Wednesday, June 29, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አምስት)

ክርስትና በኢትዮጵያ በ፬ኛው መ/ክ/ዘመን ጀምሮ በነበረው እጅግ ጠንካራ የወንጌል እና የክርስትና ትምህርት መስፋፋት ብዙ ሕዝብ ከንጉሳውያን ቤተሰብ ጀምሮ እየተጠመቀ የክርትና ሐይማኖት ተከታይ ሆነ። ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ እስከተሾመበት እስከ አብርሃ ወአፅብሃ ዘመነ መንግስት ድረስ የወንጌል ዜናዋ በሀገራችን ቢነገርም ሕዝቡን ግን በማጥመቅ የመንፈስ ቅዱስ ልጆች እንዲሆኑ ማድረግ አልተቻለም ነበር። በመካከለኛው ምስራቅ እና በሮማ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ርቱዐነ ሐይማኖት አባቶች በሮም ቤተክርስቲያን አማካኝነት በኬልቄዶን ጉባኤ የተጀመረው ኢ-ፍትሐዊ ድብደባ እና እንግልት በ፭ኛው መ/ክ/ዘመንም ሐይማኖታችንን አንክድም ምስክርነታችን አይታጠፍም ባሉት ቅዱሳን አባቶች ላይ ስለቀጠለ ዘጠኙ (ተሰዐቱ) ቅዱሳን የሮማ ቤተክርስቲያን ታስተዳድራቸው ከነበሩት ከተለያዩ የሮም ግዛት ተሰደው በእግዚአብሔር መሪነት ወደ ኢትዮጵያ መጡ።
እነዚህ ቅዱሳን ወደኢትዮያ ከመጡ በኋላ ግዕዝ ቋንቋን በሚገባ አጥንተው የተለያዩ ቅዱሳት መፃሕፍትን ወደ ግዕዝ በመተርጎም ወንጌልን ለሕዝቡ እንዲስፋፋ ወንጌል በማስተማር የተለያዩ ገዳማትን በመመስረት ሥርዐተ ምንኩስናን በማስተማር እና በማስፋፋት የቤተክርስቲያንን ትምህርት (ግብረ ዲቁና እና ምስጢረ ክህነትን) በማስተማር ወዘተ የቤተክርቲያኗ የመሪነት ሚና በመንፈስ ቅዱስ እና በተለያዩ አገራዊ ጉዳይ ከፍተኛ እመርታ እንዲያሳይ አድርገዋል። እነዚህ ቅዱሳን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባፈሯቸው ሊቃውንት አማካኝነት በአራቱም አቅጣጫ ትምህርተ ሐይማኖት በሚገባ ተጠናክሮ ቀጠለ። እንግዲህ በዚህ ጊዜ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃያል የነበረችበት እና በስልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰችበት ጊዜም ነበር። በዚህ ጊዜ የተለያዩ ቅዱሳን አባቶች የወጡበት ሲሆን ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ያሬድን ኢትዮያ የወለደችው በዚህ ጊዜ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከ፬ኛው መ/ክ/ዘመን እስከ ፰ኛው መ/ክ/ዘመን ድረስ ከፍተኛ እድገት ያስመዘገበችበት እና በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ አወንታዊ የመሪነት ሚናዋን የተጫወተችበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል። በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭም በየመን የናግራን ሰማእታትን በይሁዲዎች መጨፍጨፍ ያስቆመች ብርሃኗ ከሕዝቧ ተርፎ ለዓለም ያበራበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል።
በዚህ ሁኔታ እያለች ነው እንግዲህ በመካከለኛው ምስራቅ የተነሳው የእስልምና ማዕበል በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖውን እያሳረፈባት የመጣው። እስልምና በ፯ኛው መ/ክ/ዘመን በአረቢያ ምድር ተጠንስሶ በሀገሬው ሰዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው "ነብዩ" መሀመድ ተከታዮቹን ኢትዮጵያ ውስጥ በየዋህነቱ እና በእንግዳ ተቀባይነቱ የታወቀ ንጉስ አለ እና ወደዚያ ሽሹ በማለት ወደ ሀገራችን ሲልካቸው ሀገራችን በመልካም ሁኔታ ተቀብላ ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ አስተናገደቻቸው። ይህም በወንጌል ከተፃፉት ስድስቱ ቃላተ ወንጌል አንዱ እንግዳ ሆኜ ብመጣ ተቀብላችሁኛል የሚለውን መተግበሯ ነበር። ኢትዮጵያ ይህን በማድረጓ በቁራን ላይ አደራ ተቀባይ እና ባለውለታ ተደርጋ ትፃፍ እንጅ በወቅቱ ከነበረው የእስልምና አፍራሽ ስራዎች ልትድን አልቻለችም። በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ እንዲገታ እና ቀስ በቀስ ሀገሪቱ እየተዳከመች እንድትሄድ በኋላም የእስልምና መሪዎች ሰለባ እንድትሆን የማዳከም እቅድ ተነድፎ በሙስሊም መሪዎች ተተገበረ። በዚህ የተነሳ ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ለምነቱን ከማጣቱ በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴው እክል ሲገጥመው የአክሱም ሥርወ መንግስት ቀስ በቀስ እየተዳከመ መጣ።
ከዚህ በሀገሪቱ ማዕከላዊ መንግስት መዳከም ተከትሎ በ፱ኛው መ/ክ/ዘመን ዮዲት የተባለች አይሁዳዊት ሴት (ከፈላሻ ዘር) በሀገራችን ላይ ከፍተኛ የጥፋት ዘመን አዋጅ አውጃ ብዙ ቤተክርስቲያናት አድባራት ገዳማት ቤተመዛግብት ንዋተቅድሳት መፃሕፍት እና አልባሳት ተቃጥለዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ዲያቆናት ካህናት መምህራን መነኮሳት እና ገዳማውያን ተሰውተዋል። ለ፵ ዓመታት ባደረሰችው የጥፋት ዘመቻ ብዙ የቤተክርስቲያን መረጃዎች ጠፍተዋል። ይህ የዮዲት ጉዲት ዘመን በሀገራችን ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ከፍተኛ ጥፋት ያስከተለ እና ለረጅም ዘመናት የቆየ የሰቀቀን እና በሀገራችን ከነበሩት የቤተክርስቲያን አሰቃቂ የመከራ ዘመናት የመጀመሪያው ነው። በዚህ አሰቃቂ የግፍ እና የመከራ ዘመን የአክሱም ሥርወ መንግስት እጅግ ተዳክሞ የቤተክርስቲያኗ ትምህርትም ለ፵ ዘመናት ተስተጓጉሎ ቆየ።
የዮዲት ጉዲት ዘመን በቅርሶች እና መፃሕፍት መውደም በክርቶያኖች መጨፍጨፍ እና በአቢያተ ክርስቲያናት መቃጠል ከፍተኛ የሞራል እና የሥነልቦና ውድቀት ቢያጋጥምም የሐይማኖታዊ ባህል መዛባት እና የረጅም ጊዜ ጠባሳ በሕዝቡና በክርትና ሐይማኖት ላይ አልተወም። ይህም በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፦
፩. በዚያ ጊዜ የነበረው የሕዝቡ የሥነልቦና ጥንካሬ በዚያ ጊዜ የነበረው ሕዝብ እና መንግስትም ቢሆን ለዓለማዊ ኑሮ ዋጋው አነስተኛ እና ከሞት በኋላ ያለው ህይወት አማራጭ የሌለው በሌላ ዝባዝንኬ እና እራስን በመደለል ሊታለፍ እና ሊናቅ የማይችል መሆኑ ሕዝቡ በሚገባ የተረዳው ሀቅ ነበር። በዚህ የተነሳ ሐይማኖትን ከመተው እና ሐይማኖታዊ ያልሆነ ድርጊት እና ሥራን በወቅቱ በነበረችው ጨካኝ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ከመበገር ይልቅ ሞቶ የህይወት አክሊልን መቀበል የሚመርጥ ለፅድቅ የጨከነ ልብ ያለው ሕዝብ ነበር ማለት ይቻላል።
፪. የበኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩት አይሁዶች (ፈላሾች) ከክርቲያኖች ጋር የነበራቸው የባህል ውርርስ እና መመሳሰል፦ አይሁዶች ከክርቲያኖች ክርቲያኖች ደግሞ ከልደተ ክርስቶስ በፊት በነበራቸው ኦሪታዊ ሐይማኖታዊ ልምድ የተነሳ በነበረው የባህል መመሳሰል የዮዲት ጉዲት የጥፋት ዘመቻ የባህል አብዮት አልነበረውም።
፫. የዮዲት የጥፋት ዘመቻ በውል የታወቁ ግቦች ስላልነበሩት፦ ከክርትና ወደ ይሁዲነት በሃይል ለመቀየር ከመታሰቡ በቀር ከጭፍን ጥላቻ የመነጨ ስለነበር የራሱ ግብ ያለው ዘመቻ ስላልነበር ስር ነቀል የሐይማኖታዊ ባህል ለውጥን መሰረት ያደረገ አልነበረም።
፬. ከጥፋት ዘመኑ ማለፍ በኋላ የተከናወነው የመልሶ ማቋቋም ከፍተኛ ጥረት የተለያዩ ቅዱሳን በቃላቸው ያጠኑትን በብራና ላይ በመፃፍ እና በተለያየ ምክንያት ከጥፋት የተረፉትን ደግሞ በማባዛት አዳዲስ መፃሕፍትንም ፅፎ ለተላዩ በሐገሪቱ በሚገኙ ት/ቤቶች በማሰራጨት የተቃጠሉ አቢያተክርስቲያናትን መልሶ በማቋቋም እና በመገንባት ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ በዚህ ዘመን የደረሰው የጥፋት ቁስል ወዲያውኑ ሊያገግም ችሏል። ይህም ወርቃማው የሥነፅሑፍ ዘመን ተብሎ የታወቀውን ብዙ አባቶቻችን እስከዛሬ የምንገለገልባቸውን መፃሕፍት የፃፉ እና ወንጌልን በድፍረት የጣኦት አምልኮ ያመልኩ ከነበሩ መሳፍንት እና የተለያዩ ጎሳዎች ድረስ የተሰበከበትን ዘመን አስከትሏል። ይህ ዘመን ቤተክርስቲያን ተመልሳ ያበበችበት ዘመን ነበር።
በእስልምና እና በዮዲት ጉዲት አሰቃቂ ዘመን አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት የአክሱም ሥርወ መንግስት እየተዳከመ ሄዶ መጨረሻ የዛግዌ ሥርወ መንግስት ተመስርቶ የአክሱም ሥርወ መንግስት ሕልውና በዚሁ አከተመ። የዛግዌ ሥርወ መንግስትም የመናገሻ ከተማውን ከአክሱም ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ላስታ አዛወረው።
ኢትዮጵያ በዛግዌ ሥርወ መንግስት አስተዳደር ከሀገሪቱ ሰሜናዊ ጫፍ በአንፃራዊነት ወደ ደቡብ በመሸሿ ምክንያት ሰሜናዊ የኤርትራ ክፍለ ግዛቶች የእስልምና ተከታይ ነጋዴዎች መፈንጫ እንድትሆን በር የከፈተ ሲሆን በሀገሪቱ ላይ ያሉትን የንግድ ወሳኝ መስመሮችንና የባህር በሮችን ለመቆጣጠር አዳጋች ስለነበረ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትም የዚያኑ ያህል አዝጋሚ እንዲሆን ተገዷል። በባህር በር አካባቢ ያሉ የሀገሪቱ ጎሳዎች የእስልምና ሰለባ መሆን እስልምና ወደ ሀገሪቱ በወላሉ የመግቢያ እና የመቦረቂያ በር ክፍት ሆኖ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ በቤተክርስቲያን እድገት ላይ አሳርፏል። በርግጥ የሀገራችን ልዕልና ከአክሱም ሥርወ መንግስት ጊዜው ጋር ሲመዛዘን ያነሰ ቢሆንም ሀገሪቱ በዛግዌ ሥርወ መንግስትም የሀገራችን የሞራል ልዕልና እና የኪነጥበብ እድገት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት እና ሐይማኖታዊ እድገትም እንደተመዘገበ በዘመኑ ከተሰሩ ሥራዎች ምስክርነት እና ከተለያዩ የታሪክ ድርሳናት መገንዘብ ይቻላል።
በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ በዛግዌ ሥርወ መንግስት የነበረው የሐይማኖታዊ እድገት ተመልሶ ማበብ እና የመካከለኛው ዘመን የሀገሪቱን ታሪክ እንቃኛለን።
...ይቀጥላል…



1 comment:

  1. keep it up i learn alot from u .God be with u all the time

    ReplyDelete