Saturday, June 23, 2012

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አስር)


ያለፉትን ተከታታይ ክፍሎች ለማንበብ ከፈለጉ፡- 
8. ክፍል ስምንት 
9. ክፍል ዘጠኝ

ባለፈው ክፍል የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ እስከ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ያለውን ለመመልከት ሞክረናል፡፡ ዛሬ ከዚያ በኋላ ያለውን ዘመን እንቃኛለን፡፡

ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የኢትዮጵያን ነፃነት በአደዋ ድል በማስከበራቸው የአውሮፓውያን ሐይማኖታዊ መስፋፋትም በቤተክርስቲያን ላይ ሊያሳድረው የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ በወቅቱ ሊቀለበስ ችሏል፡፡ የዘመን ጠባሳ በኢጣሊያ ደም ናፋቂዎች እና አረመኔዎች እንዳያስከትል ብሎም የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ በመሆን ዳግም የአሸናፊነት መንፈስን በአፍሪካ እና በሌሎች ቅኝ ተገዢዎች ላይ እፍ ያለችው ኢትዮጵያችን በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የአደዋ ድል አድራጊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዛሬዋን ቅርፅ እንድትይዝ ያደረጉ ጠረፋማ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ መሪ ያልነበራቸውን ጎሳዎች በማስገበር የማዕከላዊ መንግስት አካል በማድረግ ከአራቱም አቅጣጫ ቅኝ ገዢዎች እጅ ያዳኑ እስከ ሶማሌ ጠረፍ ሄደው የኢትዮጵያ ድንበር ከልለው እና ወሰን አስከብረው የተመለሱ የድንበር ምልክትን ለቅኝ ገዢዎች በማሳየት ኢትዮጵያየን እንዳትነኩብኝ ብለው የጠረፍ ጎሳዎችን የነፃነት መብት ያስከበሩ ታላቁ የሺህ ዘመን መሪ ናቸው፡፡ ምናልባት በዚህ ባሳለፍነው ሺህ ዘመን ንጉስ ላልይበላ በአስተሳሰቡ ከእርሳቸው ይሻል ይሆናል፡፡ ከሌሎቹ ግን እጅግ በጣም የላቁ ምርጥ የሀገራችን ብሎም የቤተክርስቲያናችን ባለታሪክና ባለውለታ ናቸው፡፡  ኢትዮጵያ ደግ እና ብልህ ጀግናና ታጋሽ ድል አድራጊና ትሁት መሪዋን በእርጅና ምክንያት የምታጣበት ዘመን እየተቃረበ በመጣ ጊዜ ልጅ ኢያሱ ገና በ፲፪ ዓመቱ አልጋወራሽ ሆኖ ተመረጠ፡፡ በልጅ ኢያሱ ዘመን ልጅ ኢያሱ ገና ልጅ በመሆኑ ሀገርን ያህል ትልቅ ነገር መምራት ጨዋታውን በወግ ላልጨረሰ ለእርሱ ከባድ ሥራ ነበር፡፡ በመሆኑም ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ  ጊዜ የነበረው የሀገሪቱ ታላቅነት በአንፃራዊነት የተጎሳቆለበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከሦስታ ዓመታት ያልዘለለው የልጅ ኢያሱ ዘመን በንግስት ዘውዲቱ ተተካ፡፡
ንግስት ዘውዲቱ እጅግ መንፈሳዊ ሰው በመሆናቸው ብዙውን የሀገር አስተዳዳሪነት ጉዳዮችን ለራስ ተፈሪ መኮንን አስረክበው እርሳቸው በፀሎትና ቅዳሴ በማስቀደስ ጊዜያቸውን ያሳልፉ ነበር፡፡ ራስ ተፈሪ መኮንንም ገና ለንግስቲቱ በእንደራሴነት ሳሉ ጀምሮ በኢትዮጵያ መፃኢ ጉዳዮች ላይ ታላላቅ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የጀመሩበት እና በኢትዮጵያ የዋና መሪነት ሚና መጫዎት የጀመሩበት ነበር፡፡ በንግስት ዘውዲቱ ዘመነ መንግስት በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ  የተከናወነ ዐብይ የታሪክ ምዕራፍ አልነበረም፡፡
የንግስት ዘውዲቱ ዘመን አልፎ እንደራሴው ራስ ተፈሪ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ሳይበርዳት ሳይሞቃት ነገር ግን አንድ አንድ የዘመናዊነት ምልክቶች ተጀመሩ፡፡ ብዙዎቹ በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የተጀመሩትም እየተስፋፉ መጡ፡፡ ነገር ግን የኢጣሊ የ፵ ዐመት ለኢትዮጵያ የጥፋት ድግስ እየደረሰ መሆኑን ነጋሪት ጎሳሚ ባለመኖሩ የወዳጅነት ቅርርቦሹን በተለየ ዓይን ማየት ስላልተቻለ በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት ሁለተኛው የኢጣሊያ ተግዳሮት በኢትዮጵያ ላይ ተጀመረ፡፡ በወልወል ግጭት በማሳበብ ወረራ የጀመረችው ኢጣሊያ ህልሟን እዉን ለማደረግ ግማሽ ምዕተ ዓመት ደፋ ቀና ማለቷን ጨርሳ የፍልሚያ ጥያቄ ማቅረቧ ለኢትዮጵያ ዱብዳ ሆነባት፡፡
ፋሽስት ኢጣሊያ የተጠማዉን ደም ለመጠጣት በሰማይ በምድር ከፍ ያለ ዝግጊ,ጅት አድርጎ ታሪክን ለመበቀል ህልሙንም አውን ለማደረግ ታጥቆ ተነሳና በብዙ የጦርነት አውድማዎች ላይ ድል እየቀናው የኢትዮጵያ ሰራዊት የሚጠጣው ውሃ ላይ መርዝ በአውሮፕላኝ በመርጨት ሰራዊቱን ቀድሞ ሳይዋጋ በማዳከም አረመኔያዊ ድል አድራጊነትን ተላበሰ፡፡ በማይጨው ጦርነትም የወገኖቻችን ደም በግፍ ፈሰሰ፡፡
በዚህ መልክ ከሁለት አቅጣጫ በኢጣሊ ሶማሊያና ከሰሜን ከአሁኗ ኤርትራ ድልእየቀናው የሀገሪቱን መዲና አዲስ አበባን በ፻፳፰ ዓ.ም. ተቆጣጠረ፡፡ የቤተክርስቲያን አምስተኛው የመከራ ዘመን በዚያ ዓመት ተጀመረ፡፡
የእግዚአብሔር “እንደራሴ” በሆነው የሮማ ቤተክርስቲያን ፓፓ የተባረከው የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር የተባረከበትንሥራ በይፋ በመጀመር በገዳማትና የተለያዩ አድባራት የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መነኮሳትን፣ ደናግላን፣ ገዳማዊያን እንዲሁም በተለያዩ ከተሞችና በአዲስ አበባ ያሉ ሕዝቦችን በጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከሦስት ቀን ባልበለጠ አጭር ጊዜ ውስጥ ከሠላሳ ሺህ በላይ ሰዎችን በመጨፍጨፍ አረመኔነቱን አሳይቷል፡፡
የተለያዩ ገዳማትና አድባራትና በቦምብ በመደብደብና በማቃጠል ንዋያተ ቅድሳትን በማቃጠልና በመዝረፍ ሴቶችንና ሕፃናትን በመድፈርና ከክብር በማሳነስ ወንድ ሕፃናትን ከማደጋቸው በፊት ያለ ምህረት በአደባባይ በመግደል ኢትዮጵያና ቤተክርስቲያናችን በሦስት መቶ ዓመታት ውስጥ ወደር የሌለው የአምስት ዓመት የጥፋት ዘመን በማወጅ ብዙ ጉዳት አድርሳለች፡፡
በአምላካቸው በእግዚአብሔር አምላክነት ላይ የሚያመነዝሩ የአውሮፓ መጤዎች ክህደትና በእነ ሊዮን አማካኝነት ወደ ሮማ ቤተክርስቲያን የገባውን የተሻሻለውን የንስጥሮስ ምንፍቅና በዘመነ ሱስንዮስ በሁለንተናዊ መልኩ በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ሙከራ ያደረገችው የሮማ ቤተክርስቲያን የዚያን ጊዜ ያለተሳካላትን ህልም እውን ለማደረግ ይህንን አጋጣሚ መጠቀም መተኪያ የሌለው አማራጭ መሆኑን ስላመነችበት ሮማ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ብርቱ ጥረት አድርጋለች፡፡ በገዳማውያንና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በለዩ መናንያን ላይ የደረሰው የጥፋት ውርጅብኝ በሮማ ቤተክርስቲያን ልዩ ትእዛዝ እንደሆነም እሙን ነው፡፡  ነገር ግን የቤተክርስቲያኗ ልዩ ትእዛዝ ብቻ ሳይሆን ገዳማቱና አድባራቱ የአርበኞችና ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚዋደቁ እንቁ የኢትዮጵያ ልጆች መመሸጊያ ነውም ብለው ስላሰቡም ጭምር የተከናወነም ነበር፡፡ ነገር ግን በቅርሶችና በገዳማዉያን በንዋተቅድሳት በታቦታትና በቤተክርስቲያን ቅርሶችና አልባሳት ላይ የደረሰውን ጥፋት ስንመለከት “ሐይማኖታዊ” ዘመቻም በኢትዮጵያ አንዱ አካል መሆኑን ማጤን ይቻላል፡፡ ይህም የሮማ ቤተክርስቲያን ልዩ ትእዛዝ አካል እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለዉም፡፡ የአምልኮ አመንዝራነት ብቻ ሳይሆን የፆታ ዘማዊነትንም ያስለመዱ የንግድ መልክ አስይዘው በሀገራችን የክፉ ልማድ ጠባሳ ትተው ያለፉ እነርሱው ናቸው፡፡ ድንግል እና ያልተበረዘው ሐይማኖታዊ ባህላችንን የመካከለኛው ምስራቅ የዝሙት መንፈስ የገበኘው በመጀመሪያ በአህመድ ግራኝ ዘመን በቱርኮች አማካኝነት ሲሆን በኋላም የአውሮፓ የዝሙት መንፈስ በፋሽስት ኢጣሊ አማካኝነት ነው፡፡
የብዙ ብዙ የሥነልቦና፣ የባህል፣ የሐይማኖት፣ የቅርስ፣ የመንፈሳዊነት ጥፋቶችና ስብራቶችም ተከስተዋል፡፡  
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን የኢትዮጵያ ልጆች በጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች አልቀዋል፡፡ ይህም ዘመን በቤተክርስቲያን ታሪክ
አምስተኛው የመከራና የሰማዕትነት ዘመን ሆኖ አልፏል፡፡

ብዙ የሐይማኖት መሪዎች መስዋዕትነት በመክፈል እነ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤልን የመሳሰሉ ሊቃነ ጳጳሳት እስከ ሞት የታመኑ በመሆን ሕዝቡና ምድሪቱ ለአረመኔው ቅኝ ገዢ እንዳትገዛ በመገዘትና ትግልን በማፋፋም የፀረ-ቅኝ አገዛዝን በፅኑ እንዲጣገሉ ለአርበኞች ትልቅ የሞራል ድጋፍና መነቃቃት መፍጠር ችለዋል፡፡ የብዙ እንቁ የኢትዮጵያ ልጆች ትግልና ሞትን ያለመፍራት የእግር እሳት የሆነበት የፋሽስት ጦር በመጨረሻ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈጠረው የኢጣሊያና የእንግሊዝ በባላንጣነት መቆም በእንግሊዝ ጦር ረዳትነት ከአምስት የጥፋት ዓመታት በኋላ በአርበኞች ድል በመደረጉ ኢትዮጵያን ለቆ ወጣ፡፡ በዚህ ወቅት ግን የእንግሊዝ ጦር ከአፄ ቴወድሮስ ጋር ባደረጉት ጦርነት ወቅት እንዳደረጉት ሁሉ የኢትዮጵያን አብያተክርስትያናት ቅርሶች፣ መፃሕፍት፣ ንዋያተቅድሳትና አልባሳት ዘርፈው በመሄድ ካደረጉልን ይልቅ የወሰዱብ ስለሚበልጥ እኔ በበኩሌ ያደረጉትን እርዳታ አወንታዊነት አልቀበለውም፡፡ ይልቁንም ይህ ድል አድራጊነት በዱር በገደሉ እየተንከራተቱ የጠላት ጦርን አሳሩን ያበሉት የአርበኞች ብቸኛ ድል ነው እላለሁ እንጅ፡፡

… ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment