ጅል
መንግስት የጅል ህዝብ ው ጤት ነው ብሎ መፃፍ እጅግ የሚዘገንን ስድብ ነው፡፡ መንግስት ጅል ሊሆን ይችላል፤
ሕዝብ ግን ከቶ ጅል ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ የተሳዳቢውን ጅልነት፤ እውርነት፤ ባዶነት ያሳያል፡፡ አንድ ሰው ጅል
ሊሆን ይችላል፡፡ ሕዝብ ግን ከቶ ጅል አይሆንም፡፡
አንድ እጅግ ብዙ ከብቶች የነበሩት ባለፀጋ ነበር፡፡
ከብቶቹ በሙሉ እየታወኩ ሁሌ ይጨነቅ ነበር፡፡ ከዚያም የሚያደርገው የሚሰራው መፍትሔ ቢያጣ በአካባቢው ወደ ነበር
አንድ ጠቢብ ሰው ጋ ሄዶ፤ ከብቶቼ ሌሊቱን ሙሉ ሲታወኩ ያድራሉ፤ ችግሩን ለይቼ ማዎቅ ተሳነኝ፤ ምን ባደርግ
ይሻለኛል ብሎ ጠየቀው፡፡ ጠቢቡም በመጀመሪያ ከብቶቹን ለሁለት ከፍለህ በሁለት ጋጣ ለየብቻ አሳድራቸው፤ በአንደኛው
ጋጣ ያሉት ከብቶች በሰላም ሲያድሩ ሁለተኛው ጋጣ ውስጥ ያሉት ግን ሲታወኩ ያደራሉ፡፡ አሁንም የታወኩትን ለሁለት
ክፈላቸው፤ ከነዚህ አንዱ ክፍል በሰላም ማደር ሲችል ሌሎቹ ግን አሁንም መታዎካቸው ይቀጥላል፡፡ በሰላም ያደሩትን
ቀደም ብሎ በሰላም ካደሩት መደቦች ጋር እየቀላቀልክ ባንድ ጋጣ አሳድራቸው፤ የሚታዎኩትን ግን አሁንም ለሁለት
እየከፈልክ በሰላም የሚያድሩትን ከሰላማዊ ክፍሎች ጋር እየቀላቀልክ ጥቂት ታዋኪ ከብቶች እስኪቀሩ ድረስ ይህንን
ተግባሪህን ቀጥል፡፡
መጨረሻ ላይ እነዚህን ጥቂት ከብቶች የሚያውካቸው አንድ ወይም ሁለት ከብት ሆኖ
ታገኘዋለህ፡፡ ስለዚህ ይህንን ከብት ወይ ለቅርጫ ተሸጠዋለህ፤ ወይም አርደህ ትበላዋለህ ብሎ መከረው፡፡
እንደተመከረውም አደረገ፤ በጥባጩም አንድ ከብት ብቻ ሆኖ አገኘው፡፡
ይህ የሚያሳየው ጥቂት ሰዎች በሚፈጥሩት የብላጣብልጥነት ሥራ ሀገር ልትጎዳ ትችላለች፡፡ የሕዝብ መሪም ጅል ሊሆን ይችላል፡፡ የሀገር ምንነት
የማይገባው፣ ሆዱና ክብሩ ብቻ አምላኩ የሆነለት፤ የሕዝብ ስቃይና ሰቆቃ የደነደነ ልቡን ዘልቆ የማይገባ፣ ድህነት
ምን ማለት እንደሆነ የማያውቅ፤ በቤተ መንግስት ወይም ከቤተ መንግስት የሚተካከል ግቢ ውስጥ እየኖረ ከእርሱ የሚበዛ
ሀብት ያላቸውን ሰዎች አይቶ እኔ እኮ ደሃ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሳይሰራ የሚበልጠው ሰው እንዲኖር እንዲፈጠርም
የማይፈልግ፤ ሥልጣኑ ዘላለማዊ ለማድረግ እንደ ሄሮድስ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ህፃናት የሚያስፈጅ (የንፁሃን
ደም መፍሰስ፣ መንገላታት የማይገደው)፤ እንዲህ ያለ መሪ፣ እንዲህ ያለ መንግስት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከቶ ግን ይህ
የጅል ሕዝብ ውጤት አይደለም፡፡ አትሳቱ! ሕዝብ ቢታገስ ጅል አይባልም፡፡
ጅል ችግርን ሸሽቶ በስደት ጫካ
ውስጥ ተደብቆ የሚያላግጥ ነው፤ ጅል አምጦ የወለደውን ሕዝብ መለሶ የሚናከስ፣ የሚሳደብ፣ የሚያሽሟጥጥ ነው፤ ጅል
ችግርን በጣቶቹ እንኳን ሊነካው የማይፈልግ፤ ነገር ግን ሌሎቹ ተጋፍጠው ችግርን ከመንገዱ እንዲጠርጉለት በዚያም
እርሱና ቢጤወቹ ሰላማዊ ጉዞ ያለ መሰናክል እንዲጓዙ ፈንጅ አምካኞችን ከፊቱ እንዲሔዱለት በርቀት ሆኖ የሚያግባባ፣
የሚያሽቃብጥ ነው፡፡
ሕዝብ ግን ችግርን እየተጋፈጠ፤ እየታገሰ፤ እያለዘበ፣ እያዋዛ፤ እያለሰለሰ ፈንቅሎ ይጥለዋል እንጅ ትቶት አይሸሽም፡፡ ሌላ ሦስተኛ ወገን ችግርን ከትክሻዬ ያነሳልኛል ብሎ አይጠብቅም፡፡
No comments:
Post a Comment