ
የጥፋት ሱሶች ተጠቂና ተስፋ የቆረጠ ሆነ፡፡ የደርግ ዘመን የሥነ-ልቦናና የሞራል ስብራት የሁለትና የሦስት ትውልድ የማይጠግነው
ታላቅ ውድቀት ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ወጣቶች ከጥቂቶቹ በስተቀር የአልኮል መጠጥ ሱሰኞች፣ የሲጋራ ሱስ ባሮች ሆነው
የተከታዩን ትውልደ መሪና አቅጣጫ አመላካች ባለመኖሩ ጥዝጣዜው ይኸው እስከዛሬ ዘልቆ እስከ አጥንታችን ህመሙ ይሰማናል፡፡
ደርግ በኦርቶዶክስ
ቤተክርስቲያን ላይ በጠላትነት የተነሳባትን ያህል በሌሎች ቤተእምነቶች ላይ ትኩረት ባለማድረጉ በተለይ ለኢትዮጵያ መጤ ቤተ
እምነቶች አንፃራዊ ነፃነታቸውን በመጠቀም የቤተክርስቲያንን ልጆች እየነጠቁ የአዳራሾቻቸው ታዳሚዎች በማደረግ አያሌ የጥፋት
መላዎችን በማቀድና በመተግበር ከፍተኛ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ በ1940ዎቹ የተጀመረው የምዕራባውያን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን
ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጥቁር ፅዮናዊነትን ታስከትላለች በሚል ስጋት በወለደው ቤተክርስቲያኗን ከመቃብር በታች ለማድረግ ጥረት
እራሱን እየወለደ በደርግ ዘመንና አሁን ባለንበት ዘመን እንደ ሰደድ እሳት ቤተክርስቲያኗን ከውስጥ እና ከውጭ አየለበለበ
ይገኛል፡፡
በደርግ አገዛዝ ዘመን
በዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሐይማኖታቸውን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለለፍ ወይም በደርግ ዘመን
የነበረውን ሐይማኖት የለሽ ህብረተሰብ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ባለመቀበል በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተለያዩ ቅዱሳን ስም ፅዋ
ማኅበራትን መስርተው ቅዱሳንን እየዘከሩ ሲቆዩ በ1977 ዓም በተከሰተው የሀገሪቱ ረሃብ የተጠቃውን የትግራይና የወሎ ሕዝብ በለም
አካባቢዎች ለማስፈር በነበረው እንቅስቃሴ በመተከል ዞንና በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ለም ቦታዎች የመንደር ምስረታ ሥራ ይከናዎን
ነበር፡፡ በዚህ የመንደር ምሥረታ ሥራ ውስጥ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተለያየ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር፡፡ ከእነዚህም
መካከል እናቶች የቤት ዕቃ ማሟላት ኃላፊነት ተጥሎባቸው ስፌት ሰፍተው እንዲያስረክቡ ኮታ ተጥሎባቸው ስፌት በእያንዳንዱ እማወራ እጅ ተሰፍቶ
ተሰብስቧል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ጎልማሶች ደግሞ በመንደር ምስረታው ቦታ ተወስደው ቤት የመስራት ኃላፊነት
ስለ ተጣለባቸው በመተከልና በሌሎችም ቦታዎች እነዚህ ተበታትነው የቅዱሳንን ስም በየዶርማቸው ሲዘክሩ የቆዩ ተማሪዎች ለመጀመሪያ
ጊዜ በህብረት ሀገራዊ ራዕይ እንዲሰንቁ እርስ በእርስ ተነጋግረውም ተመሳሳይ አቋም እንዲያራምዱ ዕድል ፈጠራላቸው፡፡ በዚህ
የመንደር ምስረታ ጊዜ የነበረው መስተጋብር ግን ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶ ያልተሰራበት ስለነበረ ወዲያው ሀገራዊ ተቋም እውን
እንዲሆን አላስቻለውም፡፡ በየግላቸው ሀገራዊ ራዕይ አንግበው የተለያዩት እነዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በተለያዩ
ገዳማት በመሄድ ከገዳማዊ አባቶች ትምህርት፣ ምክርና ቡራኬ እየተቀበሉ የክረምት ጊዜያቸውን ማሳለፍ በመጀመራቸው ለሚቀጥሉት
ተከታይ የየተቋሞቻው ተማሪዎች ራዕያቸውን በማካፈል ከዓመት ዓመት ተሸጋገረ፡፡ በዚህ ሁኔታ የክረምት እረፍት ጊዜያቸውን
የሚያሳልፉ ተማሪዎች መካከል አንድ አንዶቹ በዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እየሄዱ በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ
ከነበሩት ከአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ትምህርትና ቡራኬ፣ እንዲሁም ምክር በማግኘት እነዚያ ተማሪዎች በራዕያቸው ትልቅና ዘመን
ተሻጋሪ እንዲሆኑ አስቻሏቸው፡፡
የደርግ መንግስት በሶቪየት ህብረት
መፈረካከስ ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ትግልና በውስጥም በኃይል የታሰረው ስልጣን እየላላና አቁዋሙም አየዋዠቀ እን ሻለቃ አጥናፉ አባተ ድብልቅ የኢኮኖሚ ስርዓት ነው የሚበጀን በማለታቸው ብቻ ለሀገሪቱና
ለአብዮቱ መሳካት ያደረጉትን ውለታ ሁሉ ከገደል ከቶ እንዲረሸኑ መደረጋቸውን ረስቶ በ1982 ዓ.ም ድብልቅ ኢኮኖሚና ስም ለበስ
ዲሞክራሲ በማዋቀር ደርግ ከስሞ ቢሔራዊ ሸንጎ እንዲመሰረት መደረጉ የደርግን የውድቀት ዋዜማ እንደደረሰ አመላካች ነበሩ፡፡ ደርግ
ከስሞ የመንግስቱ ኃይለማሪያም ብሔራዊ ሸንጎ ሲመሰረት የደርግ ሥርዓት ከስም ለውጥ በስተቀር ያከናወናቸው ለሀገሪቱ የሚበጁ ለውጥ
ባለመኖሩ ከ1982 ጀምሮ ደርግ እንደ ሶቪየት ሕብረት ለመውደቅ እየተንገዳገደ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ጊዜ ደርግ በ1983 ዓ.ም የመጨረሻ አማራጭ የትግል ስልት በመንደፍ
ከነጻ አውጭ ግንባሮች ጋር የሞት ሽረት ጦርነት ለማከናዎን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በብላቴ የጦር ማሰልጠኛ ተቋም ሰብስቦ ወታደራዊ
ስልጠና መስጠት ሲጀምር በ1977 ዓ.ም በመንደር ምስረታ የተገኘው ዓይነት ዕድል ዳግም በመገኘቱ በዚህ ወቅት ከእነ አባ ጎርጎሪዎስ
ካልዕ የተገኘው መንፈሳውና ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬና እውቀት ታክሎበት በብዙ ቅዱሳን ስም ሲዘከር የቆዩት የየግቢው የፅዋ ማኅበራት
አንድ ሀገር አቀፍ ማኅበርን አስገኘ፡፡ የእነዚህ ተማሪዎች ሕብረት ቀጥሎ ከደርግ ውድቀት በኋላ በ1984 ዓ.ም በአቡነ ገብርኤል
ሰያሚነት ሁላችሁም የምትዘክሩት ቅዱሳንን ነውና ማኅበረ ቅዱሳን ተብሎ እንዲሰየም በማለት ባቀረቡት ሐሳብ መሰረት ግንቦት 1 ቀን
1984 ዓ.ም የቤተክርስቲያን ባለራዕዩ ማኅበር ተመሰረተ፡፡
ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ነቢያት፣
ሐዋሪያት፣ ደናግል መነኮሳት የሚዘከሩበት በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ተብሎ በመሰየም መጀመሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች
እናት ቤተክርስቲያንን እንዲያውቁ ትምህርት በማስተማር፣ የተለያዩ የሥነ-ልቦና የምክር አግልግሎት በማከናዎን፣ እርስ በእርስ እንዲማማሩና
እንዲረዳዱ በማድረግ ወጣቱ ትውልድ በደርግ ዘመን እግዚአብሔርንና እናት ቤተክርስቲያንን ባለማወቅ የተጎዳውን ጉዳት በዚህ በእኛ ዘመን እንዳይደገም
ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ደርግም በቤተክርስቲያንና በሀገሪቱ
ፈርጀ-ብዙ ችግሮችን ለ17 ዓመታት ሲያደርስ ከቆየ በኋላ የተደገፈበት ሥርዓት በሩሲያ ወድቆ ሲንከታከት እርሱም ከሀገሪቱ ተወገደ፡፡
የ17 ዓመታት መሪው መንግስቱ ኃይለማሪያምም ወደ ወዳጅ ሀገሩ ወደ ዚምባብዌ በረረ፡፡ የደርግ ሥርዓትም በዚሁ አከተመ፡፡ ነገር
ግን በደርግ ዘመን አንፃራዊ በሆነ እይታ ሲታይ ያደረሰው ጥፋት ሚዛን የሚደፋ በመሆኑና በዘመኑም የነበረው ከሦስት አቅጣጫ የነበረው
ጦርነት ፋታ ስለነሳው ሙሉ ኃይልና አቅሙን በሙሉ ለሀገር እድገት ማዋል ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህም ሆኖ በመሰረተ ትምህርት በሀገሪቱ
ድንቁርናን ለማጥፋት የወሰደው እንምጃና የልማት ውጥኖቹ በታሪክ ማሕደር ውስጥ ከበጎ ጎኖቹ በአወንታዊነት የሚታሰብባቸው ጥቂቶቹ
ናቸው፡፡
…ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment