ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታታይ ፅሑፎችን ለመመልከት እንሞክራለን።
የኢትዮጵያን የክርስትና አመጣጥ እና አምልኮተ እግዚአብሔር ስንመለከት ታሪኩ ከክርስቶስ ልደት በፊት ብዙ ሺ ዘመናትን አቋርጦ ወደ ኋላ ይወስደናል። ይህም ኢትዮጵያ በሦስቱም ዘመናት እግዚአብሔርን እያመለከች የምትኖር ብቸኛ ሀገር ያደርጋታል። ይኸውም በዘመነ ሕገ-ልቦና በዘመነ ኦሪት እና በዘመነ ወንጌል ናቸው። የኢትዮጵያን በዘመነ ሕገ-ልቦና እግዚአብሔርን ታመልክ እንደነበር የሚያሳየው በዘፀአት ላይ የተፃፈው የሙሴ ወደ ምድያም ምድር መሰደድ እና በዚያም የካህኑ የዮቶር በጐች ጠባቂ እንደነበር የካህኑ የዮቶርን ልጅም አግብቶ እንደነበር በዚህም በኋለኛው ዘመን እስራኤልን ከግብፅ ባርነት አውጥቶ እየመራ ወደ ከነአን ምድር ሲወስዳቸው ኢትዮጵያዊቱን በማግባቱ በእህቱ በማሪያም እና በወንድሙ በአሮን ተቃውሞ እንደገጠመው ያሳያል። ዮቶር ካህን መሆኑ የሚያስረዳው በኢትዮጵያ ከሙሴ ወደ ካህኑ ዮቶር መምጣት በፊት በውል የተረዳ እና ለብዙ ጊዜ የቆዬ አምልኮተ እግዚአብሔር እንደነበር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካህኑ እና የሳሌም ንጉስ መልከጼዴቅ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እና ኢየሩሳሌምንም መመስረቱ በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ፀንቶ የቆየ አምልኮተ እግዚአብሔር እንደነበር ያሳያል።
በመፅሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ክፍሎች እንደተገለጠው ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ እንኳን የተወሰደው ኩሽ የተባለ የኖህ የልጅ ልጅ (የካም ልጅ) የመሰረታት ሀገር መሆኗን እና በስሙም ኩኝ ተብላ የምትጠራ ሀገር እንደነበረች ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜም ብሉያት መፅሐፍትን ከእብራይስጥ ወደ ፅርዕ ቋንቋ የተረጎሙ ሰብአው ሊቃናት ኩሽ የሚለውን በተለያዩ የብሉያት መፅሓፍት ያለውን የሀገሪቱ ስም ኢትዮጵያ ብለው እንደተረጎሙት ይህም የኩሽ ሌላው ስሙ ከሆነው ኢትዮጲስ የተወሰደ መሆኑን እንገነዘባለን።
ኦሪት ሕግ በሲና ምድረ በዳ በሙሴ በኩል ከተሰጠ ከ፪፻ እስከ ፫፻ ዓመታት ጊዜ በኋላም ንጉስ ሰሎሞን የእስራኤል ንጉሳቸው በነበረበት እና በኢትዮጵያም ንግስት ማክዳ በነገሰችበት ዘመን የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ንግስት በተጓዘችበት ጊዜ ከንጉስ ሰሎሞን ፀንሳ ስለተመለሰች ቀዳማዊ ሚኒሊክን ወለደች። ቀዳማዊ ንጉስ ሚኒሊክም ፳፪ ዓመት በሞላው ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄዶ ከአባቱ ዘንድ ለ፫ ዓመት ያህል ሥርዓተ ንግስናን ተምሮ ሕገ ኦሪትን እና ከሙሴ እስከ ሰሎሞን ያሉትን የብሉያት መፃሕፍት ይዞ ፫፻፲፰ ሌዋውያን ካህናትንና ወደ ፲፪ ሺ የእስራኤል የበኩር ልጆችን አስከትሎ ወደ ኢትዮጵያ መጣ።
በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሕገ-ለቦና ወደ ዘመነ ኦሪት የተሸጋገረችው። በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ ካሉት የተለያዩ ማስረጃዎች በተጨማሪ ሀገራችን በዘመነ ኦሪት አምልኮተ እግዚአብሔር ስትፈፅም የነበረች መሆኗን እስከ አሁን ህያው በሆኑት የኦሪት መስዋዕት ሲሰዋባቸው የነበሩ የተለያዩ አድባራት እና ገዳማት እንዲሁም በውስጣቸው የሚገኙት ንዋተ ቅድሳት ቋሚ ማስረጃዎች መረዳት ይቻላል። ከዚህ መተጨማሪ የሕዝቡ አኗኗር እና ሐይማኖታዊ ባህሉ የኦሪት ዘመን ትላልቅ አሻራዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር በነበራት ጥብቅ ግንኙነት ከሰሎሞን በኋላ የተፃፉትን የነቢያት መፃሕፍት በየጊዜው ተከታትላ በማስገባትና ሁሉም መፃሕፍት ወደ ግዕዝ ቋንቋ ተተርጉመው ሕዝቡ እንዲገለገልባቸው ስታደርግ እና እግዚአብሔር ጋር የነበራትን ጥብቅ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ችላለች። እንዲያውም በአንድ ወቅት ናቡከደነፆር እስራኤልን በማረከ እና ኢየሩሳሌምን ባቃጠላት ጊዜ በእስራኤል የነበሩት ከዚህ ዘመን በፊት የጠፉ የብሉያት መፃሕፍት ምንጭ በመሆን የቅዱሳት መፃሕፍትን መጥፋት ታድጋለች።
ኢትዮጵያ በነቢያት የተነገረውን እና በብሉያት መፃሕፍት የተፃፈውን የመሲህ ክርስቶስ መምጣት ነቅታ እና ተግታ ተስፋዋን እየተጠባበቀች ሳለ ከብዙ ዘመን በፊት በነበረ የኢትዮጵያ ንጉስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ገላጭነት ቅድስት ድንግል ማሪያም ከተወደደው ልጇ ጋር ሆኖ የተሰራ ስዕለ አድህኖ ያለበት የኮከብ ቅርፅ ሰርቶ ዓለምን ሊያድን የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ከዚህች ቅድስት ንፅህት ድንግል በሥጋ እነደሚወለድ ለልጆቹ ነግሯቸው። ይህ ትንቢት ሲፈፀም ይህ ኮከብ ካለበት ተነስቶ ብርሃን እያበራ መሲሁ ከተወለደበት ቦታ እንደሚሄድ እና ይህ ክስተት ሲከሰት ተከትለው ሄደው እንዲሰግዱለት እና ግብርም እንዲገብሩለት አደራ ትቶላቸው እንደሞተ እና ይህ አደራ ከልጅ ልጅ እየተላለፈ ጌታችና መድኃኒታችን በቤተልሔም ከእመቤታችን ሲወለድ የነበረው የኢትዮጵያ ንጉስ ባዜን የተተወለትን አደራ ተቀብሎ ወርቅ እጣን እና ከርቤ ይዞ ኮከቡን ተከትሎ ወደ ቤተልሔም እንደሄደ በመንገድም ሌሎች የፋርስ እና የባቢሎን ነገስታት አብረውት እንደሄዱ ወንጌልም ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ብሎ ከሚጠራቸው አንዱ የኢትዮጵያ ንጉስ እንድሆነ ይነገራል።
እንዲሁም በሐዋሪያት ሥራ ላይ እንደተገለጠው የኢትዮጵያ ንግስት ህንደኬ ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሰግድ እና ሊሳለም እንደሄደ በዚያም በጌታችን ፈቃድ እና በሐዋሪያው በፊሊጶስ አስተማሪነት እና አጥማቂነት የወንጌል ዜናዋ ወደ ኢትዮጵያ ጌታችና እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአረገ በአስረኛው ቀን እንደተሰበከ እንረዳለን። ይህም የቤተክርስቲያን ልደት ተብሎ በሚጠራው እና በሐዋሪያት ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ቀን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም በዚያችው እለት በኢየሩሳሌም በነበረው ጃንደረባዋ ልደቷ ሆነ። ጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋሪያትን “እናንተስ እኔ ማን እንደሆንኩ ታላላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ሰዓት ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ የመሰከረውን ቃል ይህ የኢትዮጵያ ጃንደረባም ፊልጶስን “እንዳልጠመቅ ምን ይከለክለኛል?” ብሎ ሲጠይቀው “ብታምን ተፈቅዷል” ባለው ጊዜ “ኢየሱስ ክርቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ” በማለት የቅዱስ ጴጥሮስ መልስ እና እምነት የቤተክርስቲያን መሰረት የሆነ ዐለት እንደሆነ ሁሉ የቅዱስ ጴጥሮስን እምነት ይህ ጃንደረባ ይዞ በመገኘቱ ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የማይነቃነቅ መሰረት ሆኖ በዚች ቀን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ተወለደች።
ከቤተ አይሁድ ተለይታ ክርስቶስን በመቀበል እና ከሌሎች በዓለም ላይ ከሚገኙት አቢያተ ክርትያናት ተለይታ ከአምልኮት እግዚአብሔር ወደ አዳም ተስፋ ፍፃሜ ወደ ሆነው ክርስትና ተሸጋገረች። ይህ የወንጌል ዜና በዚህ ጃንደረባ አማካይነት መጀመሪያ ከቤተመንግስቱ ሰዎች ጀምሮ እስከ ተራው ሕዝብ የተዳረሰ ሲሆን በኢትዮጵያ ወንጌል ተስፋፍቶ መፃሕፍት በስፋት እየተተረጎሙ ትምህርት በስፋት መሰጠት የተጀመረበት እና ሕዝቡ ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ እንዲወለድ ማጥመቅ የተጀመረው በ፬ኛው መ/ክ/ዘመን ሶሪያዊው ቅዱስ ፍሬምናጦስ በቅዱስ አትናቲዎስ እጅ ጵጵስና ተሹሞ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ ጊዜ ነበር። ከዚህ ዘመን ጀምሮ ደግሞ የሐዲሳት መፃሕፍት ከተለያዩ ቋንቋዎች ወደ ግዕዝ እየተተረጎሙ በስፋት ትምህርት ለሕዝቡ ሁሉ መሰጠት የተጀመረበት እና ክርስትና ተጠናክሮ የተጀመረበት ነበር።
በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ ከዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኋላ በኢትዮጵያ የነበረውን ሁኔታ እንመለከታለን።
No comments:
Post a Comment