Tuesday, August 21, 2012

ለሕዝብና ለቤተክርስቲያን ሰላምንና መልካም መሪን ከእግዚአብሔር ለምኑ



ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ


ሰሞኑን ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ሁለቱን ዋና ዋና የሀገሪቱን መሪዎች አጥተናል፡፡ እጅግ አስጨናቂ ጊዜ ነው፡፤ በጣምም አስደንጋጭ፡፡ ለሥጋ ለተለዩን መሪዎቻችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያና ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያሳርፍልን፡፡ በምንም በምን መስፈርት የሀገር መሪ እንኳን ወንዝ ዘመንን ያሻግራል፡፡ የኛ መሪዎች ከሁለት አስርት ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ሀገርንና ሕዝብን በመምራት ሰው በመሆናቸው ታሪካዊ ስህተት ሊፀዱ ባይችሉም ማድረግ የሚችሉትን አድርገው ሀገሪቱን አንፃራዊ የሰላም አየር ለመተንፈስ አብቅተዋታል፡፡ ይህ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ታሪክም በዚህ ተግባራቸው ሲያስታውሳቸው ይኖራል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር መለስ በልማትም ጎን ከአፄ ሚኒልክ ወዲህ አንጻራዊ በሆነ ፈጣን የልማት መንገድ እንድትጓዝ ጥሩ የአመራር ሥራ ተጫዉተዋል፡፡ አሁን ዓላምችን ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሂስ መስጠት ስላልሆነ ሂስ ተቀባይ አካል ሰምቶ የሚያስተካክለው በመሆኑ ደካ ጎናቸውን ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ሁናቴ አንፃር እናም ባለድርሻ አካላትም ሊያጤኑት የሚገቡ ነጥቦችን መጠቆም ለነገው መንገዳችን መልካም የብርሃን ጭላንጭል ሊሆኑን ይችላሉ በማለት ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦች መንግስትን የቤተክህነት ባለድርሻ አካላትና ሁላችንንም የሚመለከቱ ሲሆን ከማንኛዉም ተቋም ወይም ግለሰብ ፍላጎትና የግብ አቅጣጫ የተመሳከሩ መሆናቸውን ለማጥናት ጊዜ አተወሰደም፡፡ ብቻ በእኔ አመለካከት መልካም መስለው የታዩኝን እነሆ ብያለሁ፡-

፩. የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በሚመለከት

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከአባ ጳውሎስ በኋላ መሪዋ ማን መሆን አለበት? በሚል ርዕስ በቤተክርስቲያን የፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ለመጠቆም ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ነጥቦች በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስና የቤተክርስቲያን ባለድርሻ አካላት ከግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገቧቸው የሚያስፈልጉ ጉዳዮች፡-

  • 1.      ቤተክርስቲያን እንኳን በእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርና ርቱዕ ሐሳብ ባለው ሰው አንገት በሚያስደፋ ሁኔታ በአንድ ወቅት በአንድ አንድ አላዋቂ ሰወች ተፅዕኖ አማካኝነት በሐይማኖት ሕፀጽ ሳይሆን በአስተዳደራዊና በፖለቲካዊ ስህተት ለሁለት ተከፍላ መቅረቷ እጅግ አንጀት የሚበላ ጉዳይ ነው፡፡ እናም የአብዛኛው ኦርቶዶክሳዊ የደስታው ፍፃሜ በዚህ ዘመን እነዚህ ለሁለት የተከፈሉ ሲኖዶሶች ተመልሰው አንድ መሆን ነው፡፡ እናም ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩነቶችን ማጥበብ የሚችሉ አቋሞችን በውይይት በማፅደቅ የሰላም ሂደቱ እንዲቀጥልና በአጭር ጊዜ እንዲፈታ የቤተክርስቲያንንም ታሪክና አንድነት ማደስ ቢችል ምንኛ መልካም ነው? 
  • 2.     መከሩ ብዙ ነው፤ ብዙ የአፍሪካ ሐገራት የኢትዮጵያን እዉነተኛ ሐይማኖት እንድናስተምራቸው እኛን እየጠበቁን እያጣናቸው ነው፤ በአንድ ወቅት ከ1933 እስከ 1980ዎቹ ባሉት ዘመናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለምዕራቡ ዓለም ተግዳሮቶች ተብለው ከተዘረዘሩ አራት ዐብይ ነገሮች አንዷ ነበረች፡፡ ለምን ቢባል አሜሪካና አጋሮቿ በስለላ ድርጅቶቻቸው አማካኝነት የደረሱበት መረጃ እንደሚያሳቸው አፍሪካውያንና አጠቃላይ ጥቁሩ ዓለምን በአንድ ጥላ (እምነት) ስር በማሰባሰብ የጥቁር ፅዮናዊነትን ልታስከትልብን አፍሪካም ወደ ሐያልት ሰልፍ ልመጣብን ትችላለች ብለዉ ይሰጉ ነበር፡፡ አሁን ይህን ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ያሉ የተለያዩ ጎሳዎች የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መቀላቀል ይፈልጉ ነበር፤ አሁንም ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን አሁን ያሏት ጳጳሳትም ሆነ መምህራነ ወንጌል እንኳን ለውጭ ሊተርፉ ለሀገርም ከአዲስ አበባ የዘለለ ስራ መስራት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ከሰራን በስደት ያሉ ጳጳሳትና በየምክንያቱ የተሰደዱ የቤተክርስቲያን ሰወች በአንድ ቤተክርስቲያን ጥላ ስር ተሰባስበው እውነትን በማጣት ለተጎዳው ዓለም በተለይም እውነትን ለሚናፍቁት አፍሪካውያን ወንጌልን ለመስበክ መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡
  • 3.     በስደት ለሚኖሩት የሲኖዶስ አባላትና በእነርሱ ለሚመራው የቤተክርስቲያኗ አባላት ደግሞ አንድ ፅንፈኛ አቋም ላይ በመሆን የመከራከሪያና የመደራደሪያ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመደርደር የሰላም ድርድሩ እውነተኛ ፍሬ ለማፍራት የሚችልበትን መንገድ ተወያይቶ በመወሰን የቤተክርስቲያን ታሪክና የትውልዱን ሥነ-ልቦና ሊያቃና የሚችል ፍሬ ሐይማኖት ማፍራት እንድትችሉ እራሳችሁን ብታዘጋጁ መልካም ነው፡፡ የኛ የልጆቻችሁ ዳራችን የተሰነጠቀ በመሆኑ መድረሻችንን በቅጡ ማዎቅ ተስኖናልና ይህን የተሰነጠቀ ዳራችንን የምትደፍኑት እናንተው ናችሁ፤ ተሸንፋችሁ አሸንፉልን እንላለን-ልጆቻችሁ፡፡
  • 4.     ሁሉም የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ምእመናን በሙሉ በፍፁም ዋይታን ልቅሶ እግዚአብሔር ቤቱን መልሶ አንድ ያደርግልን ዘንድ ፀልዩ፤ ለእርቅና ለሽምግልና መልካም ሐሳቦችን በመለገስ ለሰላም አስተዋፅኦ አበርክቱ፤ በቸልታ ዝም ብንል የዚህ ትውልድ አባላት በሙሉ ታሪክ መወቀሳችን አይቀርምና፡፡
  • 5.     ጉዳዩ የሚመለከታችሁ የመንግስት ባለስልጣናት በውጭ በስደት ያለው ሲኖዶስ አባላት ፖለቲካ ስም እየለጠፉ እንዲርቁ ባታደርጉና ለቤተክርስቲያን ሰላም ድጋፍ ብታደርጉ መልካም ነው፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት መስቀል እንጅ ጠመንጃ የላቸውም፡፡ ወዳጅህ ያልሆነውን ፍፁም ወዳጅህና ባለሟል ብታደርገው ከሞት ይጋርድሃል፤ ስላንተም ይሞታል፤ በድየው ሳለ ይህንን አድርጎልኛልና ብሎ ነፍሱን ስላንተ ይሰጣል፡፡ እናም በፍቅር ማሸነፍ ከምንም በላይ አሸናፊነት ነውና በፍቅር የስደት አባቶቻችንን መልሰን ብንጠራቸው መልካም ነው፡፡  


፪. መንግስትንና የኢትዮጵያ ሕዝብን በሚመለከት

የጠቅላይ ሚንስትር መለስ የሃያ አንድ ዓመታት ብዙ ስኬት የተመዘገበበት ሲሆን አንድ አንድ ለኢትዮጵያ የማይሆን ርዕዮተ-ዓለምም የተተገበረበት በመሆኑ ጥቂት ግን ደግሞ ቸል ለማለት የማይቻሉ አንድ አንድ ጥቁር ነጥቦች አሉበት፡፡ አሁን እነዚህ ጥቁር ነጥቦች የትኞቹ ናቸው ብለን አንወያይም፤ ነግር ግን ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁናቴ አንፃር ሕዝቡና ባለድርሻ አካላት ከግንዛቤ ውስጥ ቢያስገቧቸው መልካም ነው ያልሁትን እንደሚከተለው እዘረዝራለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ የኔ የግንዛቤ አድማስ የደረሰበትን የሚያንፀባርቅ ነው እንጅ ሌላ ምንም ማለት ዓይደለም፡፡
  • 1.      ከላይ ለቤተክርስቲያን የሰጠሁትን የሰላም ጉዳይ እዚህም እደግመዋለሁ፤ መንግስት በደርግ ዘመን ብዙ ጥፋት ያጠፉ ግለሰቦችን መጀመሪያ የጥቃት ሰለባ የሆኑትን ቤተሰቦች አነጋግሮና እነርሱ ይቅር እንዲሉ አድርጎ የደርግ ባለስልጣናትን ይቅር ያለበት መንገድ ታሪክ የማይረሳው ትልቅ የሞራል ልዕልናና የሥነ-ልቦና ብስለት ያለበት አኩሪ ተግባር ነው፤ ይቅር መባባልን ይቅር ከማያሰኝ ሁኔታ ላይ ይቅርታ በማድረግ በሀገሪቱ የመቶ ዓመታት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ በመሆን አስተማረን፡፡ መሪነት ለሰላም ማለት ይህ ነው፡፡ አሁንም ባለው የፖለቲካ ስርዓትና በሌላም ምክንያት አኩርፈው ከሀገር የወጡ ብዙ ዜጎቻችን ሀገራቸውን ለማየት አንድ የሀገሪቱ የታሪክ ምዕራፍ ተካፋይ ለመሆን የኔ የሚሏት መለያቸው ኢትዮጵያን ማየት፣ ከአየሯም ተንፍሰው መጥገብ፣ ከውሃዋ ጠጥቶ ለመሪካት ዋኝቶ ለመድከም፣ ከሰለጠነው ዓለም የሸመቱትን እውቀት፣ ክሂሎትና ሙያ እንዲሁም ያላቸውን ሀብትና ጉልበት ለሀገር ለማካፈል እጅግ ይናፍቃሉ፡፡ ይህንን ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ቅድመ-ሁኔታዎች ያልበዙበት ብሔራዊ የእርቅ ማዕድ አዘጋጅቶ በዚያ ዕድል ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ የሀገር ፍቅር የሚያንቆራጥጣቸው የፈረንጅ ሀገር ኑሮና ሀብት ከዱር ገብቶ ዘፈን የሆነባቸው ሰዎች ቢጠሩበት መልካም መስሎ ታዬኝ፡፡
  • 2.     በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቅድመ-ሁኔታ ሳታበዙ የሰው ጥማት ያለባትን ሀገር በአማካሪነት፣ በመሃንዲስነት፣ በሀኪምነት፣ በድርሰት፣ በትያትር ጥበባት፣ በእርሻ፣ በማዕድን ቁፋሮ፣ በጠፈር ምርምር፣ በፖለቲካ ወዘተርፈ ያገኛችሁትን እዉቀት፣ ክሂሎት፣ ልምድና ሙያ እንዲሁም ሀብትና ጉልበት ከዚህ ከእናት ሀገራችሁ ብታፈሱት አይሻልምን? ባዳ ከላሰው ዘመድ የነከሰው እንደሚባለው የውጭ ሰዎች በሙገሳ ከሚጠሩዋችሁ የኛ ሰው ቢሰድባችሁ አይሻልም ትላላችሁን? በሀገር መኖር የመንፈስ ነፃነት ይሰጣል!!!
  • 3.     ኢትዮጵያውያን መሪያችንን አጥተናል፤ መልካም ጅምሮች ሣይጠናቀቁ፣ የታሪክ ስህተቶች ሳይታረሙ፣ ወዘተ፤ ከሁሉም ነገር አሳሳቢው የሀገር ብሔራዊነት ሳይሆን የጐሳ ብሔርተኝነት የተሻለ ጥንካሬ እንዳላቸው ይሰማኛል- እርግጠኛ ባልሆንም፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ማሰብ ያለብን ጉዳይ የብሔራዊ አንድነት ስሜት ካላዳበርን፣ የኔ ሳይሆን ያንተ ይቅደም ካላልን፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የምንሞትላት ካልሆንን ከሀገር ለክልል፣ ከክልል ለወረዳ፣ ከወረዳ ለቀበሌያችን ከቀበሌያችን ደግሞ ለቤተዘመዶቻችን የምናደላ ከሆንን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንደሆነች መቀጠል ይከብዳታል፡፡ በሀገራችን የራሳቸውን ጉዳይ ለማስፈፀም የሚጥሩ የውጭ ኃይሎች ሰለባ ከመሆን አንድንም፡፡ በኢጣሊያ የአምስት ዓመት ወረራ ጊዜ በሌ/ጀነራል ጃገማ ኬሎ ታሪክ ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢጣሊያ የኢትዮጵያን የተለያዩ ጎሳዎች እርስ በእርስ በማጋጨት የመከላከል አቅማቸው እንዲደክም የዘየደችው መንገድ ነበር፡፡ አንድ አንድ አካባቢዎች ይህንን መላ ተቀብለው የኢጣሊ ግዳይ ሲሆኑ እንደ አባ ዶዮ ያሉ አስተዋይ የጎሳ መሪዎች ግን የኢጣሊያን የተንኮል መረብ በጥበብ በጣጥሰው በመጣል እርስ በእርስ በሰላም መኖራቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ ዛሬም ሁላችን እንደ አባ ዶዮ አስተዋይ ከባሕር የሰፋ ሆድ ሊኖረን ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
  • 4.     እግዚአብሔር እጅግ መልካም፣ አስተዋይ፣ ጥበበኛ፣ የሕዝቡን እሮሮ የሚሰማ፣ የሕዝቡ ሕመም ሕመሙ የሚሆን፣ በሣል ሥነ-ልቦና ያለው ብሔራው ኩራታችን የሚሆን መሪ እንዲያድለን ተግተን መፀለይ ይገባናል፡፡ አንድ አንድ ጊዜ ምንም ይምጣ ምን በራሳችን ጉዳይ ቸልተኛ መሆን አይገባንም፡፡ መሪዎችን የሚመርጡ የፓርላማ አባላት፣ ሚንስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት መልካመ የሆነ የራሳቸው ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው መገፋፋት ያስፈልጋል፡፡ እነርሱም ከኛ መካከል የወጡ በመሆናቸው ከሕዝብና ከወገኖቻቸው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመልጡ አይችሉምና፡፡ መልካም ሃሳብ ልንመግባቸው፣ ልንመክራቸው፣ የሀገሪቱን አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲያኖሩ ልናበረታታቸው ይገባል እንጅ የማያይ የማይሰማ ጣዖት እንደሚያመሰግን ካህናተ ጣዖት የሰሩትን መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ አበጀህ! አበጀህ! ልንላቸው አይገባም፡፡ ይህ የጣዖት ካህንነት ጠባይ በቤተመንግስቱም በቤተክህነቱም መሪዎች የሕዝቡን እሮሮ እንዳይሰሙ፣ ከሕዝብ ሂስ እንዲርቁ ወዘተ በማድረግ መሻሻሎች እንዳይኖሩ አይነተኛ እንቅፋት ነው፤ እናም አወዳሾችም ተወዳሾችም ልታስቡበት ይገባል እላለሁ፡፡
   እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ፊትህን ለምሕረት አዙርልን! በደላችንም በዛ! ነገር ግን በድካማችን እንደሆነ እይ! ካንተ የሚሰወር የለምና! ኢትዮጵያ ሀገርህን፣ ሕዝቦቿን ርስትህን ይቅር በል! እንዳንተ ያለ ይቅር ባይ ቸር አምላክ የለምና፤ ሌላ ተስፋ አናደርግም! በግብሩ አንተን ደስ የሚያሰኝ የቤተክርስትያን መሪ የምዕመናን አባት አድለን! የሀገሪቱን ሕዝቦች በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመዋደድ እንዲኖሩ ምሳሌ የሚሆነን፣ ፍርድን የሚያስተካክል፣ ሀገሪቱን በስልጣኔ ጎዳና እንድትገፋ የሚያደርግ ጥበበኛ መሪም ስጠን!!! አ…ሜ…ን…!!!

No comments:

Post a Comment