Saturday, October 6, 2012

የዩኒቨርሲቲ መምህራን ስልጠና

በዚህ አዲስ ዓመት በየዩኒቨርሲቲው መምህራኑ ስልጠና መሰጠት አለባቸው በሚል ወደ ስብሰባ ገባን፡፡ ሥልጠና ስንጠብቅ የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በአራተኛ ወሩ ያለፈው ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀረበልንና ገምግሙ ተባልን፡፡ ሪፖርቱ በስድ ንባብ መለክ በስላይድ ቁጥርና መለኪያ እንዲሁም መቶኛ ሳይኖረው ላይ ላዩን የተተረከ የረጅም ልቦለድ ትረካ ይመስላል፡፡ ቆየት ብሎ ደግሞ የፀደቀ ነገር ግን ለሦስት ወር ያልተሰራበት ወይም ደግሞ አሁን ቢነገራቸው ችግር የለውም የተባለ ወይም ደግሞ ያለ እቅድ ለሦስት ወር እንደቆየን የሚያረዳ በመስከረም መገባደጃ ላይ 2005 . የበጀት ዓመት እቅድ ገምግሙ ተባልን፡፡ ልክ እንደ ሪፖርቱ ይህም ፍቅር እስከ መቃብር በተገለፀበት ዓይነት ቋንቋ ስድ ንባብ ነበር፡፡ መለከያና ቁጥር ጥላቸውን እንኳን እንዳይጥሉበት ጥንቃቄ ተደርጓል፡፡ እኛም ቁጥር፣ መለኪያ፣ መቶኛ የሌለውን የፕሮጀክተር ታግዞ የቀረበ ሥድ ንባብ እንዴት እንደምንገመግመው ግራ ቢገባን ብሶታችንን መናገር ጀመርን፤ የደመወዝ ማነስ፣ የኑሮ ማሻቀብ፣ የምሁራኑ ፍልሰት፣ የቤት አበልም ሆነ ቤት አለመኖር ወይም ማነስ ተያይዞም በየማድ ቤቱ እያደሩ ማስተማር፣ መመራመር እንዴት እንደሆነ ልምድ የመለዋወጥ ያህል ተነፈስናቸው፡፡
በስሜት ሆነን ግማሾቻችን በአርምሞ እያለቀስን፣ ሌሎቻችን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደሚጠፋ እሳት እየተንቦገቦግን፣ ሌሎቻችን ደገሞ እየተወናጨፍን የአገር ፍቅር ትያትር ቤት አርቲስቶችን በሚመስል ሁኔታ ብሶታችንን ዘረዘርን፡፡ ጥቂት ነገሩ ወደ ውስጣቸው ያልገባው ሚኒስትሩም በዲስኩራቸው የእኛን ትንታግ ምላስ ውሃ ከቸለሱበት በኋላ ደመወዝን የሚመለከተው ጉዳይ ላይ ሲደርሱእናንተ እኮ ብር ላይ ነው የተኛችሁት፤ ምሁሩ ጭንቅላት አለው፤ ብዙ እምቅ ችሎታዎች አላችሁ፤ ይህንን ችሎታ ተጠቅማችሁ ለኢንዱስትሪውና ለሀገር የሚበጅ የአማካሪነት፣ የዲዛይን፣ የማልማት፣ ወዘተ ሥራዎችን ለምን አትሰሩም? ”አሉን::
እኛም አሁን እነርሱ ምሑር ብለው ለሚጠሩት አመኔታ ካላቸው የኛው የራሳችንን ጉዳይ እኛው እንድንወስን አንድ ሰው እንኳን በኢንስቲትዩት አመራር ቦርድ ውስጥ እንዲኖር አይፈቅዱም? የኛን አማካሪነት የኛን መሪነት፣ የኛን ዲዛይንእንደማይቀበሉት የወደቁ በምርምር ያረጁ እንኳን የሐበሻ ሥነ-ልቦና የእነርሱን አገር ሥራ አመራር የማይችሉ ፈረንጆችንና ቢጮችን አያተካኩብንም ነበር እያልን ሳለ ሚኒስትሩ ከራሳቸው አእምሮ ያፈለቁት መልስ በከፊል አሳምኖን ወጣን፡፡ ቆየት ብሎ ግን በተለያዩ ግቢዎች የነበሩ የሁሉም ስብሰባ ተሳታፊዎች የተነገራቸው መልስ እንደ መዝሙር አንድ ዓይነት ነበር በማለት አንድ ባለደረቦቻቸው በስልክ የነገሩአቸው ሰው በቡድን ስንወያይ ሲነግሩን የላይ ላይ ፈገግ አልን፡፡
በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ሰላም፣ ዲሞክራሲና አክራሪነት በሚል የግንዛቤ ማስጨበጫ ባቀረቡት ድንገተኛ ሰነድ ገለፃ ከተደረገ በኋላ አንዳንዶቹን አክራሪነቶች ከእውነተኛ ክስተቶች፣ መረጃዎችና ክንውኖች ተነስተው አክራሪነት በኢትዮጵያ ያለውን ተግዳሮት ሲያትቱ መቼም በዲሞክራሲያዊ እኩልነት ማለት ሁሉንም መውቀስ ወይም እኛስ፣ እነርሱስ የሚል ጥያቄ እንዳያስነሳ ወይም ደግሞ ገዢው ፓርቲ ያልወደደውንና ገመናዬን በቀላሉ ሊያይብኝ ይችላል ወይም ደግሞ እንዲያው በደፈናው እነዚህ እንተየዎች ሁኔታቸው አላማረኝም በማለት ያልወደደውን አካል ከሽብርተኝነት ጋር በማጠጋጋት ለመወረፍ ወይም ደግሞ አሕያውን ፈርተው ዳውላውን እንደሚባለው ያለምንም ማስረጃ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተናገሩትን ሁለት ሀረጎች ይዘው እንደመዝሙር አንድ አንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እና አንድ አገር አንድ እምነት የሚል ብዥታቸውን አጉልቶ የሚያሳይ ማኅበረ ቅዱሳንን ከአክራሪነት ጋር ለማያያዝ ይሞከራል፡፡
መንግስት ያለመረጃ እንዲህ በጭፍንነት መናገር እፍረት ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ በአደባባይ ጡምራው እንደነገረን ከ2500 በላይ የተለያዩ ፎቶዎችን ወስዶ መርምሮ አንድም አንድ አገር አንድ እምነት የሚል ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች እንዳልነበሩና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየት እንዳመጡት በመጠየቅ ነበር ያስገነዘበን፡፡ እኔ ደግሞ ከኤፍሬም እሸቴ በተለየ መልክ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የጥምቀት አከባበርን በጃንሜዳ እየተገኘሁ ተካፍያለሁ፡፡ እናም በኔ ግምት ምንአልባት በጃንሜዳ የተከናወነውን ድርጊትና የባዕል አከባበር የካሜራ ዓይኖች በተሻለ እነርሱ ያልደረሱበትን ለመመልከት እችላለሁ ባይ ነኝ፡፡ አንድ አገር አንድ እምነት የሚል ፅሑፍ ያለው ቲሸርት የለበሰ አንድ ወጣት እንኳን አላየሁም፡፡ የጥምቀትን በዓል በዚህ በደመቀ ሁኔታ ማክበር የተጀመረው ደግሞ በ2001 ዓ.ም ነው፡፡ ምናልባት ከዚያ በፊት እንዲህ አይደለም ለማለት ሳይሆን መንገዶችን በባንዲራ በማስጌጥ፣ በታቦታቱ መንገድ ምንጣፍ በማንጠፍ፣ የኖኅ መርከብ ምሳሌ የሆነች ቅርቅ ያለባት ሰረገላ ማዘጋጀት፣ የበለጠ ቀድሞ ይከበር ከነበረው ይልቅ ደማቅ ለማለት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ በ2001 ዓ.ም ጀምሮ ሲለበሱ ከነበሩ ቲሸርቶች ላይ ወጣቶቹ የለበሱት በኤፌሶን 4፡4-6 ያለውን አንድ ጌታ፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንዲት ሐይማኖት የሚል ነው፡፡ አንዲት ሀገር አንዲት እምነት የሚል ሃሳብ በኦርቶዶክስ ዘንድ የጠበበ አመለካከት የለም፡፡ እኔ የምለው ግን የተለየ ነው፤ ጠባብ ይልቁንም ከምናስበው በላይ ጠባብ ኢህአዴግና አባላቱ ናቸው- ሁሉም ባይባል፡፡ ያለ እኔ ነብይ፣ ያለ እኔ ለሃገር ተቆርቋሪ፣ ያለ እኔ አዋቂ፣ ያለ እኔ የልማት አርበኛ ወዘተ የለም በማለት አክራሪነት ወደ ፍጹምነት ያደረሰው፡፡ ሁሉም የተሰማውን መተንፈስ የሚችልበት ነጻ ሚዲያ ቢኖር በድብቅ ማንም ሳይሰማ ወይም ከጠላት ጋርም በማበር መብትን ለማስከበር የሚሄድ አይኖርም፡፡ እዚህ የሚፈልገውን እድል ካገኘ ምን ውስጥ ለውስጥ አስኬደው?
የኛ ሀገር መሪዎች የሐገር ወበት፣ የቱሪዝም መስፋፋት፣ የሐገር ባህል ድምቀትና ይትባሃሉ፣ ወዘተ መናቸውም አይደል፡፡ እንዲያውም ምልክት የለሽ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ምልክታቸው መሆኑን የሚያፍሩበት፡፡ አንድ ጊዜ የሆን ስልጠና ሲጀመር አንድ ጓደኛየ ታዝቦ የነገረኝን ላካፍላችሁ፡፡ ሥልጠናው የሚሰጠው በአሜሪካዊ ድርጅት ሲሆን የሥልጠናው አማካሪ ደግሞ የኢጣሊ ድርጅት ነው፡፡ እናም የእነዚህ ድርጅቶች ኃላፊዎችና የኛ ሀገር ሥልጠና የሚሰጥበት ሚኒስትር ሦስቱም ንግግር ሲያደርጉ የአሜሪካው ንግግሩን ሲጨርስ “God Bless You!” ማለትም ኢግዚአብሔር ይባርካችሁ ብሎ ጨረሰ፡፡ የኢጣሊው ደግሞ “God Bless Ethiopia” ማለትም እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ብሎ ደመደመ፡፡ የኛው ሚኒስትር ከእነዚህ ከሁለቱ ቀጥሎ በመጨረሻ ንግግሩን ሲጨርስ “Thank you!” በማለት ጨረሰ፡፡
የሩሲያው ቪላድሚር ፑቲንና አቻቸው ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ የፋሲካና የልደት የሩሲያን ኦርቶዶክስ የአራት ሰዓት ቅዳሴ ቁመው ነው የሚያስቀድሱት፡፡ እንዴት ያስቀናል ይህንን ማየት- አንድ መሪ ማንነቱን ሲኮራበት፣ ሲኖረው፣ ሲያስተዋውቀው …. የኛ መሪዎች ቅዳሴ ቁመው ባያስቀድሱ ግን ሕያው የሆነውን የአቢያተ እምነቶችን በተለይም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እሴቶችን ትውልዱ በኩራት እንዲያስቀጥላቸው እውቅና ለምን አይሰጠውም! ወይም ቢያንስ ይህንን ያደርግ ዘንድ የእነርሱን የማይረባ ስጋትና ፍረጃ ሳይሰቀቅ እንዲያከብር፣ እንዲኖር ለምን አይተውትም!!
ማኅበረ ቅዱሳን እነዚህን ሕያው የሆኑ ሐይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶቻችንን እንዲቀጥሉ ለማድረግ የእነዚህ ሕያው እሴቶች ምንጭ የሆኑትን የአብነት ት/ቤቶችን፣ አድባራትን፣ ገዳማትን ወዘተ መርዳት፣ ወጣቱ ትውልድ እናት ቤተከርስቲያንን በስማ በለው ሳይሆን በሚገባው መጠን ሳያጋንን ሳያንኳስስ ትክክለኛና ወቅታዊ ትምህርት ማስተማር፣ የወደፊት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ግብረ ገብነትን ማስተማር፣ ጨዋና ትጉህ፣ ሩህሩህና፣ ግልፅ፣ ቀጥተኛና ሐቀኛ ወዘተ አድርጎ ማውጣት ነው ዓላማው፡፡ እንግዲህ ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት ሰው አይፈልግ ይሆናል፡፡ የአለቃ አይንና ግንባር ዕያየ የሚያድር አድሓሪ ይሆናል የሚፈልገው፡፡ ይህ ከሆነ በማኅበረ ቅዱሳንና በኢህአዴግ መካከል የዓላማ ቅራኔ “conflict of interest” ተከስቷል እንላለን፡፡ ሌላ ግን በምንም መስፈርት፣ በምንም መንገድ ያለ በቂ መረጃና ጥናት ማኅበረ ቅዱሳን ወይም አንድ አንድ አባላቱ አክራሪ ሊያስብላቸው የሚችል ምንም ምክንያት የለም- ስም በመለጠፍ ጠላት መስሎ ለታየን ማንገራገሪያ ለመስጠት ታስቦ ካልሆነ በቀር፡፡  

1 comment:

  1. GOOD STARTING KEEP IT UP,GOD BE WITH OUR SUCCESS!

    ReplyDelete