Wednesday, May 9, 2012

ቅድስት ድንግል ማሪያም በነገረ ድህነት (ክፍል አንድ)


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
እንኳን ለእናታችን ለአማናዊት ፅዮን ለቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማሪያም የልደት በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!!!
እመቤታችን ቅድስት ማሪያም ደጋግ ከሆኑ ቅዱሳን የተገኘች ንዕድት ክብርት ቅድስት መሆኗንና በነገረ ድህነት ውስጥ ያላት ቦታ ምን እንደሆነ በተከታታይ በዚህ በሎግ ላይ እንመለከታለን፡፡
የክርስትና ሐይማኖት ዋና መሰረት የነገረ ድህነት ትምህርት ነው፡፡ “ነገር” በቤተክርስቲያን የአንድን የትምህርት ወይም የጥናት መስክ የሚያሳይ በእንግሊዝኛው LOGY የሚለዉን ቃል የሚተካ ነው፡፡ ድህነት የሚለው ቃል ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ከኃጢያት ተፈውሶ በሐይማኖት መንገድ በመጓዝ የእግዚአብሔርን መንግስት መውረስ ማለት ነው፡፡ በነገረ ድህነት ውስጥ ብዙ የምንገነዘባቸው እና ክርስትናን ከሌሎች አብያተ እምነቶች የተለየ የሚያደርገው ይኸው የነገረ ድህነት ጉዳይ ነው፡፡ በነገረ ድህነት ውስጥ ብዙ ጉዳዮች ሊዳሰሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
፩. የሰው ልጅ አፈጣጠርና የአዳም ሕይወት በገነት እና ከገነት ከተሰደደ በኋላ
፪. እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የገባለት ቃል ኪዳንና የነቢያት የትንቢት ቃል
፫. እመቤታችን የአዳም ተስፋ በዘመነ ስደትና ድንግል ማሪያም በነገረ ድህነት 
፬. የእግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆንና የሰው ልጅ ድህነት ፍጻሜ
የሚሉት ሰፋፊ ጉዳዮች በነገረ ድህነት ውስጥ የሚሰጡ ትምህርቶች ናቸው፡፡ በዚህ ተከታታይ ፅሑፍ ሁሉንም ተያያዥነት ስላላቸው በጥቂት በጥቂቱ ለማየት የሚሞከር ቢሆንም በአንጻራዊነት ሰፋ ያለውን ቦታ በተራ ቁጥር ፪ ያለው ጉዳይ የሚሸፍን ይሆናል፡፡
እግዚአብሔር ረቂቅ፣ ምጡቅ፣ ሁሉን ቻይ፣ በሁሉ ቦታ ያለ፣ መፃያቱንና ኃላፊያቱን የሚያውቅ በመሆኑ አነዋወሩን ጠንቅቆ መረዳትና ማወቅ ለማንም የሚቻል አይደለም፡፡ ነገር ግን በቸርነቱ ብዛት ሕልውናውንና ባህርዩን ለቅዱሳን ሰዎችና ለቅዱሳን መላእክት ሊረዱት፣ ሊሸከሙትና ሊገባቸው በሚችል መንገድ ይገልጥላቸዋል፡፡ ቅደመ ዓለም እግዚአበሔር እንዲህ ነበር አሁን ደግሞ እንዲህ ነው ለወደፊት ደገሞ ይህንን ይመስላል የሚል ማንም የለምና፡፡ ነገር ግን እርሱ ለቅዱሳኑ በገለጠላቸው መሰረት በጣም ጥቂት ነገር መናገር ይቻላል፡፡
ቅድመ ዓለም መላእክትና ሁሉም ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት እግዚአበሔር በአንድነቱና በሦስትነቱ ጸንቶ ይኖር ነበር፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ፩፥፩ ላይ ወንጌላዊው ሲጽፍ “በመጀመሪያ ቃል ነበር፡፡ …” በማለት የገለጠው መጀመሪያ የሚለው ቃል የእግዚአበሔር መጀመሪያ አለው፤ በጊዜ የተወሰነ ሕልውና ነበረው ማለት አይደለም፡፡ ዓለምና በውስጧ የነበሩት ፍጥረታት ሳይፈጠሩ ከዋከብትም ሳይታዩ ያለውን ጊዜ ለማመልከት ነው፡፡ የእግዚአበሔር ሕልውና ወደ ኋላ መስፈርት ልኬት የሌለው በቁጥር የማይተመን የማያልቅ ርዝማኔ ያለው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባህርዩ ባህርዩን እያመሰገነው ያለ መናወጽ ፍፁም ሰላም፣ ፍፁም ፀጥታ ባለበት ጨለማ በማያገኘው ፍፁም አስደሳች በሆነ ብርሃን ውስጥ በቦታና በጊዜ መወሰን ሳይኖርበት ሦስትነቱ አንድነቱን ሣይነጣጥለው፤ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው በፍፁም አንድነትና ሦስትነት ባህርዩ ከባህርዩ ሳይቃረን ጎደሎና ወሰን በሌለበት ምልዐት፤ማጣትና ችግር፣ ሰልፍና ማጉረምረም በሌለበት ምሉዕ ጌትነት ይኖር ነበር፤ አሁንም ድህረ ዓለም በቅዱሳኑ እጹብ ቅዱስ እግዚአብሔር እየተባለ እየተመሰገነ በቀደመው አነዋወሩ በፍጥረታቱ ላይ በፍጹም ጌትነት ለዘላለም ይኖራል፡፡
እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ እየኖረ ማንም አማካሪ ሳያስፈልገው ዓለምን ፈጠረ፡፡ በስድስት ቀንም ፍጥረታትን ሁሉ በየመለካቸው ፈጠራቸው፡፡ በመጀመሪያው ቀን እሑድ ስምንት ፍጠረታትን፣ በሁለተናኛው ቀን ሰኞ እንድ ፍጡር፣ በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ ሦስት ፍጥረታትን፣ በአራተኛው ቀን ረቡዕ ሦስት ፍጥረታትን፣ በአምስተኛው ቀን ሐሙስ ሦስት ፍጥረታትን፣ በስድሰተኛው ቀን አርብ አራት ፍጥረታትን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ቅዳሜ ዐረፈ፡፡
የሰው ልጅ የተፈጠረው የሁሉም ፍጥረታት መደምደሚያ ሆኖ በእግዚአብሔር ቅዱሳን እጆች በግብር ነው፡፡ ሌሎቹ በሐልዮና በነቢብ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ለምግበ ሥጋና ለምግበ ነፍስ የሚሆኑ ፍጥረታት ከተፈጠሩለት በኋላ፣ የሚራዱትና የሚታዘዙለት የሚገዙለትም ፈጥረታት ከተፈጠሩ በኋላ የሰው ልጅ ተፈጠረ፡፡ የሰው ልጅ በምድር ባሉ ፍጥረታት ላይ ንጉስ ሆኖ የተሾመ የምድር ፍጥረታትን ይገዛና ያስተዳድር ዘንድ በነጻነትም ይኖር ዘንድ ነው የተፈጠረው፡፡ በእግዚአብሔር አርያና ምሳሌም የተፈጠረው የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡ ዘፍ. ፩፥፳፮.
ልዑል እግዚአብሔርም አዳም እርሱ እግዚአብሔር አምላኩና ፈጣሪው እንደሆነ እንዲገነዘብ በመካከል እፀ-በለስን ምልክት አደረገለት፡፡ አዳም ከእርሷ ከእፀ-በለስ እንዳይበላ ከእርሷ በበላ ጊዜ የሞት ሞትን እንደሚሞት ነገረው፡፡ አዳም እፀ-በለስን እንዳይበላ የተከለከለው እግዚአብሔር አምላኩና ፈጣሪው እንደሆነ በለስን ባዬና ለመብላት ባሰበ ጊዜ እንዲያስታውስና ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ትእዛዝ መስዋእት ማድረግን እንዲያስለምድ በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል የነበረው መልካም ግንኙነት ሳይቀዘቅዝና ሳይጠወልግ እንዲቀጥል ለማድረግ ነበር፡፡
ነገር ግን በዓለመ መላእክት ሁከት በማስነሳቱ ከርስቱ የተባረረው ዲያብሎስ በከይሲ አድሮ ለሔዋን  በመከራት ክፉ ምክር የእፀ-በለስ ፍሬ ለመመገብ እጅግ ያማረች እጅግ የምታስጎመጅ ሆና ታየቻት፡፡ መፅ. ኩፋሌ ፬፥፳ ከእፀ-በለስም ቆርጣ በላች፤ ለባሏ ለአዳምም ሰጠችው፤ ሁለቱም በአንድነት ከእፀ-በለስ በሉ፡፡ እግዚአብሔርም  ቀደም ብሎ ለአዳም በነገረው ቃሉ መሰረት አዳም የሞት ሞት ተፈረደበት፡፡ ከገነትም ተሰደደ፡፡ መፅ. ኩፋሌ ፬፥፳፬
የእመቤታችንን በነገረ ድህነት ያላትን ቦታ ስናስብ እርሷ ቅድመ ዓለም በአምላክ ህሊና ታስባ ትኖር ነበር፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ቀዳማያቱንና መፃያቱን ያውቃልና አዳም እንደሚበድል ያውቅ ነበር፡፡ አዳም በደለኛ ቢሆንም ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ እንደተናገረው በኋላም የንስሃ ልብ ሳይኖረው እንደቀረው እንደ ሳጥናኤል ሳይሆን በአዳም የንስሃ ልብ ስለተገኘበት ዳግመኛም የበደል ሐሳብ አመንጪ እርሱ ባለመሆኑ (በሰይጣን ምክር በመሳቱ) እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የመዳኛ መንገድን አዘጋጀለት፡፡ በዚህም ሰው ከመፈጠሩ በፊት ለሞቱ መድኃኒት አስገኚ የምትሆን ንዕድ ክብርት ቅድስት የሆነች ደግ እናታችን ድንግል ማሪያም በአምላክ ህሊና ታስባ ትኖር ነበር፡፡
ሳጥናኤል በዓለመ መላእክት ሁከት ባስነሳ ጊዜ መላእክቱ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት የሳጥናኤልን ሰራዊት ገጥመው ሁለት ጊዜ ተሸንፈው በሦስተኛው ወደ እግዚአብሔር ሲያመለክቱ የእመቤታችን ድንግል ማሪያም ስዕል የተቀረጸበት መስቀል ሰጥቷቸው ያንን ይዘው ቢዋጉ ሳጥናኤል እየሸሸ ሄዶ በበርባኖስ ጥልቅ ወደ ሲኦል ወርዷል፡፡ ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የጌታችንና የመድኃኒታችን የመስቀሉ ሥራ እና እመቤታችን በአምላክ ቅድመ-ዓለም የታሰቡ ሰው ከመፈጠሩ በፊት እነዚህ ጉዳዮች በእግዚአብሔር የተወሰኑ ስለመሆናቸው ነው፡፡ የድንግል ማሪያም በነገረ ድህነት ውስጥ ያላት ዐብይ ቦታ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ 
የሰው ልጅ አምላኩን በድሎ ከገነት ከተሰደደ በኋላ በታላቅ ፀፀትና ለቅሶ ንስሃ ገባ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማሪያም ተወልዶ በበደላችን ምክንያት የተረገመችውን ምድርን በኪደተ-እግሩ ቀድሶ ወንጌልን ለሕዝብ እና ለአሕዛብ አስተምሮ በጥምቀቱ በዮርዳኖስ በምድር የተቀበረውን የእዳ ደብዳቤያችንን ደምስሶ በቀናተኛ አሁዶች እጅ ተይዞ ተገርፎ እና መከራ መስቀልን ተቀብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የእዳ ደብዳቤያችንን እና በደላችንን ሁሉ ደምስሶ እንደሚያድነን ለአዳም ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ አዳምም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺው ነሽ በማለት አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው የተናገረው ለዚህ ነው። ከሥጋ ሞት በፊት በተረገመችና በሰው ልጅ ላይ አመጻን ያመጹ አራዊት ባሉባት ምድር የሚኖር ሰው ተስፋው ቅድስት በሆነች እመቤታችን፣ አምላክን ለመቀበል በተገባ ሆና በተገኘች ድንግል ማሪያም መወለድ ሆነ። እነሆ ይህንን የመሰለ የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመነ ፍዳ ማብቂያ ማብሰሪያ የእመቤታችን ድንግል ማሪያም ልደት እነሆ ዛሬ እናከብረዋለን፡፡ ከፍጥረታት በላይ የገነነች ጨረቃ፣ ፀሐይን የወለደች በእግሮቿ ጨረቃን የተጫማች፣ በራሷ ላይም አስራ ሁለት ከዋከብት ያለበት አክሊል የደፋች አንዲት እመቤት እነሆ ዛሬ ተወለደች፡፡ ራዕይ ፲፪
የመልካም ብስራት ምልክት የኖኅ ርግብ እመቤታችን የማየ አይህ መድረቅ (የዘመነ ፍዳ መጠናቀቅ)፣ የጥል ግድግዳ መፍረስ ምስራች ነጋሪ ቅዱስ ገብርኤል ምልዕተ ፀጋ ብሎ ያመሰገናት ድንግል እነሆ ዛሬ ተወለደች፡፡ በጨለማ ግዞት ለነበርን ለመልካም ብስራት ናፋቂዎች ለተዋህዶ ልጆች እንኳን ደስ ያላችሁ (ያለን)፡፡ ከወደ ሊባኖስ መልካም ብስራት ተሰማ! የጨለማ አበጋዞች ያሰደዱአት እሙ ለፀሐየ ፅድቅ ጨረቃ በዚያ ተወለደች፡፡ መሰረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች የሆኑ (መዝ. ፹፮፥፩) ከንፁህ ዘር የተገኘች (ኢሳ. ፩፥፱) እድፍ ጉድፍ ያላገኛት በዚያ ከምድር ይልቅ ከፍ ከፍ ባለው ሰው በማይኖርበት በስደት ቦታ በሊባኖስ ተራራ ተወለደች፡፡
እስኪ ሁላችንም በደስታ ሆነን፡- “ሙሽሪት ሆይ! ከሊባኖስ ነዪ፤ ከሊባኖስ ነዪ፤ ከሃይማኖት ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች ጉድጓድ ከነብሮችም ተራራ ተመልከቺ።” የአዳም ስቃዩ እንደበዛ መልካም ብስራት እንደናፈቀው አይተሽ ከሊባኖስ ነይ እንበላት፡፡
ኃጢያተኞችን በምልጃው ከፈጣሪው የሚያስታርቃቸው አንድ ቅዱስ ሲወለድ ተራሮች እንደ እምቦሳ ጥጃ ይዘላሉ፤ ምድርም ማርና ቅቤን ትሰጣለች፡፡ እንግዲህ የዓለም መድኃኒት የምታስገኝ የምህረት ዘመንን ብስራት የተሸከመች የመልካም ነገር ሁሉ መጀመሪያ የሰው ልጅ ድህነት ምክንያት ድንግል ስትወለድ ወፎች ምን ዜማ ያዜሙ ይሆን?  ተራሮች ደስታቸውን እንዴት ገልፀውት ይሆን? ምድርስ ከማርና ከቅቤ የከበረ ምን አበረከተች? ውሆች ቃላቸውን ምን ብለው ሰጡ? ያዩትን ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ የሚፅፉልን ብዕራቸው የሰላ እጃቸው የተባ እንቅልፍ ድካም የሌለባቸው ትጉሐን ደራሲያን በነበሩና የፍጥረታትን ደስታ የመላእክትን ዝማሬ ጥልቀት ያላቸው የቀላያታን ከፍ ከፍ ያለ ድምፅ በነገሩን!  ይህንን ድንቅ ነገር በቦታው የነበረ የመረዳት ውስንነት የልለበት ኃያል በነበረና በነገረን፤ ሁሉንም ነገር የሚተርክልን እንደነበረ አድርጎ የሚያሳየን ምነው ባገኘን!  በድካሜ ይህንን ተመኘሁ እንጅ ለእኔ ደካማ የመረዳት አቅም የሚመጥን ወይም ከዚያ ይልቅ የሰፋ ጥልቅ ምስጢርን አባቶቼ ነግረውኝ ነበረ፡፡ እኔስ ነገሩን በምልዐት ማየት ብመኝም ከንቱ ነኝ፤ የታደልኩትን በስፋት ያላስተዋልኩ የተሰጠኝን መልካም ዕድል ያልተጠቀምኩ ደካማ ነኝ፡፡
ምስጢራትን የምናስተውልበት ልቦና የእመቤታችንን በነገረ ድህነት ያላትን ቦታ ማስተዋል የምንችልበት ጥበብ እግዚአብሔር ያድለን፡፡
….ይቀጥላል…


2 comments:

  1. This is not from Ethiopian orthodox doctrine.

    ሳጥናኤል በዓለመ መላእክት ሁከት ባስነሳ ጊዜ መላእክቱ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት የሳጥናኤልን ሰራዊት ገጥመው ሁለት ጊዜ ተሸንፈው በሦስተኛው ወደ እግዚአብሔር ሲያመለክቱ የእመቤታችን ድንግል ማሪያም ስዕል የተቀረጸበት መስቀል ሰጥቷቸው ያንን ይዘው ቢዋጉ ሳጥናኤል እየሸሸ ሄዶ በበርባኖስ ጥልቅ ወደ ሲኦል ወርዷል፡፡ ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የጌታችንና የመድኃኒታችን የመስቀሉ ሥራ እና እመቤታችን በአምላክ ቅድመ-ዓለም የታሰቡ ሰው ከመፈጠሩ በፊት እነዚህ ጉዳዮች በእግዚአብሔር የተወሰኑ ስለመሆናቸው ነው፡፡ የድንግል ማሪያም በነገረ ድህነት ውስጥ ያላት ዐብይ ቦታ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ This is totally wrong according to EOTC doctrine. This is more of Catolic doctrine.

    ReplyDelete
  2. እስኪ አንተ ንገረን አቃንተህ! “ወላዲተ አምላክ በአምላክ ህሊና ታስባ ትኖር ነበር” የሚለው የቤተ ክርስቲያን ቃል ምን እንደሆነ አብራራልን፡፡ ነው ይህ ልክ አይደለም ማለት ነው? ቃልህን እንሰማዋለን! ማስተካከያም እናደርጋለን! በጭፍን ስህተት ነው ከማለት ንገረን እስኪ ዐምልተህና አስፍተህ! እኛም እናዳምጥህ፡፡

    ReplyDelete