Saturday, June 11, 2011

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል ሁለት)

በእናት ቤተክርስቲያን ከ፷ ዓ.ም እንከ ፫፻፲፪ ዓ.ም ድረስ እጅግ አስከፊ እልቂት እና የስደት ዘመን የነበረ እና እጅግ ብዙ የቤተክርስቲያን ቅርሶች የወደሙበት ቢሆንም በዚህ ዘመን የነበሩት የክርስቲያኖች ሕብረት እጅግ የሚያስቀና አንዱ ሌላውን ለማዳን እራሱን አሳልፎ በመስጠት መድኃኒታችን ክርስቶስን የመሰሉበት የፍቅር ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። ምንም እንኳ በዚህ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በቁጥር አናሳ ቢሆንም ፍሬው ግን ገለባ የሌለበት ንፁሕ እና ሚዛን የሚመታ የክርስትና ሕይወት የታየበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ሊከተለኝ የሚወድ መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ ‘ ብሎ ያዘዘንን ትእዛዝ በተግባር በማሳየት የተለያዩ ሰዎችን ወደ ሕይወት ጎዳና መመለስ ከሚቻልበት ሁኔታ በቀር በመድረክ እና በአደደባባይ ሰላማዊ ስብከት እና ትምህርት መስጠት እጅጉን አሰቸጋሪ የነበረበት ዘመን ነበር።
ይህ ዘመን አልፎ ቤተክርቲያን አንጻራዊ ሰላም ባገኘችበት ዘመን መልኩን ለውጦ የመጣው የዲያብሎስ ውጊያ አርዮሳውያንን አስነስቶ ምናልባትም በዐላውያን መንግስታት ከነበረው የበለጠ በቤተክርስቲያን ላይ ጉዳት አድርሶባታል። የአርዮሳውያን ተንኮል መልኩን እየቀያየረ ቆይቶ ንስጥሮስ ባስነሳው የኑፋቄ ትምህርት ላይ አባቶቻችን በኤፌሶን ተሰብስበው ያወገዙት ቢሆንም ይህንን መሰረት ያደረገ ሌላ የኑፋቄ ትምህርት ለማራመድ የቄልቄዶን ጉባኤ ላይ እራሳቸው ጉባኤ ጠርተው ፍትህ የጠፋበት ርትዕ ሐይማኖት ጠበቃ የነበሩ አባቶቻችን ጥርሳቸው እስኪረግፍ ጺማቸው እስኪነጭ የግፍ ግፍ ተደርጎባቸው የሮማን ንጉሳዊ ቤተሰብ ፍላጎት ያንፀባረቀው እና ይህንን የሮማን ወታደራዊ ኃይል መከታ ያደረገው በሮማ ጳጳስ ሊዮን ትእዛዝ ተደብድበዋል፤ በኋላም ግዞት ቤት ተለይተው እንዲታሰሩ ተደርገው በዚያው በእስር ላይ እንዳሉ አርፈዋል።
በዚህ ጊዜ (፬፻፶፩ ዓ.ም) ነው እንግዲህ ቤተክርስቲያን ለሁለት የተከፈለችው። በሰላሙ ጊዜ የተነሳው የውስጥ ጠላት ቤተክርስቲያንን ለሁለት ከፍሎ የጥፋት ልጆችን መለመለ። በእስክንድሪያ መንበረ ፓትሪያርክ ስር የነበሩት ኦርቶዶክሳዊት እና ርቱዕ የሆነች ሐይማኖትን ፍፁም ተዋህዶን ስትሰብክ የምዕራቡ እና በሮማ መንበረ ፓትሪያርክ በሊዮን ሥር እራሷን ዓለማቀፋዊት ነኝ ለማለት ‘ካቶሊክ” ብላ እራሷን ሰይማ ሁለት ባህርይን መስበክ ጀመረች። ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰዎች ክብር ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደረገ እና ሥጋዊ ፍላጎታቸው ጐልቶ የታየበት ሥርዓትም አረቀቁ።
በዚህ ሁኔታ የሮማ ቤተክርስቲያን ሰባት ዓለማቀፋዊ የቤተክርስቲያን ጉባኤዎች አሉኝ፤ የእምነት መሰረቴ እነዚህን መሰረት ያደረገ ነው ትላለች። ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ቤተክርሰቲያን ከመከፈሏ በፊት አርዮስን፣ መቅዶንዮስን እና ንስጥሮስን ለማውገዝ የተደረጉትንም ይጨምራል። እነዚህ ሦስት ጉባኤዎች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የምትቀበላቸው ብቸኛ ዓለማቀፋዊ ጉባኤዎች ሲሆኑ ከዚያ በኋላ የሮማ ቤተክርስቲያን አራት ዓለማቀፋዊ ጉባኤያት (የውሾች ጉባኤ እየተባለ የሚጠራው የኬልቄዶን ጉባኤን ጨምሮ) አከናውናለች። ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከእነዚህ ጉባኤዎች መካከል ተሳትፎ የነበራት በጉባኤ ኬልቄዶን ብቻ ቢሆንም በዚህ ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቸል ተብሎ የሰዎች የግል ፍላጎት የተነፀባረቀበት እና ፍትህ የተጓደለበት የነገስታቱ ኃይል ተፅእኖ የፈጠረበት የሮማ መንበር የበላይነትን በመንፈስ ቅዱስ ፍቃድ ሳይሆን በንጉሳዊ ቤተሰቦች እና በሮማ የካህናት ቢሮክራሲ ፍላጎት ከእስክንድሪያ መንበረ ማርቆስ ለመንጠቅ የተሞከረበት የሰው አካል እስኪጎድል ድብደባ እና እንግልት የተፈፀመበት በመሆኑ በዚህ ጉባኤ የተከናወኑ ክንውኖችንም ሆነ ውሳኔዎች አትቀበላቸውም። ሌሎቹ ሦስቱ ግን በሮማ በብቸኝነት የተከናወኑ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ የሮም ቤተካህናት እና ንጉሳውያን የፈለጉትን የደነገጉበት በመሆኑ አትቀበለውም።
የሮማ ቤተክርስቲያን የሦስቱን የመጀመሪያ ዓለማቀፋዊ ጉባኤዎች እጋራለሁ ውሳኔዎቹምንም እቀበላለሁ ብትልም ውሳኔዎችን ግን ሽራቸዋለች። በኒቂያ ጉባኤ ሠለስቱ ምእት የወሰኑትን ሐይማኖት የሚጻረር ሐይማኖት ደንግጋቸች። ምንታዌነትን ስርዋፅ አስገብታ የአባቶች ውሳኔ ነው ትላለች። በዚህም ማንም ቀና አእምሮ ያለው ሰው ከ”ሐይማኖቶች” መካከል ትክክለኛውን ምረጥ ቢባል ታሪካዊ አመጣጣቸውን በሚገባ መርምሮ ወጥነት የሌለው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚዋዥቅ ሐይማኖት”ን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚመራ ቀጥተኛ ሐይማኖት አለመሆኑን ጠንቅቆ ይረዳል። ለታረካዊ የቤተክርቲያን የመጀመሪያ የመከፋፈል አደጋን እንዴት እንደነበር በአጭሩ እንዲህ ከተረዳን የሁለቱን ልዩነት በሚገባ ለማሳየት ግን ጊዜ ስለሚያንስ እግዚአብሔር ከፈቀደ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።
በዚህ አኳኋን ቤተክርስቲያን ለሁለት ከተከፋፈለችበት ጊዜ ጀምሮ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ህያው የሆነውን የሐዋሪያት ስብከትን መሰረት ያደረገ እና ሐዋሪያት የሰበሰቧትን ቤተክርስቲያንን ምንም ዝንፍ ሳያደርጉ ጠብቀው በትምህርታቸው በህይወታቸው በተጋድሏቸው እና መፃሕፍትን በመፃፍ እና የተለያዩ የቤተክርስቲያን ሥርዐቶችን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በመሥራት ለትውልደ ትውልድ ሳይቋረጥ ለዘመናት እንደሚፈስ ንፁሕ ወንዝ ከኛ ዘመን አደረሷት።
ይህችን ቀጥተኛ ሐይማኖት ይዘው የሚገኙ አምስቱ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Orthodox Churches) የሚባሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ አርመን፣ ሶሪያ እና ህንድ ናቸው። ነገር ግን ሌሎች የምስራቅ (Eastern Orthodox Churches) የሚባሉም አሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ዶግማና ቀኖና የኛዎቹ (Oriental Orthodox Churches) ቤተክርስቲያናት ከሚከተሉት ዶግማና ቀኖና ይለያል። እነዚህ የምስራቅ (Eastern Orthodox Churches) የሚባሉት ከ፬፻፶፩ ዓ.ም እስከ ፲፻፶፬ ዓ.ም ድረስ በሮማ ቤተክርስቲያን ስር የቆዩ ሲሆኑ በ፲፻፶፬ ዓ.ም ከሮማ ቤተክርስቲያን ተገንጥለው የወጡ ነገር ግን በብዙ የዶግማ እና ቀኖና ይዘታቸው ከሮማ ቤተክርስቲያን ጋር አንድ የሆኑ በጥቂቱ ልዩነት ያላቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው።
በዚህ ሁኔታ በሮማ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ምእመናን እና አንዳንድ ካህናት እንዱሁም መነኮሳት በቤተክርሰቲያኗ ያለውን የሥርዓትና የመሠረተ እምነት ብልሹነት እና አላግባብነት እንዱሁም የጳጳሳቱን የቅንጦት ኑሮ እና የመመለክ አባዜ በመመልከት በተላያየ ጊዜ ከቤተክርስቲያኗ እየተገነጠሉ እነርሱ የመሰላቸውን ሌላ ‘ሐይማኖት” እየደነገጉ ብዙ የጥፋት ልጆችን ልታፈራ ችላለች። በሰው እንጅ በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ባለመሆኗ አንድነቷን አስጠብቃ መቆየት ተሳናት።
ከሮማ ቤተክርስቲያን እንደ አሸን የፈሉ የምንፍቅና ጐራዎችን አወጣጥ በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን።
…ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment