Wednesday, June 8, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አንድ)

በመጀመሪያ ደረጃ ዓለማቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችውን የፈተና እና የመከራ ዘመናት ብንመለከት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን በሥጋ በዚህ ዓለም በተገለጠ ጊዜ ሰይጣን እቡያን በሆኑ በአይሁድ ካህናት እና በፃፎችና ፈሪሳውያን ላይ አድሮ በእግዚአብሔር ቸርነት ለሕዝቡ ሁሉ ሲሰጥ የነበረውን የነፍስ ፈውስ የሆነውን የወንጌል ትምህርት እና የደዌ ሥጋ ፈውስ ደግሞ ተአምራቱን እነዲቃወሙ አደረጋቸው። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ዓለሙን ሁሉ እንዲሁ በመውደዱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአይሁድ ምቀኝነትን ታግሶ ወንጌልን ሰብኮልን በዚህ ዓለም ኑሮው ምሳሌውን ትቶልን መርገመ ሥጋን እና መርገመ ነፍስን በጥምቀቱ እና በሞቶ ድል ነስቶልን በትንሳኤውም ትንሳኤ ሙታንን ተስፋ አስደርጎን ክብርት ቅድስት ድንግል እናቱን እናት አድርጎ ሰጥቶን በሐዋሪያት በኩል ለትውልደ ትውልድ የሚተላለፈውን ሥርዓቱን አስረክቦን በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ።
በዐረገ በአስረኛው ቀንም መቶ ሃያው ቤተሰብ በፅርሃ ፅዮን ተሰብስበው ሳለ መንፈስ ቅዱስ ተልኮ ሐዋሪያትና አርድዕትን በዚያ በማርቆስ እናት ቤት የተሰበሰቡትን ሁሉ የወንጌል ትምህርት ያስተምሩ ዘንድ የበቁ አደረጋቸው። ይህ ቀንም የቤተክርስቲያን የልደት ቀን ተብሎ ይጠራል።
ዓለም መድኃኒቷን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳልተቀበለችው ሁሉ ሐዋሪያትም በወንጌል ትምህርትን በሚያስፋፉበት እና በሚያስተምሩበት አገር ሁሉ ቀና መንገድ አልጠበቃቸውም። ትምህርታቸው በመጀመሪያ በቤተ አይሁድ የተጀመረ ሲሆን ለምቀኝነት እንቅልፍ የማይተኙት አይሁድ የክርስቲያን ማኅበርተኞችን ያገለግሉ ዘንድ ከተሾሙት መካከል ቀዳሜ ሰማእት ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። በሌሎቹም ላይ እስራት ግርፋት እና መከራ አፀኑባቸው።
በዚህ ጊዜ የማኅበሩ አባላት በየቦታው ተሰደዱ። ነገር ግን እነዚህ የተበታተኑት ክርስቲያኖች በየሄዱበት ሁሉ የክርስትናን ትምህርት በደረሱበት ሁሉ አስፋፉት። በዚህ ጊዜም ወንጌል ትምህርት ለዓለም ተዳረሰች።
የቤተክርስቲያን ፈተና ከቤተ አይሁድ የሚመጣ ብቻ አልነበረም። ሐዋሪያት አርድእት እና ሐዋሪያነ አበው በተለያዩ የዓለም ከተሞች እየተዘዋወሩ ክርስትናን ሲያስፋፉ እና ወንጌልን ሲያስተምሩ ጣዖት አምላኪ የነበሩ አሕዛብ እና ዐላውያን ነገስታት በወንጌል መልእክተኞች ላይ ከፍተኛ እና አሰቃቂ የሆነ ስቃይ እና እንግልት አድርሰውባቸዋል። ለጣዖታቱ አገልጋይ የነበሩ ካህናት እና የአሕዛብ ነገስታት ከጣዖታት መስዋእት ከሚገኘው ገቢ የተጠቃሚነታቸው ተግዳሮት የነበረችውን እና ባዕድ አምልኮን እያወገዘች የሰበከችውን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ደፋ ቀና አሉ። ከዘመነ ሐዋሪያት ንጉስ ቆስጠንጢኖስ እስከ ነገሰበት እስከ ፬ኛው መ/ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ቤተክርስቲያን በዋሻ ከመሬት በታች ተወስና እስከ መኖር ያደረሳት ለህሊና እጅግ የሚዘገንን በክርቲያኖች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ እና ዘመቻ በተለያየ መልክ ተካሂዷል።
በዚህ ዘመን ከቤተ አይሁድ እና ከአሕዛብ ና ዐላውያን ነገስታት የሚመጣው ፈተና የቤተክርስቲያ የውጭ ፈተና ሲሆን ቤተክርስቲያን በወቅቱ ውስጣዊ ፈተናም ነበረባት። ከእነዚህም መካከል ከቤተ አይሁድ ወደ ክርስትና የተመለሱት ምእመናን እና ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና የተመለሱት ምእመናን መካከል የተፈጠረው ልዩነት ነው። ከቤተ አይሁድ የመጡት አሕዛብ ሳይገረዙ የቤተክርስቲያን ልጆች መሆን አይገባቸውም በሚል የተነሳው እና የቤተ አይሁድ እና የኦሪት ስርዐት ለማስቀጠል የነበራቸውን ሐሳብ ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና የተመለሱት ምእመናን በመቃወማቸው የከረረ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር። ይህም በሐዋሪያት የመጀመሪያው ሲኖዶስ እልባት ያገኘ ሲሆን ከቤተ አይሁድ የተመለሱት ብዙዎቹ ይህንን የሐዋሪያት ውሳኔ በመቃዎም ከክርስትና የወጡ ነበሩ።
ከዚህ በተጨማሪም የግሪክ የጥንት ፍልስፍና ይዘው የገቡ አንዳድ ወገኖች መዳን በእዉቀት ነው በማለት ግኖስቲዝም የሚባል ይክርስትና ትምህርትን ከግሪክ ፍልስፍና ጋር ያጣመረ አስተሳሰብ ይዘው ብቅ ማለት ሌላው የቤተ ክርስትያን ፈተና ነበር
ቤተ ክርስቲያን የተላዩ ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎችን አሳልፋ ከንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ስትደርስ በአንፃራዊነት ከውጫዊ ፈተና ፋታ ያገኘችበት እና የቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ ዘመን ነበር። በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ከመንግስት ግብር ነጻ የሆነችበት እና ምእመናን በይፋ ክርስቲያናዊ የአምልኮ ስርዐታቸውን በነጻነት ማከናወን የቻሉበት ዘመን ነበር።
በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ውጫዊ ሰላም ብታገኝም ውስጣዊ ፈተናዋ ግን በሰይጣን አቀናባሪነት መልኩን ለውጦ እጅግ በረቀቀ መንገድ ኑፋቄን ይዞ ብቅ አለ። አርዮስ በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ላይ ጥርጥር የሚነዛ ትምህርትን በማስተማር እና በግጥም እና በሌሎች የሥነ-ጽሑፍ መንገዶች በየመንገዱ እና በየአገኘው አጋጣሚ ውሃ ለሚቀዱ ወይዛዝርት እና ቆነጃጅት እንዱሁም ከብት ለሚያግዱ ወጣቶች ህፃናት እና ገበሬዎች ሁሉ እያነበበ እሳስነበበ እንዱሁም በልዩ ልዩ ዜማ እያዜመ የኑፋቄ ትምህርቱን እየነዛ ቤተክርስቲያንን መበጥበጥ ጀመረ። በሦስቱ ምእት ሊቃውንት እና ቅዱሳን አባቶች በጉባኤ ኒቂያ ተመክሮ አልመለስም በማለቱ ተወግዞ ቢለይም ተከታዮቹ ቤተክርቲያንን እንቅልፍ ነስተዋት በቅዱሳን አባቶቻችን ላይ ብዙ መከራ አጽንተውባቸዋል።
የአርዮስ ኑፋቄ በኒቂያ ጉባኤ ተወግዞ ቢለይም ሌሎች አርዮስን ምሳሌ ያደረጉ ልዩ ልዩ የኑፋቄ ሰዎች እርሱን ተከትለው በምስጢረ ስጋዌ እና በመንፈስ ቅዱስ ህልውና ላይ የጥርጥር ትምህርት አስነስተው በተለያዩ ጉባኤዎች አባቶቻችን መክረው አልመለስም በማለታቸው በአንድ ቃል አውግዘው ለይተዋቸዋል። ቤተክርስቲያን እነዚህን መናፍቃን ለማውገዝ እና ሐይማኖትን መሰረት ለመወሰን ያደረገቻቸው ጉባኤያት (ጉባኤ ኒቂያ - አርዮስን ለማውገዝ ጉባኤ ቁስጢንጢንያ - መቅዶንዮስን ለማውገዝ እና ጉባኤ ኤፌሶን - ንስጥሮስን ለማውገዝ) ናቸው። በእነዚህ ጉባኤያት መናፍቃኑን አውግዘው የሐይማኖት መሰረት የሆነውን ጸሎተ ሐይማኖትን ሰርተውልን አልፈዋል።

...ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment