Thursday, December 20, 2012

የእግር እሳት - ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ጉዳይ




ሰሞኑን ስለ ቤተክርስቲያን የተለያዩ ወሬዎች እየተሰሙ ነው፡፡ የሚነገሩት ነገሮች እውነት ከሆኑ የቤተክርስቲያን የመከራ ዘመናት ቢያንስ የሩብ መቶ ክ/ዘመን እንደተራዘመ ይሰማኛል፡፡ ቤተክርስቲያን በፖለቲካ መሪዎቻችን ተፅዕኖ ለሁለት ተከፍላ ሩብ መቶ ክ/ዘመን ስትበጠበጥ መንግስትም ሲፈልግ ልጆቿን ሲፈልግ ምዕመናኑን ሲያስፈልገው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናትን የቤተክርስቲያኗን ልዕልና እየተዳፈረ ከቤተክርስቲያን አውድ ላይ እያፈሰ እየወሰደ ቢሻው ሲገድል፣ ቢያሻው ሲያስር፣ ሲፈልግ ደግሞ ሲገርፍ ኖሯል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ በአባ ጳውሎስ አማካኝነት እነ አለቃ አያሌውን የመሳሰሉ ሊቃውንት ከቤተክርስቲያን እየተወገዱ ሌሎች ሰሜንኛ ሰዎች ተተክተው ቤተክርስቲያንን መሸጫና መለወጫ፣ የሙስና ማቀናበሪያ፣ የዘረፋ ፕሮጀክቶች መንደፊያ፣ ማበልጸጊያ፣ መተግበሪያ ወዘተ በማድረግ  ቤተክርስቲያን የብልሹ አሰራር ምሳሌ፣ የዘረፋ ማዕከል፣ የዘረኝነት ፅንፍ ማዕረግ መሸለሚያ፣ የመንግስት አሻንጉሊት የሆነ ትውልድ መፈልፈያ፣ የጸረ-ተዋህዶ የእፉኝት ልጆች መፈልፈያ ወዘተ እንትሆን አድርጓል፡፡
ይህ ያሳለፍነው ሩብ መቶ ክ/ዘመን በአቶ ታምራት ላይኔ (የሀገሪቱን ሀብት በአጭር አመታት ለመዝረፍ ያለታከተ መራል አልባ ሰው) አማካኝነት መሆኑ ደግሞ የህሊና ቁስል ነው፡፡ ሰሞኑን በሪፖርተር ጋዜጣ በአቶ ታምራት ላይኔ ስም የተቀመጠ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ከስዊስ ባንክ ለኢትዮጵያ ተመላሽ ተደረገ በማለት የተዘገበውን መመልከት የአቶ ታምራት ላይኔ ሞራል አልባ የሙታን አባል ስለመሆኑ መናገር ቅር የሚያሰኘው ያለ አይመስለኝም፡፡ የቁም ሙታን ታሪክ እንዲህ ይፃፍላቸዋልበነገራችን ላይ ምንዝር ከአለቃው ትዕዛዝ ሳይሰጠው በራሱ ተነሳሽነት ይህንን ትልቅ የታሪክ ክፍተት ለመፍጠር በኢትዮጵያ ሁኔታ ይነሳሳል ብየ አላስብም፡፡ በዚህም አቶ ታምራት ላይኔ የፊታዉራሪነቱን ቦታ ወሰደ እንጅ ከበስተጀርባ የአለቅዮው ትዕዛዝ አይኖርም ለማለት ይከብደኛል በኔ እይታ፡፡ ይህም ባዶ ቦታውን በተተኪው የኢህአዴግ ቀኝ እጅ እንዴት እንደተሞላ በማየት ከበስተጀርባ የነበሩትን ረጃጅም እጆች መገመት አያዳግትም ባይ ነኝ፡፡
አሁንም በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ የሰላም ውጥኑን ለማደፍረስ፣ የኢህአዴግ አሻንጉሊት ለመተካት የሚሰሩ የመንግስት አካላት ከታምራት ላይኔ በሞራላዊ ይዘታቸው (ልዕልናቸው) እጅጉን የዘቀጡ ናቸው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ታምራት ላይኔ ከበረሃ እንደመጣ እምነት ምንድነው፣ ሰላምስ ምንደናት የሚለውን ለመመለስና እርቅና ይቅርባይነት ምን ማለት እንደሆነ ያዉቃል ቢያውቅም ክብደታቸውን ይመዝናል ብዬ አላስብም፡፡ ያኔ በእርሱ አመለካከት የደርግ የሆነ ሁሉ መወገድ አለበት፣ ማሸነፍ ሁል ጊዜ በእርሱ እይታ በጦርና በኃይል እንደሆነ አድርጎ የሚገነዘብበት ጊዜ ነበር ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ያሁኖቹ ግን በምርጫ ማሸነፍ፣ መሸነፍ፣ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገት፣ ነጻነት፣ መተካካት፣ ወዘተ የሚባሉ አዳዲስ ጽንሰ ሐሳቦችን ያወቁ፣ ሀገር በመምራት የሩብ መቶ ክ/ዘመን ልምድ ያካበቱ በመሆናቸው ቤተክርስቲያኗን እራሷን እንድታስተዳድር ነጻ ሊተዋት ይገባ ነበር፡፡ በዚህም አሁንም በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ያሉ የመንግስት አካላት ሞራል አልባ ባዶ ቀፎዎች፣ የንብ መንጋ የሌላቸው፣ ንብ አናቢውም በልዩ ልዩ ማዕጠንት ያላጠነው ከሸረሪት ድር ነጻ ያልሆነ ዝንብና ቢራቦሮ የሚጠመድበት የሸረሪት ማኅደር ቀፎዎችን ይመስላሉ፡፡ በእውነትም በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ከገቡ አስቤ ዋጋ ያጣሁባቸው ባዶ ቀፎዎች እነዚህ ናቸው፡፡
ባለፈው አንድ የሪፖርተር ጋዜጣ ላይ "አገርና ሕዝብን የሚጎዱ ይወገዱ" በሚል ርዕስ ባስነበበን ፅሑፍ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ቅን አገልግሎት እንደጠፋ፣ መልካም አስተዳደር እንደጠፋ፣ የሕዝብ ሀብት በተሹዋሚዎች እንደሚዘረፍ፣ ጥቂቶች ባለሥልጣናት ብቻ በትክክል እንደሚሰሩ አትቷል፡፡ ይህ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ አቤቱታ የሚመልስ ፍርድ የሚያስተለካክል ጠፍቶ ሰው ተሰላችቶ አቤት ማለት ቢያቆም መንግስት የመልካም አስተዳደር መስፈን ነው ብሎ መሸወድ የለበትም ይላል ፅሑፉ፡፡ ይህንን በትክክል እኔ እስማማበታለሁ፡፡ ዝም ያልነው ጩኸታችንን የሚሰማን አጥተን ነው፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው በአሁኑ ሰዓት የኢህአዴግ አመራር አካላት ማለትም የአሁኑ መንግስት ከፍተኛ ተሸዋሚዎች በሞራል ልዕልና፣ በሥነ ምግባር፣ በታታሪነት፣ በአድሎዋዊ አልባነት፣ በግልፀኝነት፣ በአጠቃላይ በግብረ ገብነት የመጨረሻው የዝቅጠት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ይሰማኛል- በእኔ እይታ፡፡
እናም እነዚህ የመጨረሻው የዝቅጠት ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች እነ ታምራት ላይኔ የሠሩትን የባዶነት ታሪክ ለመድገም ቢሯሯጡ አይገርመኝም፡፡ ነገር ግን የመንግስትን ፈርጣማ ክንድ ተንተርሰናል፣ መንግስት እንዲህና እንዲያ በሏል፣ መንግስት እንዲህ አስፈራርቶናል ወዘተ በማለት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን በማስበርገግ የሚፈልጉትን የረከሰ፣ የማሰነ፣ የነተበ አሰራር በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ማስቀጠል የለባቸውም፡፡ እናም የሚከተሉትን ነጥቦች መከተል ይኖርብናል እላለሁ፡-


. ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት


የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ጳጳሳት ጥቡአን መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የማንንም ማስፈራሪያና ማንገራገሪያ መፍራት የለባቸውም፡፡ ከ30 እስከ 55 የሚሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት ቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ከ8 የማይበልጡ የመንግስት አካላት ድጋፍ ያላቸው ጳጳሳት ይህንና ያንን አደረጉ ሲባል መስማት እጅግ ይዘገንናል፡፡ የምንኩስና ሕይወት ሞት ነው፡- በመኖርና በመሞት መካከል መሞት የተሻለ የሆነበት፡፡ ታዲያ ፍርሃት ከየት የመጣ ነው? እኛ ልጆቻችሁ ከጎናችሁ ነን፡፡ ለቤተክርስቲያን የሚበጃትን እንጅ ለጥቅመኛና ለሥልጣን ጥመኛ የመንግስት ሹማምንቶች  "የሚበጃቸውን" አትምረጡ፡፡ ለቤተክርስቲያን የማይበጃት ለእነርሱም አይበጃቸውምና!!


. ሌሎች የቤተክርስቲያን አመራር አካላትና አገልጋዮች

ሁሉም የቤተክርስቲያን አመራር አካላትና አገልጋዮች ትክክለኛው የቤተክርስቲያን የሚበጅ እርቀ ሰላሙ እንዲሳካ፣ መልካም የቤተክርስቲያን መሪ አባት እንዲመረጥ የየበኩላችንን ኃላፊነት ልንወጣ ያስፈልገናል፡፡ በፀሎት፣ ድምጻችንን በማሰማት፣ ሂስ በመስጠት፣ በመጠቆም፣ በመወያየት ወዘተ፡፡

. ምዕመናን

ሁላችን ምዕመናን ደግሞ በጸሎት፣ በውይይት፣ ሂስ በመስጠት፣ መረጃ በመስጠትና በመለዋወጥ፣ አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ በማድረግ ለእርቀ ሰላሙም ሆነ ለቀጣይ መሪ ምርጫ የበኩላችንን ልንወጣ ያስፈልጋል፡፡ አላስፈላጊ አካላት በቤተክርስቲያኗ ታሪካዊ ጉዞ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳርፉ መከላከልም ያስፈልገናል፡፡

. መንግስት

በመጀመሪያ ደረጃ ከቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ እጁን ያንሳልን፡፡ ከዚያ ከጥሎ አላስፈላጊ ግርግሮችን ነቅቶ ይጠብቅ፡፡ ሁለተኛው እንኳን እራሱ መንግስት ግርግር ካልፈጠረ አላሰፈላጊ ግርግር የሚኖር አይመስለኝም፡፡ መንግስት እንኳን በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ቤተክርስቲያን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አወንታዊ ለውጥ እንድታመጣ ማስቻል ይቅርና የራሱን ተቋማዊ አደረጃጀት ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው አመራር፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ የመተካካት መርህ ተመርቶ የራሱን የፓርቲ መዋቅር ዘላቂና ፅኑዕ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ እንኳን አለቻለም፡፡ መንግስት ደጋፊና ቲፎዞ ምልመላ በተሯሯጠበት በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ባከናወነው "የተሳካለት"በተባለ እንቅስቃሴ ዛሬ ዛሬ በአቋራጭ ጥቅምን ለማሳደድ ባቀዱ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ስድ አደጎችን ያልምንም መመልመያ መሥፈርት በማጋበስ ወደ ኃላፊነት ቦታ በማስገባቱ እነዚህ ሰዎች በሚያከናውኑት ዘረፋ፣ አስተዳደራዊ በደል፣ ስንፍና፣ ቸልተኝነት፣ ዘረኝነት፣ የወሮበላ ጥቅመኛ ቡድን ምስረታ በራሱ የመንግስት አካላትና በገዢው ፓርቲ ውስጥ "ተቀምጠው የሰቀሉት ቆሞ ለማውረድ ይቸግራል"የሚባለው ብሂል በኢህአዴግ ላይ ተፈጻሚ በሆነበት በዚህ ሰዓት ይህንን የነተበ፣ የተጎሳቆለ፣ ብልሹ አሰራር በቤተክርስቲያን ላይ ለመጫን ማሰቡ የታሪክ ስህተት ይመስለኛል - ለእራሱም የሚበጀው አይመስለኝም፡፡ ንቅ እሳተ ገሞራ ጥንቃቄ ይደረግበታል፤ ለዘመናት የተረሳ የተዳፈነ እሳተ ገሞራ ግን መቼ ይነሳል? የት አካባቢ ይፈነዳል? ወዘተ ጥያቄዎችን መመለስ ይከብዳል፡፡

1 comment:

  1. መንግስት እና ሃይማኖት ከተለየ ድፍን 23 አመታትን አስቆጥረናል፡፡ ታድያ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እየገባ ነዉ በማለት የተለያዩ ዉሸት ፕሮፖጋንዳ የሚያዞሩ እና ስዉር አላማ ይዘዉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ድብቅ የፖለቲካ አላማ ያላቸዉ እንጂ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሚያስቡ ትክክለኛ ኦርቶዶክሶች አይደሉም

    እባካችሁ የተዋህዶ ልጆች እንጠንቀቅ!!! ያዘኑን መስለዉ ሊያጠራምሱን ነዉ

    ReplyDelete