እዚህ ብሎግ ላይ ተከታታይ ሁለት ጉዳዮች ላይ ፅሑፎች ይወጡ እንደነበር ይታወሳል። በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህ ተከታታይ ፅሑፎች ለረጅም ጊዜ የተቋረጡ ሲሆን የብሎጉን አንባቢዎች እጅግ ከልብ በመነጨ ይቅርታ ምህረቱ በበዛ በእግዚአብሔር እና በእናቱ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይቅርታችሁን እንደማትነፍጉኝ ተስፋ አደርጋለሁ።
ባለፈው በዚህ ርዕስ በቀረበው ክፍል ሁለት ፅሑፍ ላይ ዓለም እግዚአብሔርን ባለማዎቅ በኖረችባቸው ዘመናት የደስታ የጤነኝነት እና የምቾት እውነተኛ ምንጮች ከሰው ልጆች ርቆ የሰቆቃ እና የለቅሶ ብዙ ክ/ዘመናት እንዳለፈ እና ዛሬም እግዚአብሔርን ማወቅ እና እንደ ፈቃዱ መኖር ከብዙዎች የሰው ልጆች በመራቁ ዓለም ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ወደ ነበረው የተዘበራረቀ ህይወት እያመራች መሆኑን ተመልክተናል። ዛሬ ደግሞ ክፍል ሦስትን እነሆ!
ሰው በምድር ሲኖር ሊያተርፍ የሚያቅደው ጤናማ ህይወት፣ ደስተኝነት፣ ምቾት መሆናቸውን እና እነዚህ እሴቶችንም ለልጆቹ እና ለልጅ ልጆቹ ማስተላለፍ መሆኑን አሌ የሚል ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው እነዚህን ግቦቹን ለማሳካት የሚሰራው ለየቅል ነው። አንዳንዱ ቁሳዊ ነገሮች (ሀብታምነት) እነዚህን ግቦች ለማሳካት ሁነኛ መሳሪያ እንደሆነ ያስባል። ሌላው ደግሞ ስልጣን እነዚህን ግቦች በአቋራጭ ለማሳካት የሚጠቅም መስሎ ይታየዋል። የቀረው ክፍል ደግሞ በእውቀቱ የሚታበይ ይሆናል። “ዐመፃን፡ተስፋ፡አታድርጉ፥ቅሚያንም፡አትተማመኑት፤ባለጠግነት፡ቢበዛ፡ልባችኹ፡አይኵራ።” መዝ. 61፡10
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የደስታ ምንጭ እንደማይሆኑ ጤናማ ህይወትም ከነዚህ እንደማይመነጭ ከዚህ በፊት በነበሩት ክፍሎች ተመልክተናል። ዛሬ ደግሞ “በእውኑ ሰው በህይወቱ ጤናማ ደስተኛ እና ውጤታማ የሚሆነው ምን ዓይነት ህይወት ሲመራ ነው?” ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይሞከራል።
የሰው ልባዊነቱ ነባቢነቱ እና ህያዉነቱ ከእንስሳት ተለይቶ ማሰብ ማመዛዘን የሚችል ረቂቅ ሐሳቡንም በንግግር በሚሰማ ድምጽ በማቀናበር ለሌሎች ያለገደብ ማስተላለፍ የሚችል እና አልፎ ተርፎም ከሞት በኋላም ህይወትን የሚያጣጥም ዘላለማዊ እንዲሆን እና ደስታው ምቾቱ እና ጤናማነቱ በሥጋዊት ደማዊት ነፍሱ የሚያጣጥመው ብቻ ሳይሆን በዘላለማዊት በልባዊት እና በነባቢት ነፍሱ የሚገነዘበው በመሆኑ የደስታ ምንጩ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችም ረቂቅ የሆኑ መልካም ሐሳቦቹም ከላይ ለተጠቀሱት እሴቶች ምንጭ በመሆን ያገለግሉታል። እንዲያዉም በቁሳዊ ነገሮች የሚመጡ እርካታዎች በስጋዊት ደማዊት ነፍሱ የሚገነዘበው በመሆኑ ካስገኚው ቁሳዊ ነገር ህልውና ጋር የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን። በመሆኑም ቁሳዊ ነገር ዘለቄታ ያለው የእሴቶች ምንጭ ሆኖ አያገለግልም።
እውነተኛ የደስታ የጤናማነት እና የምቾት ብሎም የውጤታማነት ምንጮች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው።
- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔርን መውደድ እና ሕግጋቱን ማክበር
እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ በሁሉም ቦታ እና ጊዜ ያለ የዓለም እና የጠፈር ፈጣሪ እና አስተዳዳሪ ሲሆን የክብሩን እና የቸርነቱን ብዛት ተመልክቶ የሚያመሰግነው መላእክትን እና ሰውን ሲፈጥር ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስነት እንዲሁም ለአንክሮ እና ለተዘክሮ የተፈጠሩ ሌሎች ሃያ የፍጥረታት ዓይነቶችን በየመልካቸው የፈጠረ ነው። እነዚህን ፍጥረታት ሁሉ ሲፈጥር ያለ አንዳች መገኛ (እም ሃበ አልቦ) ሲሆን ጥበቡ እጅግ የመጠቀ ድካም የሌለበት ፈጣሪ የሰውን አፈጣጠር ለየት ያለ አድርጎ የሚያገለግሉትን ምግብ የሚሆኑትን እና የሚገዙለትን ፍጥረታት ከፈጠረ በኋላ የፍጥረታቱ መደምደሚያ አድርጎ የተለየ ክብር እና ሞገስ አቀዳጅቶ ፈጥሮታል።
ይህ በተለየ ክብሩ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን የተፈጠረ ሰው የእግዚአብሔርን ክብር በመሻቱ ከቀድሞ ክብሩ አነሰ። የንስሃ ልብ ለሌለው ከሰው ልጅ ቀድሞ ክብሩን ላጣው ለጠፋው ለሳጥናኤል የሚገዛ ሆነ። ነገር ግን የሰው ልጅ ከሳጥናኤል ይልቅ የተሻለ እሴት ተገኘበት። የንስሃ ልብ አልተነፈገውም። የሞት ጥፋት የምታስከትል ምኞቱ ሐሳብ አመንጪ እርሱ አልነበረምና ነገር ግን የሀሰት አባት ሳጥናኤል ስላሳተው እግዚአብሔርን ያህል ቸር ጌታ እና ገነትን ያህል መልካም ቦታ ማጣቱ በራሱ ጥፋት መሆኑን ስላገናዘበ በመፀፀት ሱባኤ ገባ። እግዚአብሔርም የሰው ልጅን መልካም ልቦና (ተነሳሂ ልቦና) ተመለከተ። የተስፋ ቃልም ተሰጠው። ልባዊ ፍጡር በመሆኑም የእግዚአብሔር ህግጋቱ በሰው ልጅ የልብ ሰሌዳ ላይ ተቀርፆ ፈቃደ እግዚአብሔርን የሚያውቅ እና በመመራመር ፈጣሪውን ለማወቅ የሚችልበት ክሂል ተሰጠው። አበ ብዙሃን አብርሃም በፍጥረታቱ ተመራምሮ እግዚአብሔርን አግኝቷልና።
እንግዲህ እግዚአብሔር ሰው የሚተዳደርባቸው ሕግጋተ እግዚአብሔርን በልቡ ቀርፆ የሰው ልብ ከዘመናት በኋላ ከመደንደኑ እና አመፀኛ ከመሆኑ የተነሳ ደግሞ የተፃፈ ሕግ ኦሪትን ሰጥቶ በአጋጣሚ ሰው ሕዝበ እግዚአብሔር ከመሆን ቢያፈነግጥ መልካም ልብ ያለው ከአመፀኛ ትውልድ የተገኘ ሰው አምላኩን ተመራምሮ ለማግኘት የሚችልበት አመዛዛኝ ልብ አድሎ ወደ ቀናችው መንገድ ጉዟችንን የመያቀና መልካም አባት የሰው ልጅ የታደለ ሀኗል።
በኋለኛው ዘመን ደግሞ ለአዳም የሰጠውን ተስፋ ዘመኑ ሲደርስ ትንቢት አናግሮ ሱባኤ አስቆጥሮ ከድንግል ማሪያም በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወልዶ የፅድቅ ብርሃን የሆነውን ወንጌን አስተምሮ በጥምቀቱ ከባርነት ወደ ልጅነት መልሶን በደላችንንም ደምስሶ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ለዓለም ቤዛ ሆኖ ተሰጥቶ በሶኦል ያሉ ነፍሳትን ማርኮ በምድር ደግሞ ድህነታችንን ሰብኮልን በትንሳኤው ትንሳኤያችንን ተስፋ አስደርጎን የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ አድሎን ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ።
እንግዲህ ይህንን ቸርነቱ የበዛ ይህንን አምላክ “እግዚአብሔርን በፍፁም ልባችሁ በፍፁም ኃይላችሁ ውደዱ” ተብለን ስንታዘዝ ይህንን ቃል የምናከብረው በደስታ መሆን አለበት። መልካም ለአደረገ ባልእንጀራ እንኳን በሐሳባችን መጥፎ ምኞት ብንመኝ አእምሯችን እንዴት እንደሚከሰን ሁላችን እናውቃለን። ሁለመናችን ለሆነ አምላካችን እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችንና በሙሉ ኃይላችን ባለመውደዳችን የሚደርስብንን የርቱዕ አእምሯችን ወቀሳ ወዴት ሄደን እናመልጠዋለን? የታዘዘውን የሚያደርግ ህሊና ግን ፍፁም ጤናማ እና ደስተኛ መሆን ይችላል።
የእግዚአብሔር ትእዛዛቱ እና ሕግጋቱ ለእኛ ለሰው ልጆች ያደሉ ናቸው። “እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርስ ተዋደዱ” ነው የተባልነው እኮ። ምንኛ መልካም ትዕዛዝ ነው። ሰላማዊ ህይወት ሰላማዊ ቤተሰብ ሰላማዊ ሰፈር ሰላማዊ ሀገር ሰላማዊ ዓለም ለመመስረት ከስጋት ቀጠና ነፃ የሆነ ዓለም የሚገኝበት ትእዛዝ!!!
ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ትእዛዛት ለእኛው ለራሳችን ያደላ ነው።
እንግዲህ እነዚህን መልካም የሆኑ ሕግጋትን በማክበር ሰላማዊ ህይወት ጤናማ ህይወት ደስተኛ ህይወት ማግኘት ይቻላል። በተቃራኒው ደግሞ እነዚህን ሕግጋት ያለማክበር ሰላማዊ ህይወት እንደሚያናጋ እና ከላይ የተገለፁትን እሴቶች እንደሚያሳጣ እሙን ነው።
የሚቀጥለው ነጥብ ደግሞ በሚቀጥለው ክፍል ይቀርባል!!! እግዚአብሔር የዚያ ሰው ይበለን!!!
…ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment