Tuesday, July 3, 2012

የቤተክርቲያን የመከራ ዘመናት - ዛሬስ ሰላም ነውን? (ክፍል አስራ አንድ)



ባለፈው ክፍል አስር ላይ የቤተክርስቲያን ታሪክ እስከ ኢጣሊያ ወረራ ለመመልከት ሞክረናል፡፡ ዛሬ ደገሞ ከዚያ ጊዜ በኋላ ያለውን ዘመን እንመለከታለን፡፡
ኢጣሊያ በአደዋ ጦርነት ወቅት ተሸንፋ ሙሉ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ባትችልም ከመረብ ወንዝ ባሻገር የሐማሴን አውራጃ ጀምሮ የአሁኗ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ነጥላ መቆጣጠርና ከ1880ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በቅኝ ግዛትነት ለአርባ ዓመታት ያህል ይዛ በመቆየቷ ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ በለቀቀች ጊዜ የኤርትራ ጉዳይ ተንጠልጥሎ በመቆየት በእንግሊዝ ሞግዚትነት ለአስር ዓመታት ያህል ቆይታ ከብዙ ትግል በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደራል መዋቅር በ1952 አንድ አገር ሆነች፡፡
ነገር ግን የኤርትራ ሕዝብ በኢጣሊያ ጨካኞች አማካኝነት የደረሰበትን የቅኝ አገዛዝ በደል ቁስል በቀላሉ መርሳት ባለመቻሉ አፄ ምኒሊክ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ኤርትራን ሆን ብለው አሳልፈው እንደሰጡ የሚቀሰቅስ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የሁለቱን እናትና ልጅ መፃኢ ታሪክ በቋፍ ላይ አስቀመጠው፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ያለው የሁለቱ እናትና ልጅ ሀገራት መለያየት ዓይነተኛ ምክንያት ሆነ፡፡ በዚህም የቤተክርስቲያን አንድነትና የሊቃውንቷ ኅብረት ለሁለት ተከፍሏል፡፡ በአስተምህሮና በዶግማ አንድ በመሆናችን በአስተዳደራዊ መዋቅር ሁለት ብንሆንም ዘላለማዊ የማይፋቅ የዶግማና ቀኖና አንድነት የአስተምህሮ አንድነታችን ሰማያዊ ቤተሰብ እንዳደረገን ይቀጥላል እንጅ የአንድነት ገመዳችን አሁንም አልተበጠሰም፡፡ የአንድ ሐዋሪያዊ ተልዕኮ ውጤቶች የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ተጋሪዎች የብሉይና የሐዲስ አምልኮተ-እግዚአብሔር ብቸኛ ባለታሪኮች የእግዚአብሔር ምርጦች የፈሩባቸው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ዜጎች ምንጮች የብሉይና የሐዲሳት እዉነታዎች ቀዳማይ የመረጃ ምንጮች የቅዱሳት መፃሕፍት ትምህርቶች ማመሳከሪያዎች የብዙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ባለቤቶች የዓለም እዉነት ማመሳከሪያዎች በመሆናቸው የተለየ አንድነታችን የጠነከረ አንድነታችን እንደነበረ ይቀጥላል፡፡  
ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ ቤተክርስቲያን በአምስቱ ወረራ ዓመታት የደረሰውን ጥፋት ለማቅናት ደፋ ቀና ያለችበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ በ1940ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ አንድ አንድ የምንፍቅና እንቅስቃሴዎች ብቅ ብቅ ያሉበት ጊዜም ነበር፡፡ ነገር ግን ትጉሓን የቤተክርስቲያን ሊቃዉንት ባደረጉት የማስተማር የመፃፍ እና መልስ የመስጠት ሥራ እነዚህ የምንፍቅና እንቅስቃሴዎች ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ የተቀለበሱበት ሁኔታ ነበር፡፡
በ1950ዎቹ ደግሞ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ተማሪዎች ኅብረት “ሐይማኖተ አበው” የሚባል ማኅበር በመመሥረት ለቤተክርስቲያን ጥሩ ሥራ መሥራት የጀመሩበት በአንዳንድ ቤተክርስቲያናት ወጣቱ ትዉልድ ከእናት ቤተክርስቲያን ጋር እንዲተዋወቅ በክርስቲያናዊ ሥነምግባር እንዲታነፅ በተለይ በአዲስ አበባ ባሉ አድባራት የሰንበት ት/ቤቶች የተከፈቱበት ዘመን ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል በቀደምትነት የሚታወቀው የምስካየ ህዙናን መድኃኒያለም ቤተክርስቲያን ውስጥ የተጀመረው የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት ተጠቃሽ ነው፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ዓመታት ደገሞ የምንፍቅና ትምህርቶች በአውሮጳውያን ተፅዕኖ አድራጊነት በእምነት ነፃነት ስም ብዙ ሚሲዮናዉያን ወደ ሀገሪቱ የገቡበት እና በተለያዩ ማታለያዎች ብዙዎችን የጠለፉበት አሳዛኝ ዘመንም ነበር፡፡ በዚህም በዘመኑ የነበሩ የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች የጠፉትን በመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመከራከር ለመመለስ ባደረጉት ሙከራ የመጀመሪያ የመናፍቃን አዳራሾች እራት ሆነው ቀርተዋል፡፡ በብዙ ሰ/ት/ቤቶች የነበሩ የመጀመሪያ መስራቾች ባለማስተዋል ቤተክርስቲያንን በመተው የመናፍቃን አዳራሾችን ተቀላቅለዋል፡፡ ከውጭ የሚመጡት ሚሲዮናውያን በሥነ ልቦናና የሥነ መለኮት ትምህርት የተማሩ ስለነበሩ የእኛ ጀማሪዎች በሥነ ልቦና ብስለት ከእነዚያ የተሻሉ አልነበሩም፡፡ የቤተክርስቲያንን ተምህርትም በአግባቡ ያልተማሩ ገና ጀማሪዎች ስለነበሩ ገና በለጋ ዕድሜያቸው የደረሰባቸውን የመናፍቃን የጥቅስ መዥጎድጎድ ሊቋቋሙት አልተቻላቸውም፡፡ በዚህም ለተወሰኑ ዓመታት ቤተክርስቲያንን በማገልገል የቆየው “ሐይማኖተ አበው”ም የእነዚህ የሎች የእምነት ድርጅቶች የሥውር ዓላማ ማስፈፀሚያ በኩር በመሆን በቤተከርስቲያን ውስጥ የተጠለለ ምንፍቅና አራማጅ ማኅበር ሆኖ አረፈው፡፡ ቤተክርስቲያን መታደስ አለባት በማለት የቤተክርስቲያን መሰረት የሆነውን ዶግማና ቀኖናዋን በማፍረስ ሌላ የአውሮጳ ቤተእምነት ዶግማና ቀኖና ወደ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን አሾልኮ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ የ“በኩር” የውስጥ ፀረ-ቤተክርስቲያን ነው፡፡
በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የነበሩት የአውሮጳ ቤተእምነቶች በኢትዮጵያ የነበራቸው እንቅስቃሴ ሁለንተናዊ ድጋፍ ይደረግላቸው የነበረው በምዕራብ አውሮጳና በአሜሪካ አማካኝነት ነበር፡፡ ምዕራባውያን ዓለምን አንድ አድርጎ እነርሱ ለሚፈልጉት ዓላማና ተግባር ለማዋል የወደፊት ተግዳሮቶች ብለው በ“ጥናት” ያገኙዋቸው አራት ነገሮች ነበሩ፡፡ እነዚህም፡-
፩ኛ. የቻይናና የሌሎች የሩቅ ምስራቅ ሕዝቦች ባህል አልደፈርስ ባይነትና አልቀላቀል ባይነት
ኛ. የሩስያ ሕብረተሰባዊ ርዕዮተ-ዓለም በዓለም መስፋፋት
ኛ. የመካከለኛው ምስራቅ የእስልምና ፍልስፍና (የዓለምን ሕዝብ ሁሉ በማንኛውም መንገድ ማስለም የሚል ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ)
ኛ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት በጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ምንጭና እናት ሆና መታየት
ነበሩ፡፡
በዚህም ምክንያት ምዕራባውያን እንቅልፍ የነሱዋቸውን አነዚህን ጉዳዮች ከመቃብር በታች ለማዋል የተለያዩ ዕቅዶችና የማስፈፀሚያ ስልቶችን ነድፈው ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁን የእነርሱ እንቅስቃሴን ማተት ስላልሆነ ዓላማችን ቤተክርስትያንን የሚመለከተውን አራተኛውን “ተግዳሮት” በሚመለከት ያቀዱት ዕቅድ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ማጥፋትና በአፍሪካውያን ዘንድ የነበራትን በጐ ስዕል ማጠልሸት ሲሆን የነደፏቸውን ስልቶች ደግሞ ለዘብተኛና የዓለማዊ ኑሮ አመቻች (Facilitators) የሆኑ የምዕራባውያን ቤተእምነቶችን በመፈብረክ ያሉትንም ሉተራዊ ቤተእምነቶች ማጠናከርና በአፍሪካና በተለይም በኢትዮጵያ በስፋት መስበክ፤ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪካዊና መፅሐፍ ቅዱሳዊ “ጥናት” በማድረግ ታሪኳን የሚያኮስስ ዶግማና ቀኖናዋን ከጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት “ጥናታዊ” ድምዳሜ ላይ መድረስ፤ በተቻለ መጠን በራሳቸው በኢትዮጵያውያን አማካኝነት ቀዳሚ ተግባራት እንዲከናወኑ በጥቅማጥቅሞች በመደለል በራሳቸው ሀገር የጥፋት አምባሳደሮች እንዲሆኑ ማመቻቸት፤ ምክንያታዊነትን (Worship of Reason)፣ የገንዘብ ወዳድነትን (Greediness)፣ ለታሪክና ለባህል ግድየለሽነትን (Ignorance to Cultural Values)ና የመሳሰሉትን ባዕድና ለክርስትና ሕይወት እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን በማስረፅ ወጣቱ ትውልድ ለእናት ሀገሩ እሴቶች የማይጨነቅ ለማመን በሰዋዊ ጥበብ ሊገለፅ የሚችል ምክንያት በመፈለግ ከሐይማኖቱ እንዲርቅ በማደረግ እነርሱ ለሚፈልዱት ዓለምን በሉላዊነት (Globalization) አንድ የማድረግ ህልማቸው ጥርጊያ መንገድ ለማዘጋጀት ቤተክርስቲያንን እጅግ ሲታገሏት ኖረዋል፡፡
ምዕራባውያን የተለያዩ በቁጥር ብዛት የሚያታክቱ ነገር ግን አንዳቸውም ቁመንለታል ባሉት ዓላማቸው ዐብይ ለውጥ በአፍሪካ ያላመጡ በአፍሪካ ዕርዳታ ለመስጠት፣ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ወዘተርፈ በሚል ምክንያት በመግባት ዋና አጀንዳቸውን የምዕራባውያንን ለዘብተኛ ቤተእምነቶች እንዲስፋፉ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያከናዉኑ የቆዩ፤ አሁንም ይህንን ተግባራቸውን እየፈፀሙ ያሉ መንግስታዊ ያለሆኑ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌነት ብናነሳ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ (World Vision Ethiopia) የሚባለው መንግስታዊ ያለሆነ ድርጅት በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወረ በዕርዳታ ስም እምነትን በማስፋፋት የቤተክርስቲያን ምዕመናንን በመንጠቅ የሌሎች ቤተእምነቶች አባል እየመለመለ ይገኛል፡፡
አሁን ከላይ ለምሳሌነት ያነሳነው ምዕራባውያን እንዴት በቤተክርስቲያን ህልዉና ላይ ቁማር ሲጫወቱ እንደነበር ለማሳየት ነው፡፡ ይህ ተግባራቸው በ1950ዎቹ የተለኮሰ የሰደድ እሳት እስካሁን ባለመብረድ እራሱን እየወለደ በቤተክርስቲያን የውስጥና የውጭ እሳት በመሆን ለማቃጠል (ለማጥፋት) እየተጋ ይገኛል፡፡ነገር ግን ይህ ሁሉ ችግር በቤተክርስቲያን ላይ ቢከሰትም ቤተክርስቲያን ግን የሲኦል ደጆች አይችሉዋትም ተብሎላታልና እስከ ዘመነ ምፅአት ድረስ ፀንታ ተኖራለች፡፡ 
በዘመነ ኃይለ ስላሴ ቀዳማዊ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የታነፁ ሲሆን የኢትዮጵያ አንድ ዐብይ ጉዳይ የፈታችበት ጥሩ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ በመሰራቱ ቤተክርስቲያን ከእስክንድሪያ ተለይታ የራሷ ሊቃነ ጳጳሳት መሾምና የራሷ ፓትርያርክ መሾም የመትችልበት ዘመን የታየበት የራሷ ቅዱስ ሲኖዶስ ያደራጀችበት ዘመን ነበር፡፡
በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት አቡነ ቴወፍሎስ አማካኝነት እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን በሰበካ ጉባኤ እንዲተዳደር በማድረግ የተሻለ አስተዳደራዊ አደረጃጀት የተጀመረበት ነበር፡፡ እንግዲህ ቤተክርስቲያን በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለች ነው ሌላው የቤተክርስቲያን የፈተና ዘመን መጥቶ ድቅን ያለው፡፡ የ1966ቱ አብዮት፣ የሕብረተሰባዊነት ርዕዮተ ዓለም፣ እና ደርግ…
… ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment