Saturday, December 4, 2010

ለምን የአፍሪካ ቀኖች በኦርቶዶክስ ለእፍሪካ ውህደት ማኅበር ላይ እንዲከበሩ አስፈለገ?


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በፌስቡክ ላይ ያለው ኦርቶዶክስ ለእፍሪካ ውህደት ማኅበር ዋና ዓላማ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖትን ለአፍሪካውያን የዋሐን መስበክ እና ማስተዋወቅ አፍሪካውያንም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖትን እንደ እናት አድርገው የጋራ የመሰባሰቢያ ጥላ እድትሆናቸው ለማድረግ እና የጋራ የድህነት መንገድ፣ የጋራ ዓላማ መዋደድ እና መፈቃቀር በአፍሪካ ሕዝቦች መካከል እንዲኖር ጥንታዊ ያልተበረዘ ያልተከለሰ በመጀመሪያው መ/ክ/ዘመን የነበረው የሐዋሪያት ስብከት የሚገኝበት የኦሬንታል ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ናቸው። የኦሬንታል ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት አባላት የሆኑ ሀገሮች 6 ሲሆኑ እነርሱም፦ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብፅ፣ አርሜኒያ፣ ሶሪያ እና ህንድ ናቸው።
ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት አቢያተ ክርስቲያናት መካከል 3ቱ በአፍሪካ ምድር የሚገኙ ሲሆኑ የሌሎቹ ከአፍሪካ ውጭ ላሉት እንደ እናት የሚታዩ እና የኦርቶዶክስ ክርስትና ዋና ማመሳከሪያ ናቸው። ስለዚህ አፍሪካ የኦርቶዶክስ ክርስትና እናት እና ጠባቂ የአደራ ባለቤትም ናት ብሎ ለመደምደም ያስችላል። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂካዊ እድገት የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ ግባ የሚባል እድገት ባለማሳየታቸው በአውሮፓውያን እና በምዕራባውያን ዘንድ የጨለማው አህጉር እየተባለች ስትጠራ ብሎም እንድ ቅርጫት ዳቦ ለቅኝ ግዛት ሲቀራመቷት እና በውስጧ የሚገኘውን የሰው ሀይል እና የተፈጥሮ ንብረቶቿን ሁሉ ዘርፈው በመውሰድ ለሀገራቸው መደለቢያ እና ማሳደጊያ አድርገው እስካሁን አፍሪካ ከራሷ በተወሰዱት ሀብቶች ሳይቀር ተመልሳ ጥገኛ እንድትሆን አንድነቷን አጥታ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላም ቢሆን ከእነዚህ መሰሪ ሀገራት የግፍ ጨዋታ ነጻ ልትሆን ከቶ አልቻለችም።
ይህ ማኅበር እነዚህ መሰሪ የአውሮፓ ሐገራት ለየዋሃን የአፍሪካ ሕዝቦች ‘ሐይማኖት” እንካችሁ በለው የሰጧቸው በግልፅ እና ‘ህጋዊ” (Official) በሆነ መንገድ ዝርፊያ እና ግፍ የተከናወነበት መርዝ የተቀላቀለበት ‘ሐይማኖት” መሳይ ግን ሐይማኖት ያልሆነ ነገር ትተው አፍሪካዊ የሆነ በአፍሪካውያን የተሰበከ የመጀመሪያው መ/ክ/ዘመን የሐዋሪያትን ሐይማኖት እንዲቀበሉ የሚያስተዋውቅ የሚሰብክ እና የአፍሪካን ሕዝቦች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስር ለማሰባሰብ ያለመ ማኅበር ነው።
ከዚህ ባሻገር ግን ይህ ዓላማ እጅጉን የተሳካ እና ከረጅም ጊዜ ስራ በኋላ ምናልባትም ከምዕተ ዓመት በኋላ ብዙሐኑ የአፍሪካ ሕዝቦች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ከሆኑ በሕዝቦቹ በራሳቸው ተነሳሺነት ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል ከነፍስ ድህነት ባሻገር ሕዝቦቹ በአንድነት ቁመው በምድራዊ ህይወት ሊኖር የሚችለውን የአህጉሪቱ በሌሎች ዓለማት የሚደርስባትን ብዝበዛ እና ሽርኘራ ለመቋቋም ወደ አንድነት (ውህደት) ለመምጣት ይህ ማህበር ግንባር ቀደም ሚናውን ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ይህ ግን የመጀመሪያው ዓላማ እጅግ በሰመረ ሁኔታ የተሳካ ሲሆን የሚመጣነው።
ማኅበሩ የተመሰረተበት ዓላማ ከሙሉ በከፊሉ ከረጅሙ ባጭሩ ከላይ የተገለጠው ሲሆን በዚህ ማኅበር የሁሉም አፍሪካ ሀገራት ዜጐች አባል መሆን እና ጠንክሮ መስራት አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ነው። ስለዚህ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዜጐችን ትኩረት ለማግኘት መስራት ወሳኝ የማኅበሩ እንቅስቃሴ ተደርጎ ይቆጠራል። ይህንን ግብ ለማሳካት እና በዙ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዜጎችን በማኅበራችን ለማካተት በኦርቶዶክስ ለእፍሪካ ውህደት ማኅበር መገናኛ ገፅ (Group Wall) ላይ እና በኦርቶዶክስ ለእፍሪካ መጦመሪያ ገፅ (Blog) ላይ እያንዳንዱን ሀገር የትኩረት ቀን ተሰጥቶት እንዲታሰብ ታቅዷል። ይህንን የእያንዳንዱን የአፍሪካ ሀገር የትኩረት ቀን በዚህ ማኅበር መሰጠቱን እንዲያስተውሉ የማኅበሩ አባላት የሚያውቋቸውን የትኩረት ቀን የተሰጠው ሀገር ዜጎችን በኢሜይል በፌስቡክ በአካል እና በተለያዩ መንገዶች በመጋበዝ የድርጊቱ ተሳታፊ እና ተዋናዮችም ለማድረግ ታቅዷል።
እነዚህ የትኩረት ቀናት ከመድረሳቸው በፊት ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ እና በርህራሄው እናቱ ቅድስት ድንግል ማሪያም በምልጃዋ እና በጸሎቷ ቅዱሳን ሁሉ በተሰጣቸው ቃልኪዳን እና አማላጅነት እንዲራዱን በያለንበት ሆነን ስለ ስራችን የቻልነውን ያህል ጸሎት እንድናደርግ የጸሎት ሳምንት የድርጊት መርሃ ግብር ተነድፎ ለማኅበሩ አባላት ግብዣ ተልኳል። እንግዲህ አባላቱ በሚችሉት ቋንቋ የሚችሉትን ጸሎት ለዚህ ስራ የተቃና ይሆን ዘንድ የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የተወሰኑ ደቂቃዎች ጊዜ እንድማይነፍጉን ባለ ሙሉ ተስፋ ነን።
በዋናው የድርጊት መርሃ ግብራችን ግን አባላቱ በ54ቱ ሀገራት ተከፋፍለው ለአንድ ሀገር በአማካይ 50 ሰው ተመድቦ በተመደበበት ሀገር ላይ መረጃዎችን ያሰባስባል። በአንድ ሀገር ላይ የተመደቡትን ሰዎች የሚያስተባብሩ እና የሚያስተናብሩ የተሰበሰበውን መረጃም በጥቅም በማዘጋጀት የሚሰሩ ለእያንዳንዱ ቡድን (ሀገር) ከ5 ያላነሱ አስተባባሪዎች ይኖሩታል። መረጃ በሚሰበሰብበት የጊዜ ክልል መረጃዎች በአባላቱ ተሰብስበው ለአስተባባሪዎች ይልካሉ። አስፈላጊውን ስራ እንዳጠናቀቁ አስተባባሪዎች ሁሉ ከገለጡ በኋላ የሀገራቱ የትኩረት ቀናት በይፋ ይጀመራል። ለእያንዳንዱ ሀገር የትኩረት ቀን የተሳካ ይሆን ዘንድ ከ5ቱ አስተባባሪዎች ቢያንስ የተጠቀሰው ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች 3ቱ እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል። እውነትነት ያላቸውን ቀደምት መረጃዎችን በማሰባሰብ እና የተሰበቡትንም በማረም ከፍተኛ ጠቀመወታ ስለሚኖራቸው የማኅበሩ አባላት ይህንን ሀላፊነት ሊወጡ የሚችሉ የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ዜጎችን በመጠቆም እንዲሁም በመጋበዝ እንዲተባበሩን ሳንጠይቅ አናልፍም። አባላቱም ምላሻቸውን እንደማይነፍጉን ባለ ሙሉ ተስፋ ነን።
አስፈላጊ የሆኑ የአሰራር ቅደም ተከተሎች ወቅቱን ጠብቀው ስለ ሚተላለፉ አባላት በንቃት እንዲከታተሉ እና ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ያለው የድርጊት መርሃ ግብር በሚችሉት ሁሉ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ከዳር እንዲያደርሱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

የማኅበሩ መስራቾች እና አስተዳዳሪዎች

No comments:

Post a Comment