Monday, September 10, 2012

የታላቅ ሕዝብ አዲስ ዓመትና የአዲስ ህይወት ዕቅድ

Adey flowers


እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴወስ በሰላም አደረሳችሁ!!!
የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ፤ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ፡፡ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፤ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፡፡መዝ. ፷፬፣፲፩፲፪
ያደይ አበባ ሲፈካ፣ የሰማይ ብሩሕነት በወፎች ዝማሬ ታጅቦ የንጋት ኮከብ ብርሃን ሲታይ፣ ያዲስ ዓመት ብስራት ነጋሪዎች በከበሮ በፅናፅልና በሌሎችም ጣዕመ ዝማሬ ሲያሰሙ፣ የልባችን በሮች ለብዙ ነገሮች ይከፈታሉ፡፡ አንድ አንድ ሰዎች ማንነታቸውን ዘላለማዊ ህይወትን ለማግኘት በሚያስችል መልኩ እራሳቸውን ለንስሃና ለስጋወደሙ ሲያዘጋጁ፣ መልካም አገልግሎት የተጠማን ሕዝብ በቀና ልቦና ለማገልገል፣ ስንፍናና ቸልተኝነት የሚባሉ የሀገር ጉስቁልና መንስኤዎችን አሽቀንጥሮ ለመጣል፣ ለበጎ ነገር ሁሉ የተዘጋጁ በውስጥ በአፍአ የቀና ለመሆን ይታጠቃሉ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ አንዳንዶቻችን የክረምት ንጋት ነጋሪት ሲጎሰም፣ የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ በተራሮች ደምቀው መታየት ሲጀምሩ ተጨማሪ የኃጢያት በሮችን ለመክፈት፣ ተጨማሪ የዘረፋ አካዉንቶችን ለማዘጋጀት፣ አዲስ የማጭበርበሪያ ስልቶችን በመንደፍ እንጀምራለን፡፡
የታላቅ ሕዝብ ታላቅነት ከላይ ከታዩት ሁለት ፀባያት የመጀመሪያዎቹ በሆኑት መልክ የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት የጥቁርነት ከፍ ያለ ማማ፣ የቀጥተኛ ሐይማኖት ምስክርና ባለቤት፣ የሐዋሪያት ትምህርት ህያዉ በሆነ ሐይማኖታዊ ባህል ህልው ሆኖ እንዲኖር ያደረገ፣ የጥንት አዝማናት አቆጣጠርና የሥነ-ፈለክ ምርምር ባለቤት፣ የውብ ኪነ-ሕንጻ፣ የፊደላት፣ የሥነ-ጽሁፍ፣ ሥነ-ስዕል፣ ሥነ-ቃል ባለቤትና ባህረ-ጥበባት ማለት ነው፡፡ ለአንድ ሐገር ሕዝብ ሁለት ዓይነት ጥበብና ሐብት አለው፡፡ እነዚህም፡-
. ቁሳዊ ጥበብና ሀብት፡- ቁሳዊ እሴቶች አንድ ሀገር በዜጎቹና በጠቅላላ በሕዝቡ እንዲሁም ያንን ሕዝብ በሚያስተዳድረው መንግስት ቁጥጥርና ባለቤትነት ያለ ሕንፃ፣ መሬት፣ ገንዘብ፣ የመገልገያ ቁሳቁስና በአጠቃላይ ከሚዳሰስና ከሚጨበጥ ነገር የተሰራ ማንኛውም ነገር ሲሆን እነዚህን ነገሮች ለመስራትና ለመጠቀም የሚያስችል ዕውቀትና ጥበብ በሙሉ በዚህ ምድብ ውስጥ ይጠቃለላል፡፡ ዓለም አድሎዋዊ በመሆኗ የሯሷ ለሆነው ታደላለች፡፡ ቁሳዊ ሀበትና ጥበብ በብዛት ያለው ሐብታምና ኃያል እንደሆነ ትሰብካለች፡፡ በዚህም ምዕራባውያንና ጥቂት የሩቅ ምስራቅ ሀገራት በዚህ መስፈርት የሰለጠኑ ያደጉ የተመነደጉ እንላቸዋለን፡፡
.  መንፈሳዊ ጥበብና ሀብት፡- ይህ ደግሞ ሰው ከእግዚአብሔር ከፈጣሪው ጋር በሚያደርገው መስተጋብር በመገለጥ (Revealation) የሚሰጥ በተለያዩ የቅድስና ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚያገኙት ፍፁም እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር በአንድነት ያለበት ነው፡፡ በዚህ ጥበብና ሀብት ያሉ ሰዎች በእርስበእርስ ኑሮዋቸው ሰላም፣ መቻቻል፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብ፣ ለራስ ያለማድላት ወዘተ ፀባያት የሚታይባቸው፣ በመከራና በችግር ጊዜ እጅግ በጣም ጠንካራ ሥነ-ልቦና ያላቸው፣ ዘላለማዊ ሕይወትን ወራሽ ስለመሆናቸው ምሉዕ እምነትና ተስፋ ያላቸው በመሆኑ ለቁሳዊ ሀብት ፍቅር የሌላቸው ነገር ግን ስንፍናን የሚጠሉና በራሳቸው ላይ እንዳይሰለጥን የሚተጉ በመሆናቸው ጊዜያቸውን በዋዛ ፈዛዛ የሚያሳልፉ ባለመሆናቸው ከጸሎትና ከአገልግሎት የተረፋቸውን ጊዜ በሙሉ በሥራ ላይ በማዋል ቁሳው ሀበት ማፍራት የሚችሉና የሚያፈሩ ነገር ግን ይህንን ቁሳዊ ሀበትና ጥበብ ከቁመተ-ሥጋና በሕይዎት ለመቆየት ከሚያስፈልጋቸው ውጭ ለተጨማሪ የፅድቅ ሥራ የሚያውሉ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ ጥበብና ሀብት ቁሳዊ ጥበብና ሀብት አያስፈልግም የሚል ፅንፍ የለውም፡፡ ነገር ግን ቁሳዊ ጥበብና ሀብት ለመንፈሳዊ ጥበብና ሀብት ማግኛ ለበጎ ሥራ መስሪያ መዋል ሲገባው ዘላለማው ሞትን የምታመጣ ሀጢያትን የምንገዛበት መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ ለሁለተኛው የሀብት ዓይነት የበለጠ ፍቅርና ትጋት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ቁሳዊ ሐብትና ጥበብ ጊዜያው ደስታና  ምቾት ሊሰጠን ቢችልም ዘላለማዊ ሕይወትን የምናገኘው ከሞት በኋላ ሌላ ሕይወትን እንድንኖር የሚያግዘን፤ በምድርም ዘለቄታ ያለው አእምሯዊ እርካታ፣ ደስታና ሀሴት የምናገኘው የመንፈሳዊ ጥበብና ሀብት ባለቤት ስንሆን ነውና፡፡ በዚህ መስፈርት መሰረት ዓለም ደሃና ሀብታም የሚባል ምድብ የላትም፡፡ መዳቢው እግዚአብሔር ቢሆንም ዓለም ወደደችም ጠላችም የአንድ ሐገር ታላቅነት የሚለካው ባለው መንፈሳዊ ልዕልና ነው፡፡ እንግዲህ አሜሪካን የመሰሉ ሀገራት ሀብታምና ኃያል ሲሆኑ ታላቅ የሚባል ሕዝብ የላቸውም፡፡ ኃያልነትና ታላቅነት ለየቅል ናቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጡምራ መድረኩ እንዳስነበበን፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት ከአብርሃም ዘመን በፊት ጀምሮ እንደነበረ እስራኤል በአምልኮ አመንዝራነቷ የተለየችውን እግዚአብሔርን በአብርሃም በኩል በፍጥረታት በመመራመር ስታገኝ ኢትዮጵያ ግን መልከ ፄዴቅን የመሰለ ካህን ወደ ኢየሩሳሌም ልካ ኢየሩሳልምን የመሰለች ከተማ መስርቶ የሳሌም ንጉስ ሆኖ ከአብርሃም የእጅ መንሻ ተቀብሏል፤ ኢትዮጵያም በመልከ ጼዴቅ እጅ እስራኤልን ባርካለች፡፡ ይህም የሚያሳየው በውል ከታወቀው ጊዜ  ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት ከአራት ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ታሪካዊ ማስረጃዎችን ባለመፈለጋችን ታሪካችንን የተቆነጻጸለ አደረግነው እንጅ አምልኮተ እግዚአብሔር ከአዳም ጀምሮ ሳይቋረጥ እንደ ጅረት ውሃ የፈሰሰባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች እንገነዘባለን፡፡ ለምን ቢባል ኢትዮጵያ የኖኅ የልጅ ልጅ ኩሽ (ኢትዮጲስ) የከተመባት ሀገር በመሆኗ አምልኮተ እግዚአብሔር ደግሞ እስከ ኖኅና ልጆቹ እንዲሁም እስከ ልጅ ልጆቹ ሳይቋረጥ የቀጠለ መሆኑን መፅሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ በመኖሩ ነው፡፡ እንግዲህ በኩሽና በዘመነ መልከ ጼዴቅ መካከል ያለውን ዘመን በጥሞና ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን አመክኒዮዋዊ በሆነ መልኩ ከተመለከትነው በዚህ ዘመን መካከል አምልኮተ-እግዚአብሔር ቢቋርጥ ኖሮ አምልኮተ-እግዚአብሔር ከመልከ-ጼዴቅ ዘመን መድረስ የሚችለው እንደ አብርሃም እግዚአብሔርን ፈልጎ ያገኘ (የተገለጠለት) ሰው አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ ይህንን ታሪክ ደግሞ ተፅፎ አላገኘንም፡፡ ይህም የሚያሳየው አምልኮተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ አልተቋረጠም ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት ዘመናት ከዓለም ዕድሜ ጋር የሚተካከል ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህም ያልተቋረጠና ያልተበረዘ አምልኮተ እግዚአብሔር የኖረች ኢትዮጵያ በኋላ የዓለም መድኃኒትን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘች እስራኤልን ሦስት ጊዜ ባርካታለች ወይም ከውድቀት አንስታታለች ወይም ደግሞ ከውድቀት አገግማ አሕዛባዊ ጠባይዋን ትታ ተመልሳ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንድትመለስ ረድታታለች፡፡ እነዚህም፡-
.  መጀመሪያ አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ የእጅ መንሻ አቅርቦ በዘላለማዊ ክህነት በአንብሮተ ዕድ ያልተሾመ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ በሆነው በኢትዮጵያዊው ካህን መልከ ጼዴቅ የተባረከ ጊዜ ነው፡፡
. ሁለተኛው ሙሴ ወደ ኢትዮጵያዊው ካህን ዮቶር ከግብጽ በተሰደደ ጊዜ ክህነትን፣ የህዝብ አስተዳደርንና መሪነትን፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን ከካህኑ ዮቶር የተማረ መሆኑ በኋላም እስራኤልን እየመራ ወደ ከነአን ባህረ ኤርትራን ከፍሎ ሲያሻግራቸው የእስራኤልን አለቆች በሻለቃ፣ በመቶ አለቃ፣ በሃምሳ አለቃ፣ በአስር አለቃ ወዘተ ከፋፍሎ የመሪነት ተዋረድን እንዲሰራና እስራኤልን በአግባቡ መርቶ ከርስት አገር እንዲገቡ ታላቅ የአማካሪነት ጥበብን የሰራ ኢትዮጵያዊው ካህን ዮቶር ነው፡፡
. ሦስተኛው እስራኤል ወደ ባቢሎን ተማርከውበወረዱ ጊዜና ኢየሩሳሌም በተቃጠለች ጊዜ፣ የቀሩት አስሩ የእስራኤል ነገዶችና ከተሞቻቸውም በአሶራውያን በተማረኩና በተመዘበሩ ጊዜ እስራኤል ከሐይማኖታዊ ቅርሶች በእጆቻቸው የቀሩ ምንም አልነበራቸውም፡፡ መፅሐፍቶቻቸውና ንዋያተ ቅድሳቶቻቸው፣ እንዲሁም የሰለሞን ቤተመቅደስ ተቃጠሉ፡፡ የእስራኤል የምርኮ ዘመን ከአንድ ትውልድ የሚረዝም ስለነበር እስራኤል ተመልሰው ነጻ ሳይወጡ፣ በቃል በረበናት የተጠኑ መፃሕፍት እንኳን ተመልሰው ሳይጻፉ ብዙዎች ረበናት በማረፋቸው እስራኤል የኦሪት መፃሕፍት ከሙሴና ሔኖክ እስከ ሰለሞን ያሉት መፃሕፍት በሙሉ ጠፉባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉስ መልእክተኞች ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት፣ ስለ ሐይማኖታዊ ቅርሶች ውድመት ሊጠይቁ፣ ሊያፅናኗቸው፣ ስለ መፅሐፍት ሁኔታ ሊጠይቋቸው ከምርኮ ቦታ ባቢሎን በመሄድ ተገናኟቸው፡፡ በምርኮ ያሉት እስራኤላውያንም የደረሰባቸውን በሙሉ ለመልእክተኞች አስረድተው መፃሕፍትም በሙሉ መውደማቸውን ነገረው መልእክት አስይዘው ወደ ኢትዮጵያ መልሰው ለከዋቸዋል፡፡ በኋላ ከባቢሎን ምርኮ አልፎ  የነጻነት ዘመን ሲተካ በንጉስ ዘሩባቤል መሪነት የሰሎንን ቤተ መቅደስ የሚመስል አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ቤተ መቅደስ ሲታነፅ የኢትዮጵያ መልእክተኞች የደስታና የነፃነት ዘመንን እግዚአብሔር ስለሰጣቸው ለእስራኤል እንኳን ደስ አላችሁ ለማለትና ከሰለሞን በኋላ የተጻፉ የነቢያት መጻሕፍት እንዲልኩላቸውም ለመጠየቅ መልእክት ከንጉሱ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ እስራኤላውያንም ከሰለሞን በኋላ የተጻፉ መጻሕፍትን አሲዘው ከሙሴ እስከ ሰለሞን ያሉትን መጻሕፍት በምርኮ ዘመን የጠፉባቸው በመሆኑ የራሳቸውን ልዑካን በመላክ ከኢትዮጵያ ወስደዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የእስራኤል ኦሪትን ከጥፋት ታድጋለች፡፡
ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የታላቅ ሕዝብ ታላቅ ሀገር የምትባለው፡፡ እንግዲህ ስለዘመን አቆጣጠራችን ሰፊ በመሆኑ ብዙ ነገር ልል አልወደድኩም፡፡ እናንተም የኢትዮጵያን ዘመን አቆጣጠር በመንፈሳዊ ጥበብ መሰረትነት የተሰራ ከሰዋዊ አመክንዮ ነጻ የሆነ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ትረዳላችሁ የሚል ግምት አለኝ፡፡ ከአውሮፓ ዘመን አቆጣጠር የተለየና የተሻለ የሚያሰኘው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ባህር ሐሳብ የሚለውን የቤተክርስቲያናችን አንድ ሰፊ ትምህርት (ስለ ሥነ-ፍጥረትና ዘመናት አቆጣጠር እንዲሁም ሥነ-ፈለክ በሚመለከት) የቤተክርስቲያን ሊቃውንት መጻሕፍትን ፅፈዋል፡፡ እነርሱን ማንበብና ስለ ዘመን አቆጣጠራችን ዕውቀታችንን ማስፋት ይቻላል፡፡
ነገር ግን አዲስ ዘመን ሲመጣ የዚች ታላቅ ሀገር ታላቅ ሕዝብ ታላቅነቱን የሚያስቀጥል ታላላቅ የሕይወት ዕቅዶችን ማቀድ ይጠበቅበታል፡፡ ያሳለፍነው ዓመት በኛ ሀገር ብዙ ክስተቶችን ያስተናገድንበት ዘመን ሆኖ አልፏል፡፡ የሁለቱ መሪዎቻችን በሥጋ ከኛ መለየት ግን ከሁሉም ዐብይ ጉዳይ ሆኖ በአእምሯችን ተቀርጾ ቀርቷል፡፡ ከእነዚህ ያለፈ ዘመን ክስተቶች መማር ያለብን ትላልቅ ነጥቦችም ይኖራሉ - መጪው ዘመንን ስናቅድ፡፡ አንድ የታክሲ ላይ ጥቅስ እዚህ ላይ ላስታውሳችሁ፡፡ እንደምትኖር ሆነህ ሥራ፤ እንደምትሞት ሆነህ ኑር፤ይላል፡፡ ለሚቀጥለው ዘመን ስናቅድ መልካምና በጎነትን የበለጠ እያዳበርናቸው ክፉነትን፣ ጨካኝነትን፣ ስግብግብነትን፣ አመንዝራነትን፣ ጥልን፣ አድመኝነትን፣ ክርክርን ወዘተ አስወግደን በአንጻሩ ደግሞ መቻቻልን፣ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን፣ አንድነትን፣ ሰላምን፣ መተማመንን ወዘተ ልናፈራ የምንችልባቸውን ዕቅዶችን ማቀድና መተግበር ያስፈልገናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከመቼውም በላይ ከጥንት ከአዳም አባታችን ጀምሮ ሳይቋርጥ የቆየው አምልኮተ እግዚአብሔር ከደርግ ዘመን ጀምሮ አደጋ የተጋረጠበት በመሆኑ ሺህ ዓመታትን አቋርጦ ከኛ ዘመን የደረሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት ምንጭ አምልኮተ እግዚአብሔር የምንፈፅምበት (በሐዲስ ኪዳን ክርስትናችን) እንዳይጠወልግ እምነትና መልካም ምግባራችንን የምናሳድግበት፣ ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳን ህብረት የለየንን ኃጢያታችንን በንስሃ የምንታጠብበትና ከዚያም ለስጋወደሙ የምንበቃበት፣ ጋብቻና ሌሎችንም ማኅበራዊ ህይወታችንን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና በሚፈቅደው መሰረት ለማከናወን በቁርጥ ህሊና የምንወስንበት መሆን አለበት፡፡ አሮጌውን ማንነታችንን ጥለን አዲሱን በክርስትና ያጌጠውን ማንነታችንን የምንተካበት እንዲሆን በፍጹም ቆራጥነት እስኪ እናቅድ፡፡ ለዘመናት የቆየው ታላቅነታችንም ከኛ ዘመን ወደ ልጆቻችን ይተላለፍልን፡፡
በዚህ አዲስ ዓመት መሪዎቻችንም የምትሞቱ መሆናችሁን አስቡ፡፡ መልካምም ክፉም በሰራችሁ ጊዜ አበጃችሁ! ማለፊያ ነው! እያሉ የእጃችሁን ምፅዋት የሚጠባበቁ በዙሪያችሁ ያሉ አፈ ጮሌዎች፣ ካህናተ ጣኦት የሕዝቡን እንባና እሮሮ እንዳታዳምጡ እዝናችሁን በማይረባ መዝሙር መሰል ጩኸት ያባዝናሉ፤ እንዳታስተውሉ ደራሽና ርባና በሌላቸው ጉዳዮችና ትዕይንቶች ዐይኖቻችሁን ይሸፍናሉና እባካችሁ ዝቅ ብላችሁ ሰው መሆናችሁን እስክንረዳ ከሕዝብ ጋር መስተጋብር ይኑራችሁ፡፡ እናንተን ሰላም ማለት የሰማይን መስኮት ከፍቶ ወደ ሰማየ ሰማያት የማረግ ያህል አይራቅብን፤ ስትስቁ፣ ስትከፉ፣ ስትቀልዱ፣ ስትሸወዱ፣ ስትጫወቱ፣ ሲደክማችሁ፣ ሲያንቀላፋችሁ ወዘተ እንመልከታችሁ፡፡ እናንተም ሕዝቡን በዚህ ጥልቀት ተመልከቱት፡፡ እንደ ሰማይ አይነኬ አለመሆናችሁን እስኪ አሳዩን፡፡ ያለፈው ዘመን ብዙ ሊያስተምራችሁ ሞት የማይቀር ሲሆን ታሪካዊ ሥራ መሥራት እንዳለባችሁ ልታውቁ ይገባል፤ መልካም አስተዳደር የተጠማን ሕዝብ፣ ቀልጣፋና ማመናጨቅ የሌለበት አግልግሎት የራቀውን ሕዝብ እስኪ በዚህ አዲስ ዓመት ጀምሮ እውን እንዲሆን ተግታችሁ ሰርታችሁ ችግራችንን ከስረ መሰረቱ ነቅለን እንድንጥለው ምሩን፤ እኛም እንከተላችሁ፡፡
በተለያዩ የመንግስትም ሆነ የግል የሕዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያላችሁ ሰዎች እስኪ ለውጥ ከራስ ይጀምራልና ይህን ምስኪን ነገር ግን ታላቅ በመንፈሳዊ ልዕልናው የሚበልጠንን ሕዝብ ይህንን ልዕልና እንደያዘ እንዲቀጥል መልካም አግልግሎትን በመስጠት እናበረታታው፤ ሳይማር ያስተማረ ሕዝብ አሁንም ተማርን ብለን ራሳችንን የምናስታብይ ተማርን ብለን እንዳልተማርን የሆንን እኛን በትዕግስቱ ብዛት ተሸክሞን እየመራን ነው፡፡ እባካችሁ መልካም አስተሳሰብን በተከታዮቻችን፣ በልጆቻችን፣ በታናናሾቻችንና በአጠቃላይ በዙሪያችን ላሉ ሁሉ በሥራችን እናሳያቸው፡፡ የጠቆረ ፊት፣ ማመናጨቅና ስድብ፣ ሙሰኝነትና ጉቦኝነት ለዚህ ምስኪን ነገር ግን ታላቅ ሕዝብ ይቅርለት፡፡ እስኪ ሁላችን በያለንበት በዚህ አዲስ ዓመት በአዲስ ቃል ኪዳን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር ቃል እንግባ፡፡
ይህ አዲስ ዓመት ለሁላችሁ የስኬት፣ የለውጥ፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነት ዓመት ይሁንላችሁ!!! አሜን!!!
መልካም በዓል!

1 comment:

  1. እስኪ ሁላችን በያለንበት በዚህ አዲስ ዓመት በአዲስ ቃል ኪዳን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር ቃል እንግባ !!! 10Q

    ReplyDelete